የባሕልና ኪነ ጥበብ ጥበቃ ተቆርቋሪው ተሾመ ወንድሙ የታዋቂውን ዓለምአቀፍ ISPA የክብር ሽልማት አሸናፊ ሆኑ

በባሕልና ኪነ-ጥበብ ዘርፍ ረጅም ዓመታት በሀገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ደረጃ የማስተዋወቅ፣ የማስተማርና ፌስቲቫሎችን ሲሠሩ፣ ለዘርፉ ዕድገትና ለውጥ ሲተጉ የነበሩት ተሾመ ወንድሙ ከፍተኛ ሽልማት ማግኘታቸው ይፋ ሆኗል።

Copy of Right Left series (5).png

Teshome Wondimu. Founder and Executive Director of Selam, 2026 International Citation of Merit Award Recipient. Credit: Credit: Selam / ISPA

በኢትዮጵያና በአውሮፓ የሚንቀሳቀሰውን "ሰላም" የተሰኘ የባህልና ኪነ-ጥበብ ዘርፍ ልማት ላይ የሚሰራ መንግሥታዊ ያልሆነ ግብረ ሰናይ ድርጅት መሥራችና ሥራ አስፈፃሚ የሆኑት ትውልደ ኢትዮጵያዊው የባሕል መሪ ተሾመ ወንድሙ፤ በኪነ-ጥበብ ዘርፍ በዓለም አቀፍ ደረጃ እጅግ ታዋቂ ከሆኑት መካከል አንዱ የሆነውን የ2026ቱ ‘International Citation of Merit’ ሽልማት አሸናፊ መሆናቸውን ዓለም አቀፉ የትርኢት ጥበባት ማኅበር (ISPA) አስታውቋል።

ይህ ሽልማት በኪነ-ጥበብ አስተዳደር፣ በበዓላት (ፌስቲቫል) ዝግጅት፣ በትምህርት፣ በምክር አገልግሎት እና በባሕል ጥበቃ ዘርፎች የላቀ አስተዋፅኦ ላበረከቱና ለረጅም ዘመን አገልግሎት ለሰጡ ግለሰቦች የሚሰጥ የክብር ሽልማት ነው።

ይህ የክብር ሽልማት ከወትሮው የተለየ የሚያደርገው በዚህ ዓመት ሽልማቱ ለተዋንያን ወይም ለኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች ከሚሰጡት ሽልማቶች በተቃራኒ፣ በራዕይና በረጅም ጊዜ ቁርጠኝነት ዓለም አቀፍ የባህል ትብብርን ላጠናከሩና ለዘላቂ የጥበብ ስነ-ምህዳር ግንባታ ለሰሩ መሪዎች መሰጠቱ ነው።

ሽልማቱ እ.ኤ.አ ጥር 15 ቀን 2026 በአሜሪካ ኒውዮርክ በሚካሄደው የISPA ጉባኤ ላይ በይፋ ይበረከታል።

በዚህ ዓመት የሽልማት ሥነ ሥርዓት ዘርፈ ብዙ የISPA ሽልማቶች የሚበረከቱ ሲሆን የታዋቂ አርቲስቶች ሽልማት (Distinguished Artist Award) አንዱ ነው።

በእዚህ የሽልማት ዘርፍ ለየት ባለ ተሰጥኦ የዓለምን የኪነ-ጥበብ ዘርፍ ያከናወኑት ተመርጠው ይሸለማሉ። ሌላኛው የፓትሪክ ሄይስ ሽልማት (Patrick Hayes Award) ሲሆን በኪነ-ጥበብ አስተዳደር ላይ የላቀ ለውጥና ፈጠራ ላመጡ የማኅበሩ አባላት ይበረከታል።

የኤንጀል ሽልማት (Angel Award) ደግሞ በገንዘብ ድጋፍ፣ በፈጠራ ወይም በደጋፊነት ለኪነ-ጥበብ ዘርፍ ዘላቂ ተጽዕኖ ላሳረፉ ግለሰቦች ወይም ተቋማት የሚሰጥ ነው።

በIPSA ይፋዊ ድረገፅ እንደተዘረዘረው የሠላም ኢትዮጵያና ሠላም ኢንተርናሽናል መሥራችና ስራ አስፈፃሚው የተሾመ ወንድሙ የስራ ታሪክ የአፍሪካን ጥበብ በዓለም አቀፍ መድረክ ለማስተዋወቅ የተደረገ የብዙ ዓመታት ጥረት ነው በሚል ተገልጿል።

አቶ ተሾመ በ "ሠላም ኢትዮጵያ" ጥበብን ለማኅበራዊ ለውጥ፣ ለማኅበረሰብ ልማትና ለኢኮኖሚ ዕድገት እንደ መሳሪያ በመጠቀም በኢትዮጵያ ዘርፈ ብዙ ለውጥ እንዲመዘገብ አስተዋፅኦ ያደረጉ ሲሆን፤ በ'ሠላም ኢንተርናሽናል' አማካኝነትም የአፍሪካ የጥበብ ተሰጥኦዎችን ከዓለም አቀፍ ተቋማትና ፌስቲቫሎች ጋር በማገናኘት ረገድ ትልቅ ሚና ተጫውተዋል።

አቶ ተሾመ በዓለም አቀፍ ደረጃ በስዊድን ብሔራዊ ኮንሰርቶች፣ በስቶክሆልም ከተማ የባሕል አማካሪነትና በተለያዩ የስዊድን የጥበብ ቦርዶች ውስጥ በማገልገላይ ሲሆኑ፤ ሥራዎቻቸው ከምስራቅና ምዕራብ አፍሪካ አልፎ እስከ ኩባ እና ቬትናም ይደርሳሉ።

በተጨማሪም የአዲስ ጃዝፌስቲቫል(Addis Jazz Festival" የፓን-አፍሪካ የኪነ-ጥበብ ነፃነት መረብ (PANAF)፣ Connect for Culture Africa (CfCA) እና ሙዚቃዊ (Muzikaw) የተሰኙ የጥበብ መድረኮች ጠንሳሽም ናቸው።

በእነዚህ መድረኮችም በርካታ ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች ከአሕጉራዊና ዓለምአቀፋዊ ባለሙያዎች ጋር ትስስር እንዲፈጥሩ፣ ስራዎቻቸውን እንዲያቀርቡና ዓለምአቀፍ ልምድ እንዲቀስሙም ዕድል ፈጥረዋል።

አቶ ተሾመ ስለተበረከተላቸው ሽልማት በሰጡት አስተያየት“ከISPA ይህንን ዕውቅና በማግኘቴ ጥልቅ ኩራት ይሰማኛል። ይህ ሽልማት የእኔን ሥራ ብቻ ሳይሆን፣ በሰላም (Selam) ውስጥ ያሉ ባልደረቦቼን፣ አርቲስቶችንና በዓለም ዙሪያ ያሉ አጋሮቻችንን የጋራ ጥረት የሚያንፀባርቅ ነው። በጋራ በመሆን ዓለም አቀፍ የባህል ውይይትን ማጠናከራችንን እንቀጥላለን” ብለዋል።

ይህ ታላቅ ዓለምአቀፋዊ ሽልማት የአቶ ተሾመ ወንድሙን የዕድሜ ዘመን ስኬት ከማብሰሩም በላይ፣ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፉ የኪነ-ጥበብ ዘርፍ ያላትን እያደገ የመጣ ተፅዕኖና የአፍሪካ ጥበብ በዓለም መድረክ ከፍ ብሎ እንዲሰማ የተጫወቱትን ሚናም ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ነው ተብሏል።

 


Share

3 min read

Published

Updated

By Demeke Kebede

Source: SBS



Share this with family and friends


Follow SBS Amharic

Download our apps
SBS Audio
SBS On Demand

Listen to our podcasts
Independent news and stories connecting you to life in Australia and Amharic-speaking Australians.
Ease into the English language and Australian culture. We make learning English convenient, fun and practical.
Get the latest with our exclusive in-language podcasts on your favourite podcast apps.

Watch on SBS
SBS World News

SBS World News

Take a global view with Australia's most comprehensive world news service