የሌበር ሴናተር ኪምበርሊ ኪችንግ በ52 ዓመታቸው በድንገት ሜልበርን ውስጥ ለሕልፈተ ሕይወት ተዳርገዋል።
የሞታቸው አስባብም የልብ ድካም ሊሆን እንደሚችል ተገምቷል።
ሕልፈተ ሕይወታቸውን ተከትሎ ከሥራ ባልደረቦቻቸውና ወዳጆቻቸው የሐዘን መግለጫ መልዕክቶች በማኅበራዊ ሚዲያ በኩል እየጎረፉ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ስኮት ሞሪሰንም "በዜና ዕረፍታቸው ጥልቅ ሐዘን" እንደተሰማቸው ገልጠዋል።

የቀድሞው ሌበር መሪ ቢል ሾርተን ሴናተር ኪቺንግ ዛሬ ሐሙስ ምሽት "በልብ ሕመም ተሰቃይተው" እምብዛም ሳይቆዩ ሕይወታቸው እንዳለፈ ገልጠዋል።
የተሰማቸውን ጥልቅ ሐዘንጋር አያይዘውም "የሳቸው ህልፈት ለሌበርና ለአገር ትልቅ እጦት ነው" ብለዋል።
የተቃዋሚ ቡድን ሌበር መሪ አንቶኒ አልባኒዚም በበኩላቸው የተሰማቸውንን ሐዘንና በሴናተር ኪምበርሊ ኪቺንግ ድንገተኛ ሞት የሌበር ቤተሰብ የተደናገጠ መሆኑን በቲዊተር ገፃቸው አስፍረዋል።

ሴናተር ኪቺንግ የተወለዱት በ1970 ብሪሰበን ከተማ ሲሆን ከ2001 እስከ 2004 የሜልበርን ማዘጋጃ ቤት ተመራጭ ሆነው አገልግለዋል።
የጤና ሠራተኞች ማኅበር ዋና ሥራ አስኪያጅ ሆነው ሠርተዋል።
ከሶስት አሠርት ዓመት በላይ የሌበር ፓርቲ አባል የነበሩ ሲሆን በ2016 የሌበር ሴናተር ሆነዋል።
የፓርላማ የውጭ ጉዳዮች፣ መከላከያና ንግድ ኮሚቴ ምክትልና ዋና ሰብሳቢ ሆነው መርተዋል።

