ከኮቪድ - 19 ወረርሽኝ ጋር ተያይዞ የቤት ውስጥ አመፅ በእጥፍ እየናረ ነው

ኮሮናቫይረስ አውስትራሊያ ውስጥ ሰፍኖ ባለበት ወቅት የቤተሰብ አመፅ በመናሩ ግንዛቤ ለማስጨበጥ፣ ለተጠቂዎች አሥፈላጊው እገዛ መኖሩን ልብ ለማሰኘት፣ አመፅ ፈጻሚዎችም ለጥቃት ተግባራቸው ሕግ ብይን እንደሚጥልባቸው ለማሳወቅና ለማስጠንቀቅ በተለያዩ ቋንቋዎች ማኅበረሰቡ ውስጥ እንዲዘልቅ የቪክቶሪያ መንግሥት ዘመቻ እያካሄደ ነው። አንድ ትልቅ የቪክቶሪያ ሆስፒታል ሪፖርት ባደረገው መሠረት በአንድ ወር ውስጥ ብቻ ከቤት ውስጥ አመፅ ጋር በተያያዘ 700 አስቸኳይ የህሙማን ሕክምና እርዳታዎች በፖሊስ ተመዝግበዋል።

Multilingual campaign launches in Victoria to address family violence rise amid COVID-19 crisis

Source: SBS

የቪክቶሪያ የቤት ውስጥ አመፅ ቅድመ መከላከል ሚኒስትር ጋብሪየል ዊልያምስ አዲሱ የ "Respect Each Other" ዘመቻ ተጠቂዎቹና ሁነቱን የተመለከቱ ግለሰቦች የአመፅ እርምጃዎቹን እንዳይሸሽጉ የሚያበረታታ መሆኑን ጠቁመዋል።

ሚኒስትር ዊሊያምስ ከጉዳዩ አሳስቢነት አንጻር መልዕክቱ ባሕላዊና ቋንቋዊ ዝንቅነት ላላቸው የማኅበረሰብ አባላት እንዲደርስ በተለያዩ ቋንቋዎች እንዲሰራጩ እየተደረጉ ያሉትን ጥረቶች ሲገልጡ፤

" በስድስት ቋንቋዎች በሬዲዮ እንዲተላለፍ ይደረጋል። እንዲሁም በ SBS ቴሌቪዥን፣ SBS on Demand እና በፌስቡክ ተተርጉመው ይቀርባሉ። መልዕክቱ በተቻለ መጠን አያሌ የማኅበረሰባት አባላት ዘንድ እንዲደርስ ማድርጉ እጅጉን ጠቃሚ ነው። የቤተሰብ አመፅ ሁሉንም የማኅበረሰባችንን አካላት የሚጎዳ ነው። እንዴት ቢባል፤ የአመፅ ድርጊቱ ማኅበራዊና ምጣኔ ሃብታዊ፣ ባሕላዊ የመደብ ጀርባን የሚለይ አይደለምና። መልዕክቱን በሁሉም ቴሌቪዥን ጣቢያዎች በተለያዩ ቋንቋዎች ማዳረስና እርዳታ ለሚሹ ሁሉ እገዛዎች መኖራቸውን ማሳወቁ በጣሙን አሥፈላጊና ጠቃሚ ነው" ብለዋል።

 ቀደም ሲልም የፌዴራል መንግሥቱ ከወረርሽኙ ጋር በተያያዘ የቤት ውስጥ አመፅን አስመልክቶ ብሔራዊ ግንዛቤ የማስጨበጥ ዘመቻ ጀምሯል። 

ወረርሽኙን ለመከላከል የተጣሉ ገደቦችን ተከትሎ የቤት ውስጥ አመፅ መረጃዎች እያመለከቱ ነው።

የቅርብ አኃዞች እንዳመለከቱት ከኮቪድ - 19 ጋር ተያይዞ የቤት ውስጥ አመፅ የእርዳታ የስልክ ጥሪዎች በ 1800RESPECT የ 20 ፐርሰንት እንዲሁም የኦንላይን እርዳታ ማመልከቻዎች በ 9 ፐርሰንት ጨምረዋል።

የብሔራዊ ፕሮግራም ሥራ አስኪያጅ ሜሎኒ ሺሃን - በርካታ ተጠቂዎች ምሽት ላይ በኦንላይ እርዳታ መጠየቅ መጀመራቸውን ተናግረዋል።

አያይዘውም፤

"ሰዎች ወጥመድ ውስጥ ገብተዋል። የተወሰኑ ሰዎች ቤት ውስጥ ለመቆየት ግድ በመሰኘታቸው የስሜት መታወክ አድሮባቸዋል፤ ሌሎች ተገልለው አመፅን ከሚመርጥ ሰው ጋር መኖራቸው ደህንነታቸው የተጠበቀ አይደለም" በማለት ወረርሽኙን ተከትሎ የቤተሰብ አመፅ የተጠቂዎችን ደኅነት ለሥጋት መዳረጉን አመላክተዋል።  

ጥቃቱ የደረሰባቸው ሰዎችም የሆስፒታሎችን የድንገተኛ አደጋ ዲፓርትመንት በከፍተኛ ቁጥር እያጣበቡ ነው።

የሜልበርን አንዱ ትልቁ ሆስፒታል ሴይንት ቪንሰንትስ ከቤተሰብ አመፅ ጋር በተያይዘ ለሕክምና የመጡ ሕሙማኖች ቁጥር በእጥፍ ያደገ መሆኑን ገልጧል። 

ይህ በእንዲህ አንዳለም ሁለት ሺህ አምስት መቶ ያህል የፖሊስ አባላት ባለፈው ወር ብቻ ከ780 የበለጡ ጥቃት የተፈጸመባቸው ቪክቶሪያውያን ቤቶችን አንኳኩቷል።  

የቪክቶሪያ ዋና ኮሚሽነር ግራሃም አሽተን በወረርሽኙ ሳቢያ ሌሎች ወንጀሎች በመቀነሳቸው የፖሊስ ኃይላቸውን አብዝተው ለቤት ውስጥ አመፅ ክትትል ማሰማራታቸውንና ከ100 በላይ ክሶችን መመስረታቸውን አስታውቀዋል።

ሁነቱም ሰዎች ደህንነታቸው ሊጠበቅበት በሚገባው ቤታቸው ውስጥ ከቶውንም ለአደጋ መጋለጫቸው መሆኑን አመልካች መሆኑ ተነግሯል።

ስለ ኮሮናቫይረስ በቋንቋዎ ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት sbs.com.au/coronavirus ድረ - ገጻችንን ይጎብኙ።

 


Share

2 min read

Published

Updated

By Gareth Boreham

Presented by Kassahun Seboqa Negewo


Share this with family and friends


Follow SBS Amharic

Download our apps
SBS Audio
SBS On Demand

Listen to our podcasts
Independent news and stories connecting you to life in Australia and Amharic-speaking Australians.
Ease into the English language and Australian culture. We make learning English convenient, fun and practical.
Get the latest with our exclusive in-language podcasts on your favourite podcast apps.

Watch on SBS
SBS World News

SBS World News

Take a global view with Australia's most comprehensive world news service