በመፈንቅለ መንግሥት ሳቢያ የሱዳን ከአፍሪካ ኅብረት በጊዜያዊነት መታገድ በሕዳሴ ግድብ ድርድር ላይ የሚኖረው ተፅዕኖ በሂደት የሚታይ መሆኑ ተነገረ

*** “ በሱዳን በተካሄደው መፈንቅለ መንግስት ሱዳናውያን ያለማንም ጣልቃ ገብነት ፍላጎታቸውን እንዲያሳኩ እንዲሁም ችግራቸውን ሲፈቱ ማየት የኢትዮጵያ ፍላጎት ነው” - አምባሳዳር ዲና ሙፍቲ

Ethiopian Foreign Ministry spokesperson Dina Mufti

Ethiopian Foreign Ministry spokesperson Dina Mufti. Source: SBS Amharic

በሳምንታዊው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጫ ቃል አቀባዩ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ወቅታዊ የዲፕሎማሲ ጉዳዮችን በተመለከተ ለጋዜጠኞች ማብራሪያ ሰጥተዋል። 

አምባሳደሩ በማብራሪያቸው እንዳሉት የአውሮፓ ሕብረት ዓለም አቀፍ ትብብር ኮሚሽነር ከምክትል ጠቅላይና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጋር በሰብአዊ እርዳታዎች ተደራሽነት ዙሪያ ተወያይተዋል፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃ እየተሰራ ባለው የሰብአዊ መብት ጥሰት ጥናት ጉዳይም ምክክር እንዳደረጉ የገለፁት አምባሳደር ዲና የጥናት ውጤቱ ህዳር መጨረሻ ይፋ እንደሚደረግ ይጠበቃል ብለዋል፡፡

የአውሮፓ ሕብረት ትብብር ኮሚሽነር ከአቶ ደመቀ በተጨማሪ ከአፍሪካ ሕብረት የሽምግልና ልኡክ መሪው የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዝደንት ኦሊሴጎን ኦባሳንጆ ጋርም አውሮፓ ሕብረት ስለሚያደርገው ድጋፍ መነጋገራቸውንም አክለው ገልፀዋል፡፡

ከሰሞኑ በአሜሪካ ባለስልጣናት የተሰጡ መግለጫዎችን በተመለከተ ጥያቄ የቀረበላቸው አምበሳደሩ ከዚህ ቀደም ከነበረው ሚዛን የሳተ እይታ በአንፃራዊነት መሻሻል የታየባቸው መግለጫዎች መሰጠታቸውን፣ የ”ሕወሓት” በአማራ ክልልና አፋር ክልል የፈፀመውን ወረራ የሚኮንኑና እንዲወጣ የሚጠይቁ እንደነበሩ አውስተዋል፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት አሁንም የችግሩ ምንጭ በይፋ እንዲወገዝና በጥልቀት ጉዳዩን መረዳት እንደሚገባቸው እምነቱ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

አምባሳደሩ ሰፊ ማብራሪያ ከሰጡባቸው ጉዳዮች አንዱ የነበረው በሱዳን የተደረገውን መፈንቅለ መንግስት ተከትሎ አገሪቱ ከአፍሪካ ሕብረት አባልነት በጊዜያዊነት የመታገዷ ነገር ነበር፡፡ አምባሳዳር ዲና “ በሱዳን በተካሄደው መፈንቅለ መንግስት ሱዳናውያን ያለማንም ጣልቃ ገብነት ፍላጎታቸውን እንዲያሳኩ እንዲሁም ችግራቸውን ሲፈቱ ማየት የኢትዮጵያ ፍላጎት ነው” ብለዋል።

የአፍሪካ ህብረት በሱዳን ላይ ያሳለፈውን ውሳኔ ኢትዮጵያ እንደምትደግፍ የተናገሩት አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ሱዳናውያን የጀመሩትን የዲሞክራሲ ሽግግር እንደሚቀጥሉበት ተስፋ እናደርጋለን ብለዋል፡፡ 

በመፈንቅለ መንግስቱ ምክንያት “ከየትኛውም የአፍሪካ ህብረት የስራ እንቅስቃሴዎች”መታገዷ ከሕዳሴው ግድብ ድርድር ጋር የሚኖረውን እንድምታ በተመለከተ የተጠየቁት አምባሳደር ዲና “ኢትዮጵያ የአፍሪካ ህብረት ውሳኔን ታከብራለች፤ የሶስትዮሽ ድርድሩም ከአፍሪካ ህብረት ውጭ እንዲካሄድ አትፈልግም” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

የወቅቱ የአፍሪካ ሕብረት ሊቀመንበር ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በሶስትዮሽ ድርድሩ ዙሪያ የምታቀርበውን የድርድር ፕሮግራም እየጠበቁ መሆኑን የተናገሩት አምባሳደር ዲና በኮንጎም ይሁን በአፍሪካ ሕብረት የሚቀርበውን ሃሳብ በተመለከተ በሂደት የምናየው ይሆናል ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

( ደመቀ ከበደ - አዲስ አበባ )


2 min read

Published

Updated

By Demeke Kebede


Share this with family and friends


Follow SBS Amharic

Download our apps

Watch on SBS

SBS World News

Take a global view with Australia's most comprehensive world news service

Watch now