አዲስ አበባ (SBS አማርኛ) – ኢትዮ ቴሌኮም የ2018 በጀት ዓመት እና የ«ቀጣዩ አድማስ ዲጂታልና ከዚያም ባሻገር 2028» ስትራቴጂ የመጀመሪያ ዓመት አፈፃፀም ሪፖርቱን ይፋ አድርጓል።
ተቋሙ በበጀት ዓመቱ 215.8 ቢሊዮን ብር ገቢ በማስመዝገብ የዕቅዱን 99.7 በመቶ ማሳካቱን የገለጸ ሲሆን፣ ይህም ካለፈው ዓመት 162 ቢሊዮን ብር ገቢ ጋር ሲነፃፀር የ33.2 በመቶ ዕድገት አሳይቷል።
በተጨማሪም 188.4 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሬ ገቢ ማስገኘቱን አስታውቋል።
የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬሕይወት ታምሩ እንደገለጹት፣ ተቋሙ ከባህላዊ የቴሌኮም አገልግሎት አቅራቢነት ወደ ሁሉን አቀፍ የቴክኖሎጂ ተቋም (Telco-to-TechCo) ለመሸጋገር የጀመረውን ስትራቴጂያዊ ለውጥ በተሳካ ሁኔታ እያስፈጸመ ይገኛል።
በ2028 ዓ.ም. የደንበኞችን ቁጥር 100 ሚሊዮን እና የቴሌብር ተጠቃሚዎችን 75 ሚሊዮን ለማድረስም ዕቅድ መያዙን ገልጸዋል።
በ2018 በጀት ዓመት 603 አዳዲስ የሞባይል ጣቢያዎች ወደ ሥራ በመግባታቸው አጠቃላይ የጣቢያዎች ቁጥር 10,613 ደርሷል። ይህም 1.5 ሚሊዮን አዳዲስ ተጠቃሚዎችን ተደራሽ እንዲሆኑ አስችሏል።
264 ተጨማሪ ከተሞች የ4G አገልግሎት ተጠቃሚ በመሆናቸው የ4G ሽፋን 82.2 በመቶ ደርሷል፤ 7 አዳዲስ ከተሞች ደግሞ የ5ጂ አገልግሎት በማግኘታቸው በአጠቃላይ 33 ከተሞች የ5G ተደራሽነት አግኝተዋል ብለዋል ፍሬሕይወት።

የተቋሙ ጠቅላላ የደንበኞች ቁጥር 90.1 ሚሊዮን የደረሰ ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ 86.9 ሚሊዮን የሞባይል ድምፅ፣ 51.5 ሚሊዮን የሞባይል ብሮድባንድ፣ 1 ሚሊዮን የፊክስድ ብሮድባንድ እና 719 ሺህ የፊክስድ ድምፅ ተጠቃሚዎች መመዝገባቸው ተገልጿል።
በዲጂታል ፋይናንስ ዘርፍም የቴሌብር ተጠቃሚዎች 60.5 ሚሊዮን የደረሱ ሲሆን፣ በበጀት ዓመቱ 4.19 ትሪሊዮን ብር የገንዘብ ዝውውር ተከናውኗል።
አገልግሎቱ ከተጀመረ በኋላ ባሉት አምስት ዓመታት ውስጥ የተከናወነው ጠቅላላ የገንዘብ ዝውውር 9.13 ትሪሊዮን ብር መድረሱን ዋና ሥራ አስፈፃሚዋ ተናግረዋል። በተጨማሪም 19.72 ሚሊዮን ደንበኞች በቴሌብር አማካኝነት የዲጂታል ብድር አገልግሎት ማግኘታቸው ተገልጿል።
እንደ ሥራ አስፈፃሚዋ ገለፃ በፋይናንስ አፈጻጸሙ የዳታና ኢንተርኔት ገቢ 31.1 በመቶ የጠቅላላ ገቢውን በመሸፈን ለመጀመሪያ ጊዜ ከድምፅ አገልግሎት ገቢ (23.5 በመቶ) በልጦ ዋነኛው የገቢ ምንጭ ሆኗል።
በተጨማሪም የEBITDA መጠን 113.1 ቢሊዮን ብር ወይም 52.4 በመቶ ሲሆን፣ ያልተጣራ ትርፍ 92.9 ቢሊዮን ብር መድረሱ ተገልጿል። የፋይናንስ ኦዲቱ ከተጠናቀቀ በኋላ የተጣራ ትርፍ በይፋ እንደሚገለጽና ከዚያም ለባለአክሲዮኖች የትርፍ ድርሻ (Dividend) ክፍፍል እንደሚደረግ ፍሬሕይወት ታምሩ ገልጸዋል።

በካፒታል ገበያ ያስመዘገበውን እድገት በተመለከተም፣ ኩባንያው ወደ ሕዝባዊ አክሲዮን ማኅበርነት ከተሸጋገረ በኋላ በግንቦት 18 ቀን 2018 ዓ.ም. በተጀመረው የሁለተኛ ደረጃ የአክሲዮን ገበያ ግብይት የአንድ አክሲዮን ዋጋ ከ300 ብር ወደ 852 ብር ማደጉን ገልጿል።
እስካሁን ድረስ ወደ 47 ሺህ የሚጠጉ የአክሲዮን ግዢ ጥያቄዎች የቀረቡ ሲሆን፣ 96 በመቶ የሚሆኑት የባለቤትነት ማረጋገጫ (Share Dematerialization) ሂደታቸው መጠናቀቁን ኩባንያው አስታውቋል።
በሪፖርቱ መሠረት የኩባንያው ጠቅላላ ሀብት (Total Assets) የ27 በመቶ እድገት በማሳየት 420 ቢሊዮን ብር ደርሷል።
ይህ ዕድገት በመሠረተ ልማት፣ በዲጂታል ፕላትፎርሞች እና በአገልግሎት ማሻሻያ ላይ በተደረገ ኢንቨስትመንት የተደገፈ መሆኑን ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ገልጸው፣ ይህም ለባለአክሲዮኖችና ለሌሎች ባለድርሻ አካላት ዘላቂ ዕሴት የሚፈጥር እንደሆነ አስታውቀዋል።

