የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልላዊ መንግስት በመተክል ዞን በዜጎች ላይ ጭፍጨፋና መፈናቀል፤ በንብረት ላይ ውድመቶች ሲደርሱ የክልሉ መንግሥትና የፀጥታ መዋቅር የመከላከልና ድርጊቱን የማስቆም እርምጃዎችን መውሰድ አለመቻል አስመልክቶ ምርመራና ማጣራት ማድረጉን አስታወቀ።
ተቋሙ ወደ ሥፍራው የራሱን የጥናትና ቁጥጥር ቡድን የላከ መሆኑን ጠቅሶ በተደረገው የጥናትና ቁጥጥር ስራም በመተከል ዞን በማንዱራ፣ በዳንጉር፣ በጉባ፣ በደባጤ፣ በቡለን እና በወንበራ ወረዳዎች ማንነትን መሰረት ያደረገ የጅምላ ጭፍጨፋ የተካሄደ መሆኑን ለማረጋገጥ ስለመቻሉና እስከ ታህሳስ 14/2013 ዓ.ም ድረስ ብቻ ከ163 በላይ ዜጎች ሕይወት ያለፈና ከ31ሺ በላይ ዜጎች መፈናቀላቸውን እንደተረዳ ገልጧል።
አያይዞም “በወንጀል ድርጊቱም የክልሉ የመንግስት የአስተዳደር አካላት፣ የፓርቲ አመራሮች እና የጸጥታ መዋቅር አካላት የተሳተፉ ስለመሆናቸው እንዲሁም ጉዳዩ የሚመለከታቸው የፌደራል መንግስት አካላት የነበራቸው ድጋፍና ክትትል በጣም ዝቅተኛ መሆኑንና ጉዳዩን በቅርበት ሲከታተል የነበረው የኮማንድ ፖስት ከችግሩ ክብደትና ስፋት አንጻር የሰራው የጸጥታ ማስከበር ስራና በአጥፊዎች ላይ የወሰደው እርምጃ ደካማ እንደነበር በተቋሙ የጥናትና ቁጥጥር ቡድኑ ለይቷል” ሲል የምርመራና ማጣራት ሪፖርቱን ግኝቶች ይፋ አድርጓል።
ግኝቶቹን ተመርኩዞም “ተቋማችን የክልሉ የአስተዳደር አካላት እና የክልሉ የጸጥታ መዋቅር በወንጀል ድርጊቱ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ እጃቸው እንዳለበት ይገነዘባል” ብሏል፡፡
በማጠቃለያውም የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ሶስት ዋነኛ ምክረ ሃሳቦችን እንደሚከተለው ለፌዴራል መንግሥቱ አቅርቧል።
1ኛ. ክቡር ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አቢይ አህመድ በመተከል ዞን ከህብረተሰቡ ተወካዮች እና ከአመራሩ ጋር ተወያይተው ያስቀመጧቸው አቅጣቻዎች በፍጥነት ተግባራዊ እንዲሆኑ
2ኛ. የሚመለከተው የፌዴራል መንግሰት በወንጀል ድርጊቱ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ተሳታፊ የነበሩ አካላት በሕግ እንዲጠየቁ ፣ ፖለቲካዊ እና አስተዳደራዊ እርምጃ እንዲወስድና ለሕዝብ ይፋ እንዲደረጉ፡
3ኛ. የፌደራል የፀጥታ መዋቅር አካላት አሁን ባለው ሀገራዊ እና ክልላዊ የፀጥታ ሁኔታ ጫና እንደሚኖርባቸው እንገነዘባለን፡ ስለዚህ ህገ መንግስቱና ህጉ በሚፈቅደው መንገድ ከሁሉም ክልሎች የተቀናጀ የጸጥታ ሀይል በማዋቀር በክልሉ ተሰማርቶ የዜጎችን ህይወትና ንብረት ሊታደግ በሚችልበት ቁመና ላይ እንዲገኝ የፌደራል መንግስት ከውሳኔ እንዲደርስ ምክረ ሃሳብ እናቀርባለን።

