የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን)፣ ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ(ባልደራስ)፣ እናት ፓርቲ፣ የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ትዴፓ) እና የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) መጋቢት 25 ቀን 2013 ዓ.ም በጋራ በራስ አምባ ሆቴል ባወጡት መግለጫ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል በመተከል እንዲሁም በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች እየተፈጸመ ያለውn ማንነት ተኮር ጭፍጨፋ እንደሚያወግዙ አስታውቀዋል።
ተፎካካሪ ፓርቲዎቹ በመግለጫቸው "በአገራችን ውስጥ ተንሰራፍቶ የቀጠለው የጥላቻ ትርክት ኢትዮጵያዊ ርዕያችንና አንድነታችን እንዲናጋ በማድረግ አገራችንን ለከፍተኛ የማኅበረ-ፖለቲካ ምስቅልቅል ዳርጓት ይገኛል" ሲሉ አተያያቸውን አንጸባርቀዋል።
አያይዘውም እስካሁን ስር የሰደዱ አሉታዊ ትርክቶችን ለመክላት "ሁሉን አካታች የሆነ የብሔራዊ ውይይትና ድርድር መድረክ በመፍጠር፤ ሁላችንንም አሸናፊ የሚያደርግ ፍትኃዊ አማካይ ላይ በመድረስ ዘላቂ እልባት ማምጣት ይገባል የሚል አቋም" ሲያራምዱ መቆየታቸውን አስታውሰው ማንነት ተኮር ጥቃቶች የበርካታ ዜጎችን ሕይወት መንጠቁን፣ አካል ማጉደሉን፣ ንብረት ማውደሙና ለመፈናቀል መዳረጉን አመላክተዋል።
አክለውም "በክልሎችና በፌዴራል መንግስቱ በኩል ከሚታየው ጉልህ ቸልተኝነት ጋር ተዳብለው ሲታዩ ችግሩ ግንባር ቀደም የብሔራዊ ደህንነት ስጋት ለመሆን በቅቷል፤ በመንግስት በኩል ከሚታየው ለከት የለሽ ዳተኝነት በተጨማሪ በመንግስት መዋቅር ውስጥ ያሉ አመራሮች ጭምር በጥቃቶቹ መሳተፋቸው ስጋቱንና አደጋውን ውስብስብ እንዳደረገው ለመግለጽ እንፈልጋለን" በማለት ባለ ስምንት ነጥብ አቋማቸውን ይፋ አድርገዋል።

1. በአገራችን ውስጥ በበርካታ አካባቢዎች በተለይም በኦሮሚያ ክልል፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል እና በተለያዩ የአገራችን አካባቢዎች ውስጥ በሚኖሩ የአማራ ተወላጆች እና በአጠቃላይ መጤ ተብለው በተፈረጁ ዜጎች ላይ እየተፈፀመ ያለውን ዘር ተኮር ጥቃት በጥብቅ እናወግዛለን።
2. የፌዴራሉ መንግስትና የክልሎቹ መንግስታት ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት በቁርጠኝነት መንቀሳቀስ እንዳለባቸው እናሳስባለን።
3. የችግሩን ግዝፈትና መደጋገም እንዲሁም በአገራችን አንድነትና ደኅንነት ላይ የደቀነውን ከፍተኛ አደጋ ከግምት ውስጥ በማስገባት ዘላቂ እልባት የመስጠቱ ጉዳይ እንደተጠበቀ ሆኖ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ገለልተኛ ኮሚሽን በማቋቋም በጥልቀት መርምሮ ውጤቱንም ለሕዝብ ይፋ እንዲያደርግ በአጽንኦት እንጠይቃለን።
4. የዚህ መግለጫ አካል የሆን ፓርቲዎችም ችግሩ የአገር አንድነት እና ደኅንነት ላይ የተጋረጠው አደጋ አስቸኳይ መፍትሔ እንደሚያሻው በማመን የመፍትሔ አካል ለመሆን እና የሚጠበቅብንን ኃላፊነት ለመወጣት ቁርጠኛ መሆናችንን እንገልፃለን።
5. በመንግስት በኩል እስካሁን በተፈፀሙት ጥቃቶች ውስጥ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ በተሳተፉ ግለሰቦችና ቡድኖች ላይ እንዲሁም በተለያየ ደረጃ የሚገኙ የመንግስት አመራሮች ሆነው የመከላከል ኃላፊነታቸውን ያልተወጡና በጥቃቱ የተሳተፉትን በሚመለከት በፍጥነት ተገቢው የማጣራት ሥራ እንዲሰራና በሕግ እንዲጠየቁ እንዲደረግ እናሳስባለን።
6. መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በተለያዩ አሰላለፎች ውስጥ ተካትተው ዘርና እምነት ተኮር ጥቃቶችን የሚፈፅሙ አካላትን ለማውገዝ፣ ለማጋለጥ እና ለመከላከል ብሎም ለማሸነፍና በሕግ ጥላ ስር ለማዋል በአንድነት እንዲቆሙ ጥሪያችንን እናቀርባለን።
7. በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች የምትኖሩ አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን በሙሉ በአማራ ሕዝብ ላይ በጥላቻ ኃይሎች እየተፈፀመ ያለውን ዘር ተኮር ጥቃት ለማውገዝ፣ ለማጋለጥና ለፍርድ ለማቅረብ ያለምንም ልዩነት በጋራ እንድትሰለፉ ጥሪያችንን እናቀርባለን።
8. በተፈፀሙባቸው ጥቃቶች ምክንያት ደጋፊ ወገኖቻቸውን ላጡና በጅምላ ተፈናቅለው ችግር ላይ ለወደቁት ወገኖቻችን በአስቸኳይ የነፍስ አድንና የመልሶ ማቋቋም የተቀናጀ ርብርብ እንዲደረግ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን።
በመጨረሻም በቅርቡ በኦሮሚያ ክልል ወለጋ አካባቢና በቤኒሻንጉል ክልል በተፈፀሙት ዘር ተኮር ጥቃቶች ሕይወታቸውን ላጡ ወገኖቻችን ነፍስ ይማር እያልን፣ የተለያዩ ጉዳቶች ለደረሰባቸው ወገኖች ማገገምን እንዲሁም ለወዳጅ ዘመዶቻቸው መፅናናትን እንመኛለን።

