የቡሬ የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክና የፊቤላ ኢንዱስትሪያል ኮምሌክስ ተመርቀዋል።
በምርቃቱ ሥነ ሥርዓት ላይም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ፣ ምክትል ጠቅላይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ፣ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አገኘሁ ተሻገርና ሌሎችም ከፍተኛ የፌደራልና የክልል የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል እንዳሉት በ 2010 ዓም አራት ነጥብ ስድስት ቢሊየን ብር ወጪ የተደረገበት የቡሬ ኢንዱስትርያል ፓርክ ሥራው በመጀመሪያ ምእራፉ 260.5 ሔክታር መሬት ላይ ያረፈ ነው።
አሁን ስራ የጀመረውን ሪችላንድን ጨምሮ በፓርኩ ፋብሪካ ከፍተው ለመስራት እንቅስቃሴ የጀመሩ ኢንቨስተሮች በቅርቡ ወደ ስራ ይገባሉ ብለዋል አቶ መላኩ።
የአማራ ክልል ፓርኮች ልማት ቢሮ ኃላፊ ደሴ አሰሜ በበኩላቸው በኢንዱስትሪ ፓርኩ የሚገቡ ፋብሪካዎች በዋናነት የግብርና ምርቶችን በግብዓትነት የሚጠቀሙ እና የሚያቀነባብሩ ፣ ምርታቸውን ወደ ውጭ የሚልኩ እና ለግብርናው ዘርፍ መዘመን መሠረት የሚጥሉ መሆናቸውን ገልፀዋል።
የግብርና ምርቶችን በፋብሪካ በማቀነባበርና እሴት ጨምሮ ለውጭ ገበያ በማቅረብ የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማሳደግ እገዛው የጎላ መሆኑም በምረቃው ላይ ተገልጿል።
የፓርኩ የመጀመሪያ ምዕራፍ በሙሉ አቅሙ ወደ ሥራ ሲገባ እስከ 25 ሺህ ለሚሆኑ ሰዎች የሥራ እድል እንደሚፈጥርም ይጠበቃል ተብሏል።
በተያያዘ ዜና ከኢንዱስትሪ ፓርኩ ቅርብ ርቀት ላይ የሚገኘውና በቀን 1.5 ሚሊዮን ሊትር ዘይት የሚያመርተው የፊቤላ አግሮ ኢንዱስትሪያል ኮምፕሌክስም ተመርቋል፡፡
ከበላይነህ ክንዴ ግሩፕ አንደኛው ኮርፖሬት የሆነው እና 4.5 ቢሊዮን ብር ወጪ የተደረገበት የፊቤላ አግሮ ኢንዱስትሪ ኮምፕሌክስ የአገሪቱን 60 በመቶ የምግብ ዘይት ፍላጎት የመሸፈን አቅም ያለው ሲሆን፣ በሙሉ አቅሙ ማምረት ሲጀምርም ለ3 ሺህ ዜጎች የሥራ እድል እንደሚፈጥርም ባለሀብቱ በላይነህ ክንዴ ተናግረዋል፡፡
አቶ በላይነህ የኤሌክትሪክ ኃይልና የውጭ ምንዛሬ እጥረት እንዲቀረፍላቸውና ባቀዱት ልክ ሰርተው ለአገርና ህዝብ ኢኮኖሚ ዕድገት አስተዋፅኦ ማድረግ እንዲችሉ ጠይቀዋል።
የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አገኘሁ ተሻገር ባለሀብቱን አቶ በላይነህ ክንዴንና በቡሬ የተቀናጀ አግሮኢንዱስትሪ ፓርክ ስራ የጀመረውን ሪችላንድ ፋብሪካን አመስግነዋል። የክልሉን ሰላም በማስጠበቅና አስፈላጊውን ድጋፍ ሁሉ በማድረግ የባለሀብቶችን ኢንቨስትመንት እንዲሰፋ ለማድረግ ክልሉ ዝግጁ ነው ብለዋል።
የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በምረቃ ስነስርዓቱ ላይ እንደተናገሩት "አገራችን በርካታ ባለሃብቶች ቢኖራትም ሁሉም ወደ ባለፀግነት ደረጃ ላይ አልደረሱም፡፡ ባለሃብት ማለት ገንዘብ ያለው ማለት ሲሆን ባለፀጋ ግን ልብም ያለው ነው፣ ባለፀጋ ሰርቶ ያሰራል፤ አትርፎ ያካፍላል፤ ለወጣቶች ተስፋና ስራ ይሰጣል፡፡ በዚህ መሰረት ፖለቲከኞች አገልጋይ፣ ባለሃብቶችም ባለፀጋ ከሆናችሁ ኢትዮጵያን ማሻገር እንችላለን" ብለዋል፡፡
ግዙፉን የዘይት ፋብሪካ ላስመረቁት ባለሃብት አቶ በላይነህ ክንዴና በቡሬ የተቀናጀ የኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ ቀድመው በመግባት እቅዳቸውን ተግባራዊ ያደረጉት የሪችላንድ ፋብሪካ አቶ ሙላት መንገሻ ትልቅ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
ፍራፍሬ ወደውጭ ልከን ጭማቂ ማስመጣት የለብንም ያሉት ዶክተር አብይ ሰሊጥና ኑግ ወደውጭ እየላክን ዘይት ስንቀበል ኖረናል፣ ስለዚህ ይህ መስተካከል አለበት ፤ ወደብልጽግና ለመሸጋገር ግብርናን በተሻለ መንገድ እሴት ጨምረን መስራት አለብን ብለዋል፡፡
ከ700 አመት በላይ እድሜ ያላት ቡሬ በንግድ እንቅስቃሴዋ ቀዳሜ ነበረች ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የቀደመውን ታሪኳ አስጠብቀን ማቆየት ባለመቻላችን አሁን ላይ ወደኋላ መቅረቷን አውስተዋል፡፡ አሁን የተጀመሩት ትላልቅ ስራዎች ግን ቡሬን ወደቀደመ ታሪኳ ለመመለስና ለማሳደግ ትልቅ አቅም ናቸው ብለዋል፡፡
በፊቤላ ኢንዱስትሪ ኮምፕሌክስና በቡሬ የተቀናጀ አግሮኢንዱስትሪ ፓርክ ምርቃት አስተዋፅኦ ላበረከቱ ግለሰቦችና ተቋማት ሽልማት ተበርክቷል።

