በዘንድሮው የ2020 የሜልበርን ዋንጫ ፈረስ ውድድር 'Twilight Payment' አንደኛ 'Tiger Moth' ሁለተኛ 'Prince of Arran' ሶስተኛ በመሆን ውድድራቸውን አጠናቅቀዋል።
ከውድድሩም በኋላ በሰባት ዓመታት ውስጥ ለስድስተኛ ጊዜ የተወዳዳሪ ፈረስ ሕይወት አልፏል።
ሕይወቱን ያጣው ፈረስ 'Anthony Van Dyck' በአንደኛ እግሩ ላይ የደረሰበት የአጥንት መጋጠሚያ ስብራት ብርቱ ሕመም ለሕልፈቱ አስባብ እንደሆነ ተገልጧል።
ሆኖም አንድ የእንሰሳት መብቶች ተሟጋች ድርጅት የፈረሱን ሞት አስመልክቶ ምርመራ እንዲካሄድ ጥሪ አድርጓል።
ከፍሌሚንግተን ፈረስ መወዳደሪያ ቅጥር ግቢ ውጪም በቅንጅት ለፈረስ ውድድር የደህንነት ጥበቃ አባላት የተቃውሞ ሰልፍ ተካሂዷል።
አንዲት የቅንጅቱ ቃል አቀባይ የፈረሱን ሕልፈት አስመልክተው የመረረ ተቃውሟቸውን ሲያሰሙ፤
"የፈረሱ ሞት አኛን አላስደመመንም። በእጅጉ አበሳጭቶናል። ለቁማር ትርፍ ለሚካሄድ የፈረስ ውድድር ፈረሶች ይሞታሉ። አውስትራሊያ ውስጥ በየሶስት ቀናቱ አንድ ፈረስ በፈረስ መጋለቢያ ሥፍራ ይሞታል። ስለ ፈረስ ሞት አሁን መስማታችን ብቸኛው ምክንያትም የሜልበር ዋንጫ በመሆኑ ነው። የዓለም ዓይኖችም ይህን ተመልክተዋል። ይህ እየሆነ ያለው ለቁማር ትርፍ ሲባል ነው። ሰዎች ገንዘብ እስከሰጧቸው ድረስ ፈረሶችን መገደላቸውን ይቀጥላሉ" ብለዋል።

