"ረቂቅ የወንጀል ሥነ ሥርዓትና የማስረጃ ሕጉ ከሰብአዊ መብቶች አንጻር ሊሻሻል ይገባል" - ኢሰመኮ

*** የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን

EHRC

Dr Daniel Bekele, Chief Commissioner of Ethiopian Human Rights Commission. Source: Supplied

ኢሰመኮ "ረቂቅ የወንጀል ሥነ ሥርዓትና የማስረጃ ሕጉ ከሰብአዊ መብቶች አንጻር ሊሻሻል ይገባል" አለ

ትናንት ለሚዲያዎች ባደረሰው መግለጫ እንዳስታወቀው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) "ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የወንጀል ሥነ ሥርዓትና የማስረጃ ሕግ (Criminal Procedure Code and Evidence Law) በርካታ ድንጋጌዎች ከሰብአዊ መብቶች ሕግና መርኆች አንጻር ሊሻሻሉ እንደሚገባ" ገልጿል።

ኮሚሽኑ ዛሬ ይፋ ባደረገው ባለ 33 ገጽ ሪፖርት ማሻሻያ እንዲደረግባቸው ካሳሰበው ነጥቦች መካከል ዋና ዋናዎቹ:-

~ መርማሪ ፖሊስ ተጠርጣሪን ለመያዝ፣ ለብርበራ እና በልዩ የወንጀል ምርመራ ዘዴ ኃይል ሊጠቀም የሚችለው፤ ጥንቃቄ የማድረግን፣ የሕጋዊነትን፣ የጥብቅ አስፈላጊነትን፣ የተመጣጣኝነትን እና አድልዎ ያለማድረግን መርኆችን ባከበረ መልኩ እና ሌላ አማራጭ መንገድ የሌለ መሆኑ ሲረጋገጥ ብቻ መሆኑን፤ በዚህ ረገድ ተጠያቂነትን የሚያሰፍን ሥነ ሥርዓት በግልጽ ሊደነገግ የሚገባ መሆኑን፣

~ በወንጀል የተጠረጠረ ወይም የተያዘ ሰው የቃል አቀባበል ሂደትን ጨምሮ በማቆያ ቤት ወይም በእስር ወቅት ኢሰብአዊ አያያዝ እንዳይፈጸምበት እና ተፈጽሞም ሲገኝ ተጠያቂነት እንዲኖር የሚያስችሉ ማሻሻያዎች ሊካተቱ የሚገባ መሆኑን፤

~ ለጥቃት ተጋላጭ የሆኑ የማኅበረሰብ ክፍሎች በእስር በመያዝ፣ በምርመራ፣ በክስ እንዲሁም ምስክርነት በመስጠት ሂደት ሰብአዊ መብቶቻቸውን፣ ክብራቸውና ልዩ ፍላጎቶቻቸውን የበለጠ ሊያስከበሩ የሚያስችሉ ማሻሻያዎች ሊካተቱ እንደሚገባ፣

~ ሕፃናት ከእናታቸው ጋር የሚታሰሩበትን ሁኔታ ለማስቀረት ነፍሰ ጡር ለሆነች ሴት ወይም ከዘጠኝ ዓመት በታች የሆነ ሕጻን ወይም የምንትንከባከበው የአካል ጉዳተኛ ልጅ ላላት እናት የዋስትና መብት ወዲያውኑ እንዲፈቀድ እና በጥፋተኝነት ፍርድ ጊዜም ከእስር ውጪ ያለ ቅጣት (Non-Custodial Measures) በአማራጭነት እንዲወሰድ፣

~ ማንኛውም የታሰረ ሰው በተጠረጠረበት ወይም በተከሰሰበት ወንጀል ጥፋተኛ ሆኖ ቢገኝ ሊጣልበት የሚችለውን የመጨረሻውን የእስር ቅጣት እርከን ያክል በእስር የቆየ እንደሆነ ወዲያውኑ ሊለቀቅ የሚገባ መሆኑን፣

~ ለሕገ ወጥ መያዝ ወይም ለእስር የተዳረገ ሰው ካሳ የሚያገኝበት ሥነ ሥርዓት ሊደነገግ የሚገባ መሆኑን የሚመለከቱ ናቸው፡፡

ኮሚሽኑ በሪፖርት ከ30 በላይ በሆኑ ድንጋጌዎች ላይ የማሻሻያ ምክረ ሃሳብ ከእነ ማብራሪያዎቹ አቅርቧል።  ለምክር ቤቱ ሕግና ፍትሕ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ እንዲሁም ለጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ጽ/ቤት ማድረሱንም አስታውቋል።

በሌላ በኩል ረቂቅ ሕጉ ከሰብአዊ መብቶች አንጻር በርካታ ጠንካራ ጐኖች እንዳሉትና እነዚህም፤ የወንጀል ምርመራ ዓላማ እውነትን ማውጣት መሆኑን፣ መካሄድና መጠናቀቅ ያለበትም አስፈላጊ ካልሆነ በስተቀር ተጠርጣሪው ሳይያዝ መሆኑን በግልጽ መደንገጉ፣ በስህተት የተሰጠ ፍርድ እንደገና የሚመረመርበት ሥነ ሥርዓት መደንገጉ የሚሉትን እንደሚጨምር ኮሚሽኑ ገልጿል።

የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ "ረቂቅ ሕጉ በርካታ ጠንካራ ጎኖች ቢኖሩትም በኮሚሽኑ ሪፖርት የተመለከቱትን የማሻሻያ ምክረ ሃሳቦች በማካተት ከዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ግዴታዎች ጋር የተጣጣመ ሕግ ማውጣት የግድ አስፈላጊ ነው" ብለዋል

[ደመቀ ከበደ ፡ አዲስ አበባ]

 

 

 


2 min read

Published

By Demeke Kebede


Share this with family and friends


Follow SBS Amharic

Download our apps

Watch on SBS

SBS World News

Take a global view with Australia's most comprehensive world news service

Watch now