በሰሜን ኢትዮጵያ ባለው ግጭት አውድ የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በተመለከተ የተቋቋመው የሚኒስቴሮች ግብረ-ኃይል በይፋ ሥራውን መጀመሩን አስታወቀ።
የግብረ ኃይሉ ዋነኛ ተልዕኮ በሰሜናዊ የኢትዮጵያ ክፍል የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን አስመልክቶ አጥፊዎችን በሕግ ተጠያቂ እንዲሆኑ ለማስቻል እና ተጎጂዎችን መልሶ ለማቋቋም ነው።
ግብረ-ኃይሉ በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን እና በተባበሩት መንግሰታት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ጽ/ቤት በጋራ በተደረገው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ምርመራ ላይ የተመላከቱ ምክረ-ሀሳቦችን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል የተጠቃለለ ስትራቴጂ እና የድርጊት መርሀ-ግብር በማጽደቅ ሥራውን ከሕዳር 20/2014 ዓ.ም ጀምሮ በይፋ ጀምሯል።
የስትራቴጂ እና የድርጊት መርሀ-ግብሩም በግጭቱ ምክንያት የተፈጸሙ ሁሉንም ከባድ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን የሚሸፍን ሲሆን መንግስት ከወሰደው የተናጠል ሰብዓዊ የተኩስ አቁም እርምጃ በኋላ በአፋር እና አማራ ክልል ተፈጸሙትንም ይመለከታል።
ግብረ-ሀይሉ ስራውን በውጤታማነት ለማከናወን እንዲያስችለው የወንጀል ምርመራ እና ክስን፣ የስደተኞች እና ተፈናቃዮች ጉዳዮችን፣ የጾታዊ ጥቃቶችን እና የሀብት ማሰባሰብን አስመልክቶ ስራዎችን የሚያስተባበሩ ከፍትህ ሚኒስቴር፣ የሰላም ሚኒስቴር፣ የሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳዮች ሚኒስቴር እና የገንዘብ ሚኒስቴርን ባዋቀረ አራት ኮሚቴዎች የሚመራ ይሆናል።
ግብረ ኃይሉ የሙያ ነፃነት ያለው ልዩ የወታደራዊ እና መደበኛ ጥምር የወንጀል ምርመራ እና ክስ የስራ ክፍል እንዲቋቋም፣ የተቋቋሙት ኮሚቴዎች ስራቸውን በሚያከናውኑበት ወቅት ተጎጂን ማዕከል ያደረገ የአሰራር ስርዓትን እንዲከተሉ እና ትኩረታቸውም ተጎጂዎች እውነትን የማወቅ እና ፍትህ የማግኘት መብቶቻቸው አንዲከበሩ እንዲሁም አቅም በፈቀደ መጠን የመልሶ ማቋቋም ድጋፍ እና ካሳ የሚያገኙበትን ስርዓት ተግባራዊ በማድረግ ላይ እንዲያተኩሩ አቅጣጫዎችን አስቀምጧል።
አክሎም፤ የፍትህ ሚኒስቴር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ግብረ-ሀይሉ የተጣለበትን ኃላፊነት በአግባቡ ለመወጣት ይችል ዘንድ አግባብነት ካላቸው ሀገራዊ እና አለምአቀፋዊ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ከአቅም ግንባታ ጋር የተያያዙ የቴክኒክ እርዳታ እና ድጋፍ እንዲገኝ ተገቢውን እንቅስቃሴ እንዲያደርጉ የስራ መመሪያ ሰጥቷል።
ሕወሓት
ሕወሓት ኢራን፣ ቱርክና የተባበሩት ዓረብ ኢምሬቶች ለኢትዮጵያ መንግሥት መሳሪያዎችን እንዳያቀርቡ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬስ ኖቬምበር 17,2021 በፃፈው ደብዳቤ አመልክቷል።
የአቤቱታውንም አስባብ ሲያመላክት መሳሪያዎቹ የዓለም አቀፍ ሕግን በተጻረረ መልኩ በሰላማዊ ሰዎችና ሰላማዊ ዒላማዎች ላይ ጥቃቶችን ለመፈጸም ውለዋል ብሏል።
አቤቱታውን በትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ስም ለተመድ ዋና ፀሐፊ የላኩት ዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ወደ ግጭት የገቡት ለሕዝባቸው ትድግና ሲባል ያለ ውዴታ እንደሆነ ጠቁመው፤ ሆኖም ሁሌም በድርድር ግጭቱን ለመግታት ፈቃደኛ እንደሆኑ በመጥቀስ መረጋጋት፣ የሰብዓዊ መብቶች መከበር፣ ረሃብ ከትግራይ፣ ከመላው ኢትዮጵያና ከአፍሪካ ቀንድ እንዲከላ እንደሚሹም ገልጠዋል።

