Watch FIFA World Cup 2026™

LIVE, FREE and EXCLUSIVE

የ7ኛው ጠቅላላ አገራዊ ምርጫ 723 የምርጫ ክልሎች ውጤት ፀደቀ፤ 40 የፓርላማ መቀመጫዎች ይፋ ሆኑ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የ7ኛውን ጠቅላላ አገራዊ ምርጫ ውጤት የማረጋገጥ ሂደት በመቀጠል የ723 የምርጫ ክልሎችን ውጤት ማፅደቁን አስታወቀ። ቦርዱ በአራተኛ ዙር ይፋ ባደረገው ውጤት 40 የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና 35 የክልል ምክር ቤት መቀመጫዎች እንደተረጋገጡ ገልጿል።

gettyimages-1233571686-612x612.jpg
A man prepares his ballot at a polling booth in Bahir Dar, Ethiopia, on 21 June 2021. Credit: EDUARDO SOTERAS/AFP via Getty Images

ቦርዱ ባሳወቀው ውጤት መሠረት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በተወዳደሩባቸው የምርጫ ክልሎች አብላጫ ድምፅ በማግኘት ወደ ፓርላማ መግባታቸው ተረጋግጧል።

በዚህ ዙር የታወጁት 40 የፓርላማ መቀመጫዎች መካከል 23 መቀመጫዎችን ብልፅግና ፓርቲ ሲያሸንፍ፣ 14 መቀመጫዎች ተቃዋሚ ፓርቲዎች እና 3 መቀመጫዎች ደግሞ የግል ዕጩዎች አሸንፈዋል።

ከተቃዋሚዎች ያሸነፉት መቀመጫዎች መካከል አብዛኞቹ ብልፅግና ፓርቲ ዕጩ ባላቀረበባቸው የምርጫ ክልሎች የተገኙ ሲሆን፣ ብልፅግና ፓርቲ በቀጥታ ተወዳድሮ የተሸነፈበት ምርጫ ክልል በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የአማሮ ኬሌ ምርጫ ክልል ብቻ መሆኑ ተጠቅሷል።

በአማሮ ኬሌ ምርጫ ክልል የኢዜማ ዕጩ አወቀ አምዛዬ አሳ ከ87,521 ተመዝጋቢ መራጮች 35,545 ድምፅ በማግኘት አሸናፊ ሆነዋል።

ይህም እስካሁን ቦርዱ ካፀደቃቸው ውጤቶች ውስጥ ብልፅግና ፓርቲ ዕጩ አቅርቦ በተቃዋሚ ፓርቲ የተሸነፈበት ብቸኛ ምርጫ ክልል አድርጎታል።

እንዲሁም በግል ዕጩነት የተወዳደሩት አንጋፋው ፖለቲከኛ ዶ/ር ዲማ ነጎ እና የአዲስ ትውልድ ፓርቲ ፕሬዝዳንት ሰለሞን ታደሰ ከበደ በተወዳደሩባቸው ምርጫ ክልሎች አሸናፊ ሆነዋል።

ተቃዋሚ ፓርቲዎችና የግል ዕጩዎች ያሸነፉባቸው የፓርላማ መቀመጫዎች

በዚህ ዙር በተረጋገጡት 40 የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫዎች ውስጥ 14 መቀመጫዎች በተቃዋሚ ፓርቲዎች እና 3 መቀመጫዎች በግል ዕጩዎች ተይዘዋል።

እነሱም አፋር ክልል • ሙሳ አደም ዑመር (አፋር ሕዝብ ፓርቲ) – አዋሽ ፈንታሌ ምርጫ ክልል

ኦሮሚያ ክልል • አራርሶ ቢቂላ ኤሌሞ (የግል ዕጩ) – ደደር 2 ምርጫ ክልል • ዶ/ር ዲማ ነጎ ሰርቦ (የግል ዕጩ) – ጎሬ ምርጫ ክልል • ሰለሞን ታደሰ ከበደ (አዲስ ትውልድ ፓርቲ) – ኮፈሌ 2 ምርጫ ክልል

ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል • ደግፍ ተመስገን ሽኩሮ (ኢዜማ) – እነሞርና ኤነር ምርጫ ክልል • ዝኑር አብዱልወሀብ ኮርሴራ (ነፃነትና እኩልነት ፓርቲ) – ቅበት ምርጫ ክልል

አማራ ክልል • ጋሻው መርሻ ይማም (አብን) – እስቴ 1 ምርጫ ክልል • መልካሙ ጸጋዬ ገላው (አብን) – ላይ ጋይንት 1 ምርጫ ክልል • ገብረመሰቀል አደመ አንለይ (አዴኃን) – ገርጨጭ ምርጫ ክልል • ዩሱፍ ኢብራሂም ሽፋው (አብን) – ኩታበር ምርጫ ክልል • ሙሐመድ ቡሹራ ዑመር (ነፃነትና እኩልነት ፓርቲ) – ሳይንት 2 ምርጫ ክልል

ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል • ተፈራ ጀበሮ አባሮ (ኢዜማ) – ሎማ ቦሳ ምርጫ ክልል • ብርሃኑ ሚስል ጳሳጋላ (ነፃነትና እኩልነት ፓርቲ) – ማጀት መደበኛ ምርጫ ክልል *አዲስ አበባ* • አበበ ገመቹ ሌንጮ (የግል ዕጩ) – ምርጫ ክልል 11

ደቡብ ኢትዮጵያ ክልል • ጎበዜ ጎአ ዳዱ (ወህዴግ) – ሶዶ ዙሪያ ምርጫ ክልል • ታደሰ ወራሳ ጎዲ (ጌህዲድ) – ወናጎ 3 ምርጫ ክልል • አወቀ አምዛዬ አሳ (ኢዜማ) – አማሮ ኬሌ ምርጫ ክልል

 የክልሎች ውጤት

በአማራ ክልል ይፋ ከተደረጉት 9 መቀመጫዎች ውስጥ 4ቱን ብልፅግና ፓርቲ ሲያሸንፍ፣ አብን 3 መቀመጫዎች፣ ነፃነትና እኩልነት ፓርቲ 1 መቀመጫ እና አዴኃን 1 መቀመጫ አግኝተዋል። በኦሮሚያ ክልል ከታወጁት 6 መቀመጫዎች 3ቱን ብልፅግና ፓርቲ ሲያሸንፍ፣ 2 መቀመጫዎች በግል ዕጩዎች እና 1 መቀመጫ በአዲስ ትውልድ ፓርቲ ተወስዷል።

በደቡብ ኢትዮጵያ ከተረጋገጡት 6 መቀመጫዎች 3ቱን ብልፅግና ፓርቲ ሲያሸንፍ፣ ቀሪዎቹን ወህዴግ፣ ጌህዲድ እና ኢዜማ እያንዳንዳቸው አንድ አንድ መቀመጫ አግኝተዋል።

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ከታወጁት 4 መቀመጫዎች 2ቱን ብልፅግና ፓርቲ ሲያሸንፍ፣ ነፃነትና እኩልነት ፓርቲ እና ኢዜማ እያንዳንዳቸው አንድ መቀመጫ አግኝተዋል።

በአፋር ክልል ከታወጁት 3 መቀመጫዎች 2ቱን ብልፅግና ፓርቲ ሲወስድ፣ ቀሪውን 1 መቀመጫ የአፋር ሕዝብ ፓርቲ አሸንፏል።

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የታወጁት ሁለት መቀመጫዎች ሙሉ በሙሉ በተቃዋሚ ፓርቲዎች የተያዙ ሲሆን አንዱን ኢዜማ እና ሌላውን ነፃነትና እኩልነት ፓርቲ አሸንፈዋል።

በሐረሪ፣ በሲዳማ እና በሶማሌ ክልሎች የታወጁት ስድስት የፓርላማ መቀመጫዎች በሙሉ በብልፅግና ፓርቲ ተወስደዋል።

በአዲስ አበባ ምርጫ ክልል 11 የተመዘገበ ያልተጠበቀ ውጤት

ከተረጋገጡት ውጤቶች መካከል ትኩረት የሳበው የአዲስ አበባ ምርጫ ክልል 11 ውጤት ነው። በዚህ ምርጫ ክልል ገዢው ብልፅግና ፓርቲ ዕጩ ባላቀረበበት ውድድር፣ የትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት ቅንጅት ዕጩ እና የ6ኛው ፓርላማ አባል ዶ/ር አበባው ደሳለው ዳግም ለመመረጥ ቢወዳደሩም ድል ሳይቀናቸው ቀርተዋል።

በምትኩ በግል ዕጩነት የተወዳደሩትና የሪፍት ቫሊ ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ አበበ ገመቹ ሌንጮ አብላጫ ድምፅ በማግኘት የፓርላማውን መቀመጫ ማሸነፋቸውን ቦርዱ አስታውቋል።

የምርጫ ክልል 11 በዚህ ምርጫ እጅግ በርካታ ፓርቲዎችና ዕጩዎች የተሳተፉበት ሲሆን፣ አንድ ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ፣ የወላይታ ሕዝቦች ነፃነት ንቅናቄ፣ ራያ ራዩማ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ፣ ሕዳሴ ፓርቲ፣ ሰላም ለኢትዮጵያ ጥምረት፣ አዲስ ትውልድ ፓርቲ፣ ኢዜማ፣ ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት፣ የወሎ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ እና የግል ተወዳዳሪዎች ተሳትፈውበታል።

 129 የምርጫ ቅሬታዎች ቀርበዋል

ከምርጫው አፈጻጸም ጋር ተያይዞ በ129 የምርጫ ክልሎች ላይ ቅሬታዎች መቅረባቸውን የቦርዱ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ ገልጸዋል።

ከእነዚህ ውስጥ 86 ቅሬታዎች ውሳኔ ያገኙ ሲሆን፣ 75 በቂ ማስረጃ ባለመቅረቡ ውድቅ ተደርገዋል።

10 ቅሬታዎች ደግሞ በአቅራቢዎቻቸው ፈቃድ ተነስተዋል።

በሀላባ 1 ምርጫ ክልል በቀረበ የሕግ ጥሰት አቤቱታ መሠረት ድጋሚ የድምፅ ቆጠራ እንዲደረግ መወሰኑን ቦርዱ ገልጿል።

በአሁኑ ወቅት 253 የምርጫ ክልሎች ውጤቶች በማረጋገጥና በኦዲት ሂደት ላይ እንደሚገኙ የገለጸው ቦርዱ፣ ቀሪዎቹ 43 ቅሬታዎችም በምርመራ ላይ እንዳሉ አስታውቋል።

ቦርዱ በቀጣይ ቀናት ተጨማሪ የምርጫ ውጤቶችን ይፋ እንደሚያደርግም ገልጿል።


4 min read

Published

By Demeke Kebede

Source: SBS


Share this with family and friends


Follow SBS Amharic

Download our apps

Watch on SBS

SBS World News

Take a global view with Australia's most comprehensive world news service

Stream now