ብዙውን ጊዜ አዲስ ዓመት ሲቃረብ ስለ አዲስ ዓመት ውሳኔዎቻችን አንስተን እንነጋገራለን። እያንዳንዳችን በተስፋ የተመላ፣ በታላላቅ ዕቅዶችና በበጎ ጥረቶች የታጀበ የተሻለ ዓመት እንመኛለን።
ሀገር መናገር ብትችልና ምኞቷ ምን እንደሆነ ብንጠይቃት ምን ትል ይሆን?
እያንዳንዱ ሀገር ለሕዝቡ የተለየ ርዕይ ይኖረዋል። መጨረሻ ላይ ግና ሁሉም የሚመኙት ሰላምን ነው።
በዕለተ ዕንቁጣጣሽ፣ በኢትዮጵያ አዲስ ዓመት፣ እናት ኢትዮጵያን ምኞቷ ምን እንደሆነ ብንጠይቃት፣ መልሷ ተመሳሳይ ይሆናል፤ ሁሉም ልጆቿ በሰላም፣ በአንድነትና በመተሳሰብ ሲኖሩ ማየት።
ምንም እንኳን አንድ ሀገር በቀጥታ መናገር ባትችልም፣ ድምፃዋ በሕዝቧ አማካይነት ይሰማል። ነገር ግን ሕዝብ እርስ በእርሱ ተከፋፍሎ እና በግጭት ውስጥ እያለ እንዴት ለሀገሩ ድምፅ ሊሆን ይችላል?ወ/ት ናዲያ ፔይትሮ ሞናያ
ምናልባትም መልሱ ዛሬ ኢትዮጵያውያን ለማንነታቸው በሚሰጡት ምላሽ ውስጥ ይገኛል።
ቀደም ሲል ኢትዮጵያ ስትነሳ በመጀመሪያ ወደ አዕምሮ የሚመጣው ጥንታዊና አስደናቂ ታሪኳ ነበር። የሰው ልጅ መገኛ ተብላ የተከበረችው ኢትዮጵያ ከጥንት ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ከድንቆች አንዷ ድንቅ ሆና አለች።
አርኪኦሎጂስቶች፣ የታሪክ ምሁራን፣ ተመራማሪዎች እና ቱሪስቶች ጥንታዊ ሀብቶችንና ምስጢራትን ለማግኘት ወደ ኢትዮጵያ መጥተዋል፣ አሁንም እየተመላለሱ ነው።
ከእነዚህም መካከል በአክሱም ጽዮን ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን በጥብቅ በሚጠበቅ ቤተ ፀሎት ውስጥ ተቀምጦ ይገኛል ተብሎ የሚነገርለት የቃል ኪዳኑ ታቦት ይገኝበታል። እሱንም ዕድሜውን ሙሉ አንድ መነኩሴ ብቻ ይጠብቀዋል ተብሎ ይታመናል።
እነዚህ አስደናቂ ታሪኮች በኢትዮጵያ ቅርስ ውስጥ በጥልቅ የተሸመኑ ሲሆን፣ የሀገሪቱን ያለፈ ታሪክ ብቻ ሳይሆን የሰው ልጅን አጠቃላይ ታሪክም ይተርካሉ። ዛሬም ቢሆን ብዙዎቹ እነዚህ ምስጢራት ተመራማሪዎችን እያስደመሙ ናቸው፤ ሙሉ በሙሉ ገና ያልተገለጠ ታሪክ አካል ሆነውም ቀጥለዋል።
ከታሪኳ ጋር በተያያዘ፣ የኢትዮጵያ ታላላቅ ሐውልቶችና ታሪካዊ ቦታዎች፣ አክሱም፣ ላሊበላ እና ሐረር ጀጎልን ጨምሮ ከዩኔስኮ የዓለም ቅርስ ሥፍራዎች መካከል የተመዘገቡ ሲሆኑ፣ የሀገሪቱን ብልፅግናማ ቅርስ፣ ሥልጣኔ እና ታሪካዊ ውርስ የሚወክሉ ምልክቶች ሆነው ቆመዋል።
ከእዚህ ታሪክ ጎን ለጎን፣ የኢትዮጵያ ገዢዎችና መሪዎችም በሀገሪቱ ታሪክ ላይ የማይረሳ አሻራ ትተዋል። ከእነርሱ መካከል ንጉሠ ነገሥት ምኒልክ ተጠቃሽ ናቸው። በአድዋ ጦርነት በወራሪው የጣሊያን ጦር ላይ ያገኙት ድል የኩራትና የፀረ ቅኝ ግዛት ትግል ምልክት አድርጓቸዋል።
የእርሳቸው መሪነት፣ የሠራዊታቸው ጀግንነት፣ እንዲሁም የኢትዮጵያ ሕዝብ ፅናትና አንድነት ለዚህ ታላቅ ድል አስተዋፅኦ አድርገዋል። ይህ ድልም የኢትዮጵያን ስም በአፍሪካ ኩራትነት እንዲጎላ አድርጓል። ተዘውትሮም በቅኝ ግዛት ፈጽሞ ያልወደቀች ብቸኛዋ የአፍሪካ ሀገር ተብላ እንድትገለጽ ምክንያት ሆኗል።
ከታሪኳና ከመሪዎቿ ባሻገር፣ የኢትዮጵያ ማንነት በተፈጥሯዊ ውበቷና ሀብቶቿ ላይ የተመሠረተ ነው፤ እነዚህም ከተፈጥሮ ታላላቅ ስጦታዎች መካከል ይቆጠራሉ።
ከእነዚህም መካከል ግርማ ሞገስ የተላበሱ ተራሮቿ ይገኙበታል። ደጋማ ቦታዎቿ፣ ለም መሬቶቿና ሸለቆዎቿ። ከውሃ ሀብቶቿ፣ እንደ ዓባይ ወንዝና ፏፏቴዎቿ። ከዱር እንስሳቶቿ መካከልም፤ የኢትዮጵያ ብቸኛ ቅርስ፤ የጥንካሬ፣ የፅናት እና የኩራት ምልክቶች የሆኑቱ ጥቁር አንበሳ እና ዋልያን አካትቶ። 830 የአእዋፍ ዝርያዎቿ፤ እንዲሁም ቢራቢሮዎቿና ነፍሳቶቿ ሳይቀሩ።
እነዚህ እና ሌሎች ሥፍር ቁጥር የሌላቸው የሕይወት መገለጫዎችና ቀለማት፣ ከሀገሪቱ ልዩ የአየር ንብረትና የ13 ወራት የፀሐይ ብርሃን ጋር በመሆን፣ ኢትዮጵያን በተፈጥሮ፣ በታሪክ እና በባሕል ልዩ የሚያደርጓት ናቸው።
የኢትዮጵያ ማንነትና ውበት በሕዝቧ ሕይወትና ባሕሎችም ይንጸባረቃሉ። ከ80 በላይ የተለያዩ ቋንቋዎች፣ የተለያዩ ሃይማኖቶች፣ እምነቶች፣ ወጎችና ልማዶች፣ ጥበቦች፣ ዘፈኖች፣ ግጥሞች፣ ተረቶች፣ ምሳሌያዊ አነጋገሮች፣ ባሕላዊ ምግቦችና መጠጦች፣ በእጅ የሚሠሩ አልባሳት፣ መሣሪያዎችና ቅርሶች፣ እንዲሁም ልዩ የመግባቢያና የማኅበረሰብ ኑሮ ዘይቤዎች የእዚህ ብዝሃነት መገለጫዎች ናቸው።
ከባሕላዊ የቡና ሥነ ሥርዓት ጀምሮ እስከ እንግዶችን በአክብሮትና በሞቅ ልብ የመቀበል ልማድ ድረስ፣ ልዩ የእንግዳ መስተንግዷዊ ባሕሎች፣ ባሕላዊ ሙዚቃ፣ ተረትና ትርክቶች። እንዲሁም፤ የጎረቤቶች፣ የወዳጆች እና የሀገር ሽማግሌዎች አተዳደሞች፤ የኢትዮጵያ ማንነት መገለጫዎች ሆነው ቆይተዋል።
ይህ ማንነት በታሪክና በባሕል ብቻ ሳይሆን፣ በሕዝቧ ዕለት ተዕለት ትሁትና ታታሪ ኑሮ፤ እንዲሁም ቤተሰቦችንና ማኅበረሰቦችን በሚያስተሳስሩ የዕለት ተዕለት ትስስሮች የተጋመደ ነው።
ዛሬ ግና የማንነት ትርጉም በእጅጉ ተለውጧል። ከጊዜ ወደ ጊዜም ወደ ዘር፣ ብሔር፣ ቋንቋ እና ሃይማኖት ተኮር አስተሳሰብ ሆኖ እየወየበ መጥቷል።
እነዚህ በእውነቱ የኢትዮጵያን ባለ ብዙ ብሔር፣ ባለ ብዙ ባሕል እና ሕያው ማኅበረሰብ ሀብትና ውበት ሊያንጸባርቁ ሲገባቸው፣ በምትኩ፣ በብሔር ማንነት ላይ የተመሰረቱ መለያየትና ማግለል፣ እንዲሁም ከእዚያም የከፋ የማኅበራዊ ክፍፍል፣ አድልዎ፣ ጭቆና እና ጥቃት እየተስፋፉ መጥተዋል።
በሳቢያውም፤ በማኅበረሰቦች መካከል ለሚፈጠሩ ክፍፍሎችና ግጭቶች አስተዋፅኦ አድርገዋል፤ ሲልም ለብዙ ወገኖች ሕይወት መጥፋት ምክንያት ሆነዋል።
ምናልባትም መተማመንን እንደገና የመገንባቱ ጉዞ የሚጀምረው፣ ኢትዮጵያን በታላላቅ ድሎቿም ሆነ በእጅግ ፈታኝ ወቅቶቿ ያሻገሯትን ዕሴቶች በማስታወስ ይሆናል።
የኢትዮጵያ ታሪክ ለረጅም ጊዜ እንዳሳየው፣ ታላላቅ ስኬቶቿ የተገኙት ሕዝቧ በአንድነት በቆመበት ወቅት ነው። እንዲሁም፤ ሀገርኛ ይትባሃሉ “ድር ቢያብር አንበሳ ያስር” እንዲል፤ እየተባባሰ ባለው ዘመነ ክፍፍል፤ አባባሉ ጠቃሚ መልዕክትን ያስተላልፋል።
የሀገሪቱ የወደፊት ዕድል እና ብልፅግና የተመሠረተው ሕዝቧን በሚያለያዩ ነገሮች ላይ ሳይሆን፣ በሚያስተሳስሯቸው ዕሴቶችና ግንኙነቶች ላይ ስለመሆኑ ግንዛቤ ያስጨብጣል።
ይህ በውጭ ሀገር ከምትኖር አንዲት ኢትዮጵያዊት ዕይታ አኳያ የተፃፈ ትሁት ምልሰታዊ ምልከታ ነው። በቀላሉ ለመጪው ዓመት የቀረበ ከልብ የመነጨ ምኞት ነው።
ኢትዮጵያ ግጭት ባለበት ሥፍራ ሰላምን፣ አለመረጋጋት ባለበት ሁኔታ መረጋጋትን፣ አለመግባባት ባለበት ሥፍራ መግባባትን፣ አለመተማመን ባለበት ሥፍራ መተማመንን፣ ክፍፍል ባለበት ሥፍራ አንድነትን፣ እጥረት ባለበት ሥፍራ ብልፅግናን፣ እና ጥላቻ ባለበት ሥፍራ ፍቅርን እንድታገኝ የሚመኝ ምኞት።ወ/ት ናዲያ ፔይትሮ ሞናያ
አዲስ ዓመት ሲቃረብ፣ አንድ ላይ የመቆምን ኃይል እንደገና እናግኝ። ኢትዮጵያ በብዙ ውብ አበቦችና ዛፎች የምታብብ አንዲት የአትክልት ሥፍራ መሆኗን እናስታውስ። እያንዳንዱ አበባ ሣርና ዛፍ በቀለሙ፣ በቅርጹ፣ በመልኩ፣ በመዓዛው፣ በባሕሪውና በልዩ ጠባዩ ቢለያይም፣ በአንድነት ሲሆኑ በሕይወት የተሞላ ልዩ ውበት ያለውን የአትክልት ሥፍራ ይፈጥራሉና።
እንደ ኢትዮጵያ ሕዝብ፣ ባሕሎች፣ ቋንቋዎችና እምነቶች ሁሉ።
ይህ ብዝሃነት ያለፈ ታሪካችንን ቀርጿል። የአሁኑን ዝንቅ ሕይወታችን አበልፅጓል። መጪውንም ጊዜ ያጠናክራል። ብዝሃነታችን ድክመታችን አይደለም፤ትልቁ ጥንካሬያችን እንጂ። የተባበረች ታላቂቷ ኢትዮጵያም መሠረት ነው።
መልካም አዲስ ዓመት!
ናዲያ . ቫ. ፒዬትሮ ሞናያ እንግሊዝ አገር በሚገኘው የኤክሰተር ዩኒቨርሲቲ (University of Exeter) የሶስተኛ ዲግሪ (PhD) የምርምር ተማሪ ነች።
ፀሐፊዋን በሚከተለው የኢሜይል አድራሻ ማግኘት ይቻላል፤ nadiamonaia@gmail.com

