የዕርቅ ሳምንት ፋይዳ ምን ያህል ነው?

በ2020 ሃያኛ ዓመቱን ያስቆጠረው የዕርቅ ሳምንት እንደሌሎቹ 19 ዓመታት ሁሉ መጥቶ ሔዷል። ከሜይ 27 እስከ ጁን 3 በየዓመቱ የሚከበረው የዕርቅ ሳምንት፤ አውስትራሊያን የተሻለ ፍትሕ፣ እኩልነትና ዕርቅ የገባት አገር እንድትሆን የራሱን አሻራ አሳርፏል። ይሁንና የታዝማንያው ነባር ዜጋ የሕግ ባለሙያ ማይክል ማንሴል የዕርቅ ሳምንቱ ዓላማው ስቷል ባይ ናቸው።

How relevant is Reconciliation Week?

Rodney Dillon Source: SBS

የዕርቅ ሳምንት - አውስትራሊያ የነባር ዜጎቿን ባሕል አድምቃ የምታከብርበት ቢሆንም፤ የተወሰኑ የታዝማኒያ ነባር ዜጎች ቁብ ሰጥተው አያከብሩትም።

የታዝማኒያ ነባር ዜጎች የመሬት መማክርት ጉባኤ ሊቀመንበር የሆኑት ማይክል ማንሴል የዕርቅ ሳምንቱ ትርጓሜውን አጥቷል ከሚሉት መካከል አንዱ ናቸው።  

 አቶ ማንሴል የዕርቅ ሳምንቱ እንዲሻር ጥሪ አቅራቢ አይደሉም።

የእሳቸው አተያይ የአውስትራሊያ ነባር ዜጎች ፊት ተጋርጠው ያሉትን ጋሬጣዎችን ለመክላት በዓመት አንዴ ችግሮችን አንስቶ ማለፍ ሳይሆን ዓመቱን ሙሉ ሊነሳ ይገባል ባይ ናቸው። 

እሳቤያቸውንም ሲያመላክቱ፤

"እኒህ ነገሮች በዓመቱ ውስጥ በተቀሩትም 11 ወራት ቢከናወኑ ባለፉት 12 ወራት ውስጥ እኒህ-እኒህ ነገሮችን ከውነናል ማለት ይቻላል። በዓመት አንዴ ተገናኝቶ የነባር ዜጎችን ዳንስ ተመልክቶና ዘፈናቸውን አድምጦ፤ ሁሉም ድንቅ ነው ብሎ ወደ ቤት ከመሔድ ይልቅ" ብለዋል።

በሌላ በኩል ግና የዕርቅ ታዝማኒያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ማርክ ሬድመንድ የታዝማኒያ ነባር ዜጎች ዕርቅን አስመልክቶ የተወሳሰበ አተያይ እንዳላቸው ያምናሉ። 

የራሳቸውን አመለካከት ሲያንጸባርቁ ግና ለየት ያለ ምልከታ አላቸው።

"የተወሰኑ ሰዎች ዕርቅን አስመልክቶ አዋኪ ጉዳይ እንደሚሆንባቸው እንረዳለን። ሁሉም ሰው በተመሳሳይ መልኩ አይመለከተውም። እኛ በዚህ ጉዞ ላይ ነን። ዕርቀ ሰላሙ በ2000ዎቹ የተቀረጸው በፓት ዶድሰንና ፍሬድ ቼኒ ነው። ዕሳቤው የመጣው በነባር ዜጎች አረጋውያን ከሚመራው የዕርቅ መማክርት ጉባኤው ነው። ምንጨ ታሪኩ  ከበሬታን ከተላበሱ አረጋውያን ነው። ለእኒያ አረጋውያን ከበሬታዬን እቸራለሁ" የሚል።

 አቶ ሬድመንድ የዕርቅ ታዝማኒያ ቦርድ የነባር ዜጎች ውክልና ያለው፤ ወደ ትክክለኛ አቅጣጫ ኳሷን እያንከባለለ ያለና በተለያዩ ታሪካዊ አሻራ ሳቢያ ግና የፍላጎት ቅደም ተከተላቸው የተለያዩ መሆናቸውን ያመላክታሉ።

'አገራችን ላይ የተከሰተውን እውነታ በግልጽ ሳንነጋገር አገርን ለዕርቅ እንደምን ማብቃት እንችላለን?' ሲሉም ይጠይቃሉ።

የታዝማኒያ ፓላዋ አረጋዊ ሮድኒ ዲለን በበኩላቸው በወጣት ነባር ዜጎች ላይ የሚደርሱት እሥራቶች በጉዳይነት ተይዘው መፍትሔ ሊበጅላቸው እንደሚገባ ያሳስባሉ። 

እንዲሁም የአውስትራሊያ ነባር ዜጎች የራሳቸውን ማኅበረሰብ ችግሮች ለመፍታት እንዲቻላቸው በሁሉም የመንግሥት የኃላፊነት ደረጃዎች ሊሳተፉ እንደሚገባና ራሳቸውን ችለው ከውሳኔ ላይ እንዲደርሱ ያበረታታሉ።  

ማይክል ማንሴል በበኩላቸው ነባር ዜጋ ያልሆኑ አውስትራሊያውያን የዕርቅ ሳምንትን ከማክበር ባሻገር፤ ለጋዜጦች፣ ለየአካባቢያቸው ፖለቲከኞች፣ ለፕሪሚየሮችና ለጠቅላይ ሚኒስትሩ በመጻፍ ነባር ዜጎች በአውስትራሊያ ፓርላማ ውስጥ ውክልና እንዲያገኙ ሊያግዙ ይገባል በማለት ያሳስባሉ።

 

 

 


2 min read

Published

By Sarah Maunder

Presented by Kassahun Seboqa Negewo



Share this with family and friends


Follow SBS Amharic

Download our apps

Watch on SBS

SBS World News

Take a global view with Australia's most comprehensive world news service

Watch now