የኢፌዴሪ ፕሬዚደንት ሳሕለወርቅ ዘውዴ፤ ዛሬ መስከረም 24 በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባላት የጋራ ስብሰባ ላይ ተገኝተው ስለ አዲስ የመንግሥት አስተዳደር ምስረታና የፓላማ መከፈትን አስመልክተው ተናግረዋል።
ኢትዮጵያውያንን ስለ አገርና ሕዝብ አንድነት ሲያመላክቱም "ወደንም ጠላንም ተለዋጭ አገር የለንም" በማለት ጥላቻን እንዲጠየፉ፣ መቻቻልና መደማመጥን እንዲያጎለብቱ አሳስበዋል።
አክለውም፤
- ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት በእጅጉ ተፈትናለች፤ሉዓላዊነቷንና አንድነቷን ለማናጋት ተሞክሯል
- የዚህ ሁሉ ጽናትና ትግል ለዛሬዋ ቀን አድርሶናል። እዚህ እንድንደርስ ደማቸውን ያፈሰሱትን የመከላከያ ሰራዊት እንዲሁም ውድ ኢትዮጵያውን ማስታወስ ተገቢ ነው ኢትዮጵያ የሕዝብ ውክልና ስርዓት የ90 አመት ልምድ አላት
- የኑሮ ውድነትና ስራ አጥነት ወሳኝ መፍትሔ የሚፈልጉ የኢኮኖሚ ፈተናዎች ሆነው ቀጥለዋል
- ያለፈው ዓመት በሕዳሴ ግድብ ስኬት የተመዘገበበት ነበር
- ኢትዮጵያን ለማፍረስ የሚሹ አሸባሪዎችን ሴራ በሀገራቸው ህልውና የማይደራደሩ ኢትዮጵያውያን ሆ ብለው በመነሳት ማክሸፍ ችለዋል
- በሕግ ማስከበር ዘመቻው ለተጎዱ ዜጎች የሚደረገው ሰብዓዊ እርዳታና ወደ ቀዬያቸው እንዲመለሱ የማድረግ ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል
- የተንሰራፈው ስራ አጥነት እንዲቃለል የኑሮ ውድነት እንዲስተካከል የገጠሙን ችግሮች እንዲፈቱ መንግስት ትኩረት ሰጥቶ ይሰራል
- የአቅርቦትና የፍላጎት አለመጣጠምን፣ የተዛባ የንግድ ስርአት፣ በዝናብ ጥገኝነት ላይ ያለውን ግብርና ለማስተካከል ይስራል፤ የንግድ ስርአቱን የማስተካከል ስራ ይሰራል
- የመንግስት ገቢን በ2014 በጀት ዓመት 600 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር ለማድረስ ግብ ተጥሏል
- በበጀት አመቱ በግብርናው መስክ 592 ሚሊዮን ኩንታል የሰብል ምርት ለማምረት ግብ ተጥሏል
- አረንጓዴ አሻራን በማስቀጠል የደን ሽፋኑ እንዲጨምር ይድረጋል
- በማኒፋክቸሪንግ ዘርፍ አዳዲስ ዘርፎች እንዲከፈቱ ይደረጋል፤ የማኒፋክቸሪንግ ምርት እንድስፋፋ ይደረጋል፤ ማኒፋክቸሪንግ ለጠቅላላ ኢንዱስትሪ የሚያደርገውን አስተዋጾ ከፍ ለማድረግ ይሰራል
- ማዕድናትን በአይነት በመጠንና በብዛት ለውጭ ገበያ በማቅረብ የውጭ ምንዛሬን ከፍ ለማድረግ ይሰራል
- የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪውን አቅም በመገንባት የአገር ውስጥ ፍላጎትን በአገር ውስጥ ተቋራጭ ለመሸፈን ይሰራል
- የመንገድ መሰረተ ልማት ፍትሃዊና የተቀናጀ በማድረግ ይሰራል
- በከተሞች የመሬትና የመኖሪያ ቤት አቅርቦት ውጤታማነትን ለማሻሻል ይሰራል
- የከተሞች የምግብ ዋስትና ስርአትን የማሳደግ ስራ ይሰራል
- ከቱሪዝም ዘርፍ የሚገኝ ገቢን ለማሳደግ የቅርስ እንክብካቤ ስራ ይሰራል፤ ነባሮች ይታደሳሉ፤ አዳዲስ የቱሪስት መስህቦች ይስራሉ፣ ሁሉም ክልሎች በአዲስ አበባ ላይ የታየውን የቱሪስት ማዳረሻ ልማት ተሞክሮ ወስደው ይሰራሉ
- የመጠጥ ውሃና የግል ንጽህና ጥበቃን የማስፋፋት ስራ ይሰራል
- ለገጠር ኤሌክትሪክ ሃይል የማዳረስ ስራ ይሰራል ብለዋል።
ዛሬ የተከናወነው የምክር ቤቶቹ የመክፈቻ ጉባኤ ተጠናቋል።
አመሻሹን በመስቀል አደባባይ የጠቅላይ ሚኒስትሩ በዓለ ሲመት እንደሚከናወን የሚጠበቅ ሲሆን ከተለያዩ ወዳጅ አገራት የመጡ የአገር መሪዎችና ተወካዮች ለመታደም ተገኝተዋል።
Share

