“ሁከት እና ብጥብጥ በማነሳሳት” ወንጀል ተጠርጥረሃል ተብሎ በእስር ላይ በሚገኘው በጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ላይ የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት የ10 ቀናት የምርመራ ጊዜ መፍቀዱ ታወቀ።
የጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ የምርምራ ጊዜውን የፈቀደው የተከሳሽ ጠበቃ ያቀረቡትን መከራከሪያ እና የዋስትና ጥያቄ ውድቅ በማድረግ ሲሆን የምርመራ ጊዜው ከግንቦት 19 ቀን 2014 ጀምሮ የሚታሰብ መሆኑን ችሎቱ ገልጿል።
ባለፈው ሳምንት ሐሙስ በጸጥታ ኃይሎች በቁጥጥር ስር የዋለው ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ፤ ለመጀመሪያ ጊዜ ፍርድ ቤት የቀረበው በማግስቱ አርብ ግንቦት 19 መሆኑ ይታወሳል። በመጀመርያ ችሎቱ የተጠርጣሪው ጠበቃ አቶ ሔኖክ አክሊሉ፤ ጉዳዩ መታየት ያለበት “በመገናኛ ብዙሃን አዋጅ መሰረት ነው” ብለው ተከራክረው እንደነበርም ይታወቃል።
ይሁንና የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በዛሬው የችሎት ውሎው “ምርመራው ጅምር መሆኑን” በመጥቀስ፤ ጉዳዩ የሚታየው “በአዋጁ ነው አይደለም የሚለውን አሁን መወሰን እንደማይቻል” መግለፁ ተጠቅሷል።
አዲስ ዘይቤ እንደዘገበው ይህን ተተንርሶም ፍርድ ቤቱ በጋዜጠኛ ተመስገን ጠበቃ በኩል የቀረበውን የዋስትና ጥያቄ ውድቅ በማድረግ የፖሊስን የምርመራ ውጤት ለማድመጥ ለሚቀጥለው ሳምንት ሰኞ ግንቦት 29 ቀጠሮ ሰጥቷል።

