በትግራይና መተከል ሰብዓዊ ድጋፍ ለሚሹ ወገኖች ዓለምአቀፍ የድጋፍ ማሰባሰብ ዘመቻ ተጀመረ
" ሰብአዊነትና ፍቅር ፡ ለትግራይና መተከል" በሚል መሪ ቃል ለተፋናቀሉ እና ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች የድጋፍ ማሰባሰብ ዘመቻ መጀመሩን አስመልክቶ በጣይቱ ሆቴል አስተባባሪ ኮሚቴው ዛሬ መግለጫ ሰጥቷል።
በተለያየ መልኩ የሰብአዊ እርዳታ ሲያሰባስቡ የነበሩ 5 የተለያዩ የሰብዓዊ መብትና ሙያ ማህበራት እንዲሁም በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች በጋራ ጥምረት ሆነው እንደሚሰሩ አስታውቀዋል።
በዚህም ከዚህ ቀደም በአገር ውስጥና በውጭ አገሮች በተናጠል ሆነው የሰብአዊ ድጋፍ ሲያሰባስቡ የነበሩ አካላትን ወደ አንድ ማዕከል በመምጣት “ሰብአዊነትና ፍቅር፤ ለትግራይና መተከል” በሚል መሪ ሃሳብ ድጋፍ ማሰባሰብ መጀመራቸው ተገልጿል።
በአርቲስት እና የሰብአዊ መብት ተሟጋቹ ታማኝ በየነ መሪነት ግሎባል አሊያንስ፣ ሰብአዊ ድጋፍ ጥምረት፣ የኢትዮጵያ በጎፈቃደኛ ጋዜጠኞችና የኪነጥበብ ባለሙያዎቸ ለሰብአዊ መብቶች ማህበር፣ ለትግራይ እርዳታ አሰባሰሳብ በጎ ፈቃደኞች፣ ለመተከል እርዳታ አሰባሳቢ በጎ ፈቃደኞች እና የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ከዛሬ ጀምሮ ድጋፍ ማሰባሰብ ጀምረዋል።
የጥምረቱ ሰብሳቢ አርቲስትና የሰብአዊ መብት ተሟጋች ታማኝ በየነ "በአገር ውስጥና በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚከናወን ሲሆን ለትግራይ እና መተከል ድጋፍ የሚሹ ወገኖች የሰብአዊና ፍቅር ዘመቻ የሚደረግበት ነው" ብሏል።
"በትግራይና እና በመተከል እርዳታ የሚሹ ወገኖች የኛው ወገኖች ናቸው" ያለው ታማኝ በየነ "በመሆኑም በችግር ላሉ ኢትዮጵያውያን ልንደርስላቸው ይገባል"ብሏል::
ዘመቻው የአይዞህታ ወገናዊነትን ማንፀባረቅን ያካተተ ከመሆኑም በላይ በአዲስ አበባ ጣይቱ ሆቴል የምግብ፣ አልባሳት፣ የህክምናና ንፅህና መጠበቂያዎችን እርዳታዎችን እስከ የካቲት 16 /2013 ዓም የሚካሄድ የማሰባሰብ እንደሚሰራ አስተባባሪዎቹ ገልፀዋል።
የድጋፍ ማሰባሰብ ሥራው ከጣይቱ ሆቴል በተጨማሪ በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ዋና ጽህፈት ቤት እና በክልል የቀይ መስቀል ቅርንጫፎች ቁሳቁስ የማሰባሰብ ሥራ እንደሚሰራ ተጠቁሟል።
ከዓይነት እርዳታ የማሰባሰብ ስራ በተጨማሪ የገንዘብ ድጋፍ ማድረግ የሚችሉ ሰዎች በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኩል በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ስም በተከፈተ ልዩ የአካውንት ቁጥር 1000327016559 ላይ ገቢ የማሰባሰብ ስራ ይከናወናል ፡ ለዚህ መላው ኢትዮጶያዊ በሚችለው መልኩ ለወገኑ እንዲደርስ አስተባባሪዎች ጥሪ አቅርበዋል::
በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያዊያንም በግሎባል አሊያንስ በኩል በተከፈተ “በትግራይና መተከል ለተጎዱ ወገኖቻችን የበኩልዎን ይረዱ ዘንድ እናሳሰባለን” በሚል በተከፈተ "ጎ ፈንድ ሚ" አካውንት አማካኝነት ድጋፍ ማድረግ እንደሚችሉ ተገልጿል።
[ደመቀ ከበደ ፡ አዲስ አበባ ]

