ሜልበርን ላይ በተጣለው የኮሮናቫይረስ ገደብ ሳቢያ ገቢያቸውን ላጡ ድጎማ ሊደረግ ነው

*** የተመድ ቢሮ የትግራይ ደኅንነት ጉዳይ ውስብስብ መሆኑን ገለጠ

SBS Amharic

Source: SBS Amharic

የአውስትራሊያ ፌዴራል መንግሥት ሜልበር ላይ በተጣለው የኮሮናቫይረስ ገደብ ሳቢያ ገቢያቸውን ላጡ የአስቸኳይ ጊዜ ድጎማ እንደሚያደርግ አስታወቀ። 

የፌዴራል መንግሥቱን የአስቸኳይ ጊዜ ድጎማ የሚያገኙት ባለፉት ሰባት ቀናት ገቢያቸው የተሰተጓጎለባቸው ሰዎች ሲሆኑ፤ ዕድሚያቸው ከ17 ዓመት በላይ ሆኖ በሳምንት ከ20 ሰዓታት በላይ ይሠሩ ከነበረ ለ$500 ከ20 ሰዓታት በታች ይሠሩ የነበሩ ለ$325 ድጎማ ከሰኞ ጁን 7 ጀምሮ በሴንተርሊንክ በኩል ማመልከት ይችላሉ።  

ድጎማውን ለማግኘት ከ10 ሺህ ዶላርስ ያነሰ ተቀማጭ ያላቸውና ሌላ ምንም ዓይነት ተጨማሪ ድጎማ የማያገኙ መሆናቸውን ማረጋገጥ ይጠበቅባቸዋል። 

ሌበር የፌዴራል መንግሥቱ  የድጋፍ እጁን ለመዘርጋት እስካሁን ማቅማማቱን አንስቶ ተችቷል። የሌበር ምክትል መሪ ሪችድ ማልስ አክለውም "የሞሪሰን መንግሥት ለወሸባና ክትባት ክሽፈት ባይበቃ ኖሮ ቪክቶሪያ ላይ ገደብ ባልተጣለባት ነበር ብለዋል።

በሌላ በኩል የቪክቶሪያ ባለ ስልጣናት ሁኔታቸው መሻሻል ካሳዩ ሜልበርን ላይ የተጣለው ገደብ ምናልባትም ከቀነ ገደቡ ቀደም ብሎ ሊነሳ እንደሚችል አመላክተዋል።

በዛሬው ዕለት ሶስት ሰዎች ቪክቶሪያ ውስጥ በቫይረሱ መጠቃታቸው ተመዝግቧል።

የሪጂናል ቪክቶሪያ ገደብ ዛሬ ከምሽቱ 11.59pm ጀምሮ ይነሳል። 

ባለፉት 24 ሰዓታት ውስጥ 23,921 የቪክቶሪያ ነዋሪዎች የኮሮናቫይረስ ክትባት ተከትበዋል።

ትግራይ

የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ የትግራይ ጸጥታ ጉዳይ በእጅጉ ውስብስብና ዋዣቂ ሆኖ ያለ መሆኑን አመለከተ። 

 

በመካሄድ ላይ ያሉት ግጭቶች ከፍተኛ እንቅስቃሴ የተመላባቸው በመሆናቸው፤ ባብዛኛው በገጠር አካባቢዎች ሰብዓዊ ግልጋሎቶችን ማስፋትና ማቀድን እየገቱ መሆኑንም አክሎ ገልጧል።

በሌላም በኩል ከወርኃ ማርች ጀምሮ ግጭቶች በኤርትራ ድንበር ከሰሜናዊ ምዕራብ እስከ ምስራቃዊ ዞኖች የተገቱ ቢሆንም ባብዛኛው የተደራሽነት እገዳ እንደሚገጥም አመልክቷል።

የረድኤት ሠራተኞችን ጨምሮ በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚደርሱ አመፆችና ጥቃቶች ቀጥለው ያሉ መሆናቸውን የጠቀሰው ቢሮ፤ ከግጭቱ መነሳት ጀምሮ ዘጠኝ የረድኤት ሠራተኞች የተገደሉ መሆናቸውን ገልጧል። ሟቾቹ ሁሉም ኢትዮጵያውያን መሆናቸውንም አስታውቋል።  

የጤና ተቋማት ከፌብሪዋሪ እስከ ኤፕሪል ባሉት ጊዜያት ጾታ ተኮር ጥቃቶች የተፈጸመባቸው 1,288 ሰዎችን ተቀብለው የሕክምና ግልጋሎቶችን እንደሰጡና የተጠቂዎች ቁጥር ከዚያም በላይ እንደሚሆን አመላክቷል። 

ቢሮው ከማርች 27 እስከ ሜይ 31 ባሉት ጊዜያት ውስጥ የተመድ ኤጄንሲዎችና ሽርካዎች አቅርደውት ከነበረው 5.2 ሚሊየን የምግብ እርዳታ ማድረስ የቻሉት ለ2.8 ሚሊየን ሰዎች መሆኑን ገልጧል።

የአስቸኳይ ጊዜ መጠለያዎችንና ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶችን ለ3 ሚሊየን ሰዎች ለማድረስ ተልሞ የነበረ ቢሆንም መግለጫውን እስካወጣበት ቀን ጁን 2 ድረስ ግና ማድረስ የቻለው ካለመው 15 ፐርሰንት ያህል ወይም ለ430,000 ብቻ መሆኑን አስታውቋል።

 


2 min read

Published

Updated

By NACA

Presented by Kassahun Seboqa Negewo


Share this with family and friends


Follow SBS Amharic

Download our apps

Watch on SBS

SBS World News

Take a global view with Australia's most comprehensive world news service

Watch now