የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የፕሬስ ሴክሬታሪ የውጭ ቋንቋዎና ዲጂታ ሚዲያ ዘርፍ ኃላፊ ቢልለኔ ስዩም ለውጭ መገናኛ ብዙሃን መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽን እና የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በጥምረት የሰሩትን የሰብዓዊ መብት ጥሰት ሪፖርት ተቀብሎ የተሰጡትን ምክረ ሃሳቦች እንደሚተገብር ገልፀው፤ የሰብዓዊ መብት ሪፖርቱ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች የተፈጸሙባቸውን አካባቢዎች ሙሉ በሙሉ ሳይሆን በከፊል የዳሰሰ ነው ብሎ እንደሚያምንና ይህንንም በወቅቱ ሪፖርቱን ላቀረቡ አካላት ገልጿል ነው ያሉት ሃላፊዋ፡፡
በሌላ በኩል መንግሥት ለ2ኛ ጊዜ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቱ በሌላ አካል ይመርመር የሚለውን ሃሳብ እንዳልተቀበለው ጠቅሰው፥ "የአውሮፓ ኅብረት አካላት የሚፈልጉትን የፖለቲካ ፍላጎት በተመድ የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት በኩል ለማስፈጸም ካልሆነ በስተቀር የቀደመውን ምርመራ ላለመቀበል ምክንያት የላቸውም ብሎ እንደሚያምንም" ተናግረዋል።
የሰብዓዊ እርዳታን መንግሥት ለአማራ፣ አፋር እና ትግራይ ክልሎች የምግብ አቅርቦት ማሰራጨቱን ጠቅሰዋል።
በዚህም በሰሜን ወሎ ዞን ለወልዲያ፣ ቆቦ፣ መርሳ፣ በሰሜን ሸዋ ለአጣዬ፣ ኤፍራታ፣ አንጾኪያ፣ ሸዋ ሮቢት፣ እና መንዝጌራ ወረዳዎች እንዲሁም በአማራ ክልል በኦሮሞ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን ለባቲ፣ አርጡም ፉርሲ፣ ደዌ ሐሮዋ፣ ጂሌ ጥሙጋ እና በደዌ ጨፋ ወረዳዎች በተጨማሪም ለጋሸና፣ ላሊበላ፣ ዋድላ እና ለላስታ ወረዳዎች የምግብ አቅርቦት እንዲሰራጭ አድርጓል ነው ያሉት፡፡
በአፋር ክልል ከ1 ነጥብ 3 ሚሊየን በላይ ዜጎች አስቸኳይ የምግብ አቅርቦት በማስፈለጉ እና ከ400 ሺህ በላይ ዜጎች ከአካባቢያቸው በመፈናቀላቸው ለ21 ወረዳዎች እርዳታ መቅረቡን አስረድተዋል፡፡
በትግራይ ክልልም 225 የጭነት መኪኖች የእርዳታ አቅርቦት ይዘው ወደ ክልሉ መግባታቸውን አስረድተዋል፡፡
[ ደመቀ ከበደ ፡ አዲስ አበባ ]

