በዕለቱም የልገሳው አስተባባሪ አቶ ጃማ ፋራህ፤ የፉትስክሬይ ሮታሪ ክለብ ዓለም አቀፍ አገልግሎት ዳይሬክተር፤ በሥፍራው ለታደሙ ተጋባዥ እንግዶችና የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሰጪዎች ንግግር አድርገዋል።
በንግግራቸውም ወቅት የአሁኑ የሕክምና ቁሳቁሶች ልገሳ ወደ አፍሪካ ቀንድ ሲላክ ለ21ኛ ጊዜ መሆኑን አመላክተዋል።
በዕለቱ ወደ ዱብቲ ሆስፒታል የሕክምና ቁሳቁሶቹን ለመላክ ትብብር ያደረጉትን ግለሰቦችና ድርጅቶችንም ስለ በጎ አስተዋፅዖቻቸው ልባዊ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
በተጠቃሽነትም፤ በሜልበርን የአፋር ማኅበረሰብ፣ በተለይም በብሪስበን የአፋር ማኅበረሰብን፣ በሜልበርን የሐረሪ ማኅበረሰብ፣ ዓለም አቀፍ ለጋሾችን፣ የቅርብ ጓደኞች፣ የአፍሪካ ቀንድ ማኅበረሰብ አባላትንና የሮታሪ ክለብ አባላትን አመስግነዋል።
በታካይነትም የSBS አማርኛ ፕሮግራምን አክሎ የተለያዩ በደርዘኖች የሚቆጠሩ ድርጅቶችንና መሪዎቻቸውን ስለ ድጋፍና አገልግሎቶቻቸው ምስጋናዬ ይድረስ ብለዋል።
አቶ ጃማ በተለይ ከSBS አማርኛ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ቀጣዩ የፉትስክሬይ ሮታሪ ክለብ ዓለም አቀፍ አገልግሎት የአፍሪካ ቀንድ ፕሮጄክት የልገሳ ልም ወደ አማራ ክልል እንደሚሆን ተናግረዋል።
በዕለቱ በሥፍራው የተገኙት በአውስትራሊያ የኢትዮጵያ ተጠባባቂ አምባሳደር አንዋር ሙክታር መሐመድም በበኩላቸው፤ አሁነኛውን የዱብቲ ሆስፒታል ልገሳ አክሎ ለዓይን እማኝነት ሲበቁና የበጎ አድራጎቱን አስተባባሪ አቶ ጃማ ፋራህና ቡድናቸውንም ሲያገኙ ለሶስተኛ ጊዜ መሆኑን ጠቅሰዋል።
አምባሳደር አንዋር በፉትስክሬይ ሮታሪ ክለብ ዓለም አቀፍ አገልግሎት የአፍሪካ ቀንድ ፕሮጄክት አማካይነት ለእርዳታ ፈላጊ ኢትዮጵያውያን ወገኖች እየተደረጉ ያሉትን ሰብዓዊ ልገሳዎችንና የበጎ አድራጎት ተግባራትን ከልብ እንደሚያደንቁ ተናግረዋል።
በአውስትራሊያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ስም "ርዕይ ላላቸው መሪዎችና ድርጅቶች፤ በተለይም አይታክቴ የሆኑትን አቶ ጃማ ፋራህና ቡድናቸውን፣ እንዲሁም የሕክምና ቁሳቁሶቹ ወደ ኢትዮጵያ ለመላክ ድካምና ስልቸታ ሳያገኛቸው ጥረት ላደረጉ ሽርካዎቻችን በሙሉ ልባዊ አድናቄቴን እገልፃለሁ" ብለዋል።
ተግባሮቻቸው በሕዝብ ልብ ውስጥ በጎ ተፅዕኖን ካሳደሩቱ ውስጥ እናንት አንዱ ናችሁ።በአውስትራሊያ የኢትዮጵያ ተጠባባቂ አምባሳደር አንዋር ሙክታር መሐመድ
የልገሳውን በጎ አስተዋፅዖ ይዘት አንስውም ወደ ዱብቲ ሆስፒታል የሚላኩ የሕክምና ቁሳቁሶች በልገሳነት ብቻ የሚወሰኑ ሳይሆኑ "ተስፋን አንሰራሪና መንፈስንም አነቃቂ ናቸው" ብለዋል።
አያይዘውም "የሕክምና ቁሳቁሶቹ ወሳኝ የሕክምና ክብካቤ ተቋማትን እንደሚታደግ፣ የአካባቢውን ሐኪሞችና ነርሶች በሚመጥናቸው የሕክምና ቁሳቁስ እንደሚያጎለብታቸውና በእጅጉ ተጋላጭ፣ ድጋፍና ደህንነትን ለሚሹቱ ሕይወትን ታዳጊ የሚሆን ነው" ሲሉ አፅንዖት ሰጥተው አመላክተዋል።
አምባሳደር አንዋር ከSBS አማርኛ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ወቅትም "ይህ በበጎ አድራጎት ተግባርና ልገሳ ብቻ ተወስኖ የሚታይ ሳይሆን፤ በኢትዮጵያና አውስትራሊያ መካከል ያለውን ዓለም አቀፍ ግንኙነት አንዱ አጠናካሪ መንገድ ነው" ብለዋል።

