የሥራ ዳታ
የአውስትራሊያ የሥራ አጥነት ቁጥር 6.2 ደርሷል።
ከ 590,000 በላይ አውስትራሊያውያን በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ሳቢያ ኤፕሪል ውስጥ ሥራቸውን ማጣታቸውን የአውስትራሊያ ስታቲስቲክ ቢሮ አስታውቋል።
ይህም ከሴፕተምበር 2015 ወዲህ ከፍተኛው የሥራ አጥነት ቁጥር ሆኖ ተመዝግቧል። የሥራ አጥነቱ ቁጥር የፌዴራል መንግሥቱ $130 ቢሊየን የሥራጠባቂ የደመወዝ ድጎማ ባይታከልበት ኖሮ ቁጥሩ ከዚህም የናረ ይሆን ነበር።
የፌዴራል መንግሥቱ የሥር አጥነት መጠን በዚህ ዓመት 10 ፐርሰንት ይደርሳል የሚል ግምት አሳድሯል።
ይህንኑ የቢሮውን የሥራ ዳታ ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ስኮት ሞሪሰን በጠሩት ጋዜታዊ መግለጫቸው "600 000 ያህል ሥራዎች ከስመዋል፡፡ እያንዳንዳቸው ሥራቸውን ላጡት አውስትራሊያውያን፣ ለቤተሰቦቻቸውና ለማኅበረሰባቸው ቅስም ሰባሪ ናቸው። በጣሙን ፈታኝ ዕለት" ብለዋል።
ሥራ አጥነቱ እያንዳንዱን የአውስትራሊያ ስቴትና ክፍለ ግዛት ያካተተ ሲሆን፤ ኒው ሳውዝ ዌይልስ 6 ፐርሰንት፣ ቪክቶሪያ 5.2 ፐርሰንት፣ ኩዊንስላንድ 6.8 ፐርሰንት፣ ደቡብ አውስትራሊያ 7.2 ፐርሰንት፣ ምዕራብ አውስትራሊያ 6 ፐርሰንት፣ ታዝማኒያ 6.2 ፐርሰንት ኖርዘን ቴሪቶሪ 6 ፐርሰንት፣ የአውስትራያ ካፒታል ቴሪቶሪ 4.2 ፐርሰንት ደርሷል።
ከ 6 ሚሊየን በላይ አውስትራሊያውያን በሥራጠባቂ ደመወዝ ድጎማ ያሉ ሲሆን፤ 1.6 ሚሊየን በሥራፈላጊ የሥራ አጥነት ድጎማ ተቀባይነት ይገኛሉ።
የአየር መንገድ አክሲዮን ግዢ
የኩዊንስላንድ መንግሥት የቨርጂን አውስትራሊያ አየር መንገድን አክሲዮን እገዛለሁ ብሎ መነሳት በፌዴራል መንግሥቱ በኩል ትችትን አስከትሏል።
በመንግሥት ስር ያለው የኩዊንስላንድ ሙዋዕለ ንዋይ ኮርፖሬሽን በኪሳራ ሳቢያ ባለፈው ወር በፈቃደኝነት የውክልና አስተዳደር ስር የሚገኘውን አየር መንገድ ለመግዛት ዕሳቤውን ይፋ አድርጓል።
ይሁንና የፌዴራል የአገር ውስጥ ጉዳዮች ሚኒስትር ፒተር ዳተን ኩዊንስላንድ $7 ቢሊየን ዕዳ እያለባት ለአክሲዮን ግዢ የሚያበቃ አቅም የላትም ለምርጫ የሚሆን ፖለቲካዊ ስልት ካልሆነ በስተቀር ሲሉ የኩዊንስላንድ መንግሥትን ዕሳቤ ለማጣጣል ሞክረዋል።
የቻይና - አውስትራሊያ ንግድ
አውስትራሊያ የኮሮናቫይረስ መነሻ ይመርመር ብላ ከመነሳቷ ጋር ተያይዞ በቻይናና አውስትራሊያ መካከል የተባባሰውን መሸካከር ተከትሎ ውጥረት ውስጥ ለገባው ንግድ ቻይና ጸጥታዋን ሰብራ ምላሽ ሰጥታለች።
በዚሁ ሳምንት ውስጥ የአውስትራሊያ የንግድ ሚኒስትር ሳይመን በርሚንግሃም ከቻይናው የንግድ ሚኒስትር በኩል ምላሽ ተነፍጌያለሁ ብለው ነበር።
ሆኖም የቻይና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዛዎ ሊጂያን ቻይና ከአውስትራሊያ ጋር መልካም ግንኙነትን እንደምትሻና በአውስትራሊያ በኩል አመኔታና ትብብር እንደሚያስፈልግም ሲገልጡ፤
" የሰከነ የቻይና - አውስትራሊያ ግንኙነት ለሁለቱም አገራት የጋራ ጥቅሞች አስፈላጊ ነው፤ ይሁንና የሁለትዮሽ ጥረቶችን ግድ ይላል። አውስትራሊያ ግማሽ መንገድ ላይ እንደምትገናኘን፣ የጋራ መከባበር፣ እኩልነትና የጋራ ትሩፋት፣ የቻይናና አውስትራሊያን ስትራቴጂያዊ ሽርካነት መንፈስን የተላበሰ የቻይና - አውስትራሊያ የጋራ አመኔታና ትብብርን ትተገብራለች ብለን ተስፋ እናደርጋለን" ብለዋል።
ሴናተር በርሚንግሃም በበኩላቸው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጫን ተከትሎ ከቻይና መንግሥት ጋር በቅርቡ በአውስትራሊያ የከብት ሥጋ የውጭ አቅርቦት ላይ ቻይና የጣለችውን ዕገዳ አስመልክቶ እንደሚነጋገሩ ያላቸውን ተስፋ ገልጠዋል።

