ለጀግኒት ሴቶች በሙሉ

የሴቶች ቀን በዙሪያችን ያሉትን፣ ሕይወታችንን የቃኙትን እና በየቀኑ በእንክብካቤያቸው፣ በትዕግስታቸው፣ በፍቅራቸው እና በጠንካራ ስራቸው ሕይወታችንን በመቅረጽ ላይ ያሉትን ሴቶች ለአፍታ ቆም ብለን እንድናስብ የሚያስታውሰን ቀን ነው። ሴቶችን በሙያቸው፣ በማዕረጋቸው፣ በሽልማታቸው እና በስራ ስኬታቸው ብቻ በሚያሞግስ ማህበረሰብ ውስጥ፤ ከመጋረጃ ጀርባ በጸጥታ የሚሰሩትን፣ የማይታዩትን፣ የማይሰሙትን፣ የማይከበሩትን፣ ነገር ግን እጅግ አስፈላጊ የሆኑትን ሴቶች መዘንጋት ቀላል ነው።

Nadia 2.png

Nadia V. Pietro Monaia. Credit: Images / NVP Monaia

የቤት እመቤቶች ብዙ ጊዜ ከትዕይንት ጀርባ ብዙ ስራዎችን እየሰሩ፣ ነገር ግን "ስራ አጥ"፣ "እናት ብቻ" ወይም "ሚስት ብቻ" ተብለው ይፈረጃሉ። በእውነቱ ግን ቤተሰብን በትከሻቸው የተሸከሙ፣ በቤት ውስጥ ፍቅር፣ በተስፋ መቁረጥ ውስጥ ተስፋን፣ በድካም ውስጥ ጥንካሬን፣ በህመም ውስጥ ፈውስን፣ በግጭት ውስጥ ሰላምን፣ በጭንቀት ውስጥ ደህንነትን፣ በሀዘን ውስጥ ደስታን የሚያመጡ እና የሚወዷቸውን በምቾት እና በደህንነት የሚጠብቁ እነሱ ናቸው።

አንድን ሕንፃ ወደ ሞቅ ያለ ቤት፣ ጥሬን ወደ ማዕድ፣ ቀንን ወደ ብሩህ ጊዜ፣ ምሽትን ወደ ሰላማዊ ማረፊያ በመቀየር የስምምነት፣ የምቾት እና የአንድነት ሥፍራን ይፈጥራሉ።

ዕንቅልፍ አልባ ምሽቶቻቸው፣ የማይታዩ እንባዎቻቸው፣ የማይሰሙ ጩኸቶቻቸው፣ የእርዳታ ጥሪዎቻቸው፣ ያልተነገሩ ታሪኮቻቸው እና ጸጥ ያሉ ህመሞቻቸው ብዙ ጊዜ ከፈገግታቸው ጀርባ እና በዓይኖቻቸው ጥልቀት ውስጥ እንደ ጠባሳ ተደብቀው ይቀራሉ። በፍቅር የተዘጋጁ ምግቦች፣ በሕመም ጊዜ ሁሉንም ሰው የሚንከባከቡበት መንገድ፣ እና እንደ ወላጅ፣ አስተማሪ፣ አማካሪ، ነርስ፣ ሐኪም፣ ጓደኛ እና ጠባቂ ሆነው የሚያሳልፉት ሕይወት ብዙ ጊዜ የሚገባቸውን ዕውቅና የማያገኙ የፍቅር ሥራዎች ናቸው።

ብቸኛ ሴቶች (ያላገቡ፣ የተፋቱ፣ ባላቸውን ያጡ) በቤት ውስጥም ሆነ ከቤት ውጭ ያሉ ሀላፊነቶችን በማመጣጠን የበለጠ ከባድ ሸክም ይሸከማሉ። የሚሸከሙት ሸክም እጅግ ከባድ ቢሆንም፣ ማኅበረሰቡ ግን ጥንካሬያቸውን ለማድነቅ፣ ጥረታቸውን ለመረዳት እና ፍላጎቶቻቸውን ለማሟላት ጊዜ ወስዶ አያስብም። እንዲሁም የራሳቸው ሕመም እና ትግል እያለባቸው ሌሎችን መንከባከብን የማያቋርጡትን አንዘንጋ።

አካላቸው ቢደክምም አሊያም ቢዝልም ሰጭ ልባቸው አያቆምም።

ሁላችንም ቅድመ አያቶቻችን፣ አያቶቻችን፣ እናቶቻችን፣ ሴት ልጆቻችን፣ እህቶቻችን፣ አክስቶቻችን፣ አስተማሪዎቻችን፣ ጎረቤቶቻችን ወይም ጓደኞቻችን ዛሬ ከጎናችን ላይኖሩ ይችላሉ፤ ነገር ግን እያንዳንዳችን ህይወታችንን በጥልቅ የነካች፣ በልባችን የፍቅር፣ የደግነት፣ የጥንካሬ እና የድፍረት ዘር የዘራች፣ ማንም በማያይበት ጊዜ ያበረታታችን፣ እና በችግራችን ጊዜ ትከሻዋን ያሳረፈች ሴት እናውቃለን።

ዛሬ፣ በሕይወት የሌሉትን፣ ድምፃቸው ፀጥ ያለ ቢሆንም ተፅዕኖአቸው ግን በውስጣችን የሚኖረውን ሴቶችንም እናከብራለን። ትምህርታቸው፣ መስዋዕትነታቸው፣ ጥንካሬያቸው እና ፍቅራቸው በህይወታችን ውስጥ እንደተሸመነ ይኖራል። ጊዜ ሊሰርዘው የማይችለው ነገር ግን ሊያከብረው የሚችለውን አሻራ፣ ፈገግታ፣ ዘፈን፣ ሳቅ፣ ግጥም፣ ታሪክ፣ እሴት እና ጥበብ ትተውልን አልፈዋል።

ሴቶች በጦርነቶች፣ በትግሎች እና በድሎች ውስጥ ከወንዶች ጎን ቆመው ነበር፣ አሁንም ቆመዋል፤ ብዙ ጊዜ ቤተሰብን እና ማኅበረሰብን አንድ አድርጎ የሚይዝ የጀርባ አጥንት እና ደጋፊ በመሆን።

ሚናቸው በአንድ ቃል፣ ማዕረግ ወይም ታሪክ ሊገለጽ አይችልም። ሴት የህይወት መገኛ፣ የእውቀት ምንጭ፣ ትምህርት ቤት፣ እና የቤተሰብ፣ የማህበረሰብ እና የሀገር መሰረት ናት። ተጽእኖዋ ከራሷ አልፎ ይሰፋል፤ እሷ የመጀመሪያዋ ተሸካሚ፣ የመጀመሪያዋ አድማጭ፣ የመጀመሪያዋ አስተማሪ፣ የመጀመሪያዋ አጽናኝ እና የመጀመሪያዋ መሪ ናት።

ባለፉት ዘመናት፣ የሴቶች ጉዳይ በውይይቶች፣ በጦፈ ክርክሮች፣ እና በማህበራዊ፣ ሃይማኖታዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች እምብርት ላይ ቆይቷል። ቀደምት ከነበሩት የመሠረታዊ እውቅና እና የውክልና ትግሎች ጀምሮ እስከ ዓለም አቀፍ የእኩልነት ዘመቻዎች ድረስ። ሴቶች እና ወንዶች ለሴቶች መብት፣ ክብር እና ደህንነት ያለመታከት ታግለዋል።

ድምፃቸው ፍትሃዊ ያልሆኑ ስርዓቶችን ተገዳድሏል፤ ህጎችን ቀይሯል፤ ማኅበረሰቦችንም አሻሽሏል። እድገቶች ታይተዋል፤ ሴቶችን ለመቀበል ብዙ በሮች ተከፍተዋል፤ እድሎች ሰፍተዋል። ባለፉት ትውልዶች በሕልም ብቻ ይታሰቡ የነበሩ አሁን ብዙ የሕግ ማሻሻያዎች ተደርገዋል። እነዚህም በብዙ መንገዶች ሴቶችን ይጠብቃሉ፤ እንዲሁም ያበቃሉ።

ይሁን እንጂ፣ እነዚህ እድገቶች ቢኖሩም፣ ወደ ሙሉ እኩልነት የሚደረገው ጉዞ ገና አላለቀም። ዛሬም በ21ኛው ክፍለ ዘመን፣ ስፍር ቁጥር የሌላቸው ሴቶች ዘረኝነት፣ አድልዎ እና ገደቦች ያጋጥሟቸዋል። ብዙዎች ትምህርት ይነፈጋሉ። በአመራር ቦታ ድምፃቸው ይታፈናል፤ ለእኩል ስራ ዝቅተኛ ክፍያ ይከፈላቸዋል፤ ወይም ሴት በመሆናቸው ብቻ ሕልማቸውን እንዳያሳኩ ይደረጋሉ።

ሌሎች ደግሞ ነፃነታቸውን የሚገድቡ እና አቅማቸውን የሚያዳክሙ ባህላዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ ወይም ፖለቲካዊ መሰናክሎች ያጋጥሟቸዋል። በብዙ የዓለም ክፍሎች ሴቶች አሁንም ደህንነታቸውን እና የወደፊት ህይወታቸውን አደጋ ላይ የሚጥል ጥቃት፣ ብዝበዛ እና ስርአታዊ ኢፍትሃዊነት ያጋጥሟቸዋል።

በየዓመቱ በጣም ብዙ ሴቶች እና ልጃገረዶች በጥቃት፣ በግድያ፣ በማጎሳቆል፣ በአስገድዶ መድፈር፣ በዘረኝነት ወይም ሊጠብቃቸው ባልቻለ ስርዓት ህይወታቸውን ያጣሉ።

እንዲያም ሆኖ፣ ሴቶች ይነሳሉ። በጨለማ እና ፈታኝ ጊዜያት ውስጥ እንኳን፣ ለተሻለ ቀን ተስፋን ይዘው ይጓዛሉ። ይቋቋማሉ፤ ይቆማሉ፤ ይንከባከባሉ፤ እንደገና ይገነባሉ፤ የተሻለ ቀንን ያልማሉ።

ጉብዝናቸው ለውጥ እንደሚቻል፣ እና እያንዳንዷ ሴት ደህንነቷ የተጠበቀ፣ የተከበረች እና ነፃ የሆነችበት ፍትሃዊ፣ ደግ፣ እና ሩህሩህ ዓለም መገንባት እንደሚቻል ማስታወሻ ነው።

በታሪክ ውስጥ፣ ሴቶች ማኅበረሰቦችን በሚታይም ሆነ በማይታይ መንገድ ቀርፀዋል። ለቤተሰብ፣ ለትምህርት፣ ለሳይንስ፣ ለሂሳብ፣ ለሕክምና፣ ለሥነ-ጽሁፍ፣ ለኢኮኖሚክስ እና ለሰው ልጅ እድገት በሁሉም ዘርፍ አስተዋፅኦ አድርገዋል።

ፈዋሾች፣ ተንከባካቢዎች፣ መሪዎች፣ አርቲስቶች፣ አሳቢዎች፣ መምህራን፣ ፈላስፎች፣ ምሁራን፣ ጠባቂዎች እና ማኅበረሰብ ገንቢዎች ነበሩ። ከለውጥ ግንባር ቀደምትነት እስከ መጋረጃ ጀርባ ድረስ ቆመዋል።

በታሪክ ውስጥ ከታወቁት ታላላቅ ጀግኖች መካከል አንዳንዶቹ ዓለም ስማቸውን ላያውቀው የሚችል፣ ነገር ግን ሥራቸው፣ መስዋዕትነታቸው እና ፍቅራቸው ትውልዶችን የቀረፁ እና አሁንም የሚቀርፁ ጸጥተኛ ሴቶች ናቸው።

የሴቶች ብዝሃነት ውበት ከሰው ልጅ ታላላቅ ጥንካሬዎች እና ስጦታዎች አንዱ ነው። ከእያንዳንዱ ዘር፣ ባሕል፣ ቋንቋ፣ እምነት፣ ሃይማኖት እና አስተዳደግ የመጡ ሴቶች ልዩ ጥበብን፣ ወጎችን እና አመለካከቶችን ያመጣሉ።

ኃይለኛ እና ቻይ ፣ ጠንካራ እና ገር፣ ቆራጥ እና ሩህሩህ፣ ኩሩ እና ትሁት፣ ተናጋሪ እና ዝምተኛ በመሆን፣ ሴትነት አንድ አይነት ቅርፅ፣ አንድ ድምጽ ወይም አንድ መንገድ ሳይሆን፣ ዓለምን እንደሚያብብ አትክልት የሚያለመልም፣ እያንዳንዷ ሴት የራሷን ቀለም፣ ጠረን፣ ብርሃን፣ ውበት፣ እና ልዩነት የምትጨምርበት ደማቅ ማህደር መሆኑን ያረጋግጣሉ።

እንደ ማኅበረሰብ፣ የተሻለ መስራት አለብን። ሴቶችን የሚጠብቁ፣ ከፍ የሚያደርጉ፣ ጠንካራ ሥራቸውን እውቅና የሚሰጡ እና የሚደግፉ ሥርዓቶችን መፍጠር አለብን። ክብርን፣ አካታችነትን፣ እና እኩልነትን የሚያረጋግጡ መዋቅሮችን መገንባት አለብን።

ግንዛቤ አስፈላጊ ነው። ለውጥም ከእያንዳንዳችን ይጀምራል።

በራሳችን አነስተኛ መንገዶች፣ ሴቶችን በማክበር፣ ፍትሃዊ እና በደግነት በመያዝ፣ የሚገባቸውን ክብር በመስጠት፣ እንዲሁም በቤታችን፣ በስራ ቦታችን እና በማኅበረሰባችን ውስጥ ያሉትን ሴቶች በመርዳት እና በመደገፍ ልናከብራቸው እንችላለን።

በዚህ የሴቶች ቀን፣ ሁሉንም ሴት እናክብር፤ የሚንከባከቡትን፣ የሚያሳድጉትን፣ የሚማሩትን፣ የሚራመዱትን፣ የሚመሩትን፣ የሚወጡትን፣ የሚያሸንፉትን፣ የሚደሰቱትን እናክብር። ለሚወድቁት፣ ለሚፈውሱት፣ ለሚታገሉት፣ ለቆሰሉት፣ ለሚያለቅሱት፣ ከእኛ ጋር ለሌሉት፣ ተስፋ ለሚያደርጉት፣ እና በጸጥታ ጥንካሬያቸው ዓለምን አንድ አድርገው ለያዙት እንጸልይ።

እናም ሁላቸውም ሴቶች፣ በየትኛውም ቦታ፣ ያለ ፍርሃት፣ በክብር፣ በእኩል እድል፣ በፍቅር እና በተስፋ የሚኖሩበትን የወደፊት ጊዜ ለመፍጠር ራሳችንን እናስገዛ።

ሁላቸውም ሴቶች ክቡር ናቸው!

ናዲያ . ቫ. ፒዬትሮ ሞናያ (Nadia V. Pietro Monaia) ኢትዮጵያዊት-ኤርትራዊት እና ጣሊያናዊት፣ ብዙ ቋንቋዎችን የምትናገር እና የባህል ብዝሃነት ያላት በእንግሊዝ አገር (UK) በሚገኘው የኤክሰተር ዩኒቨርሲቲ (University of Exeter) የፒኤችዲ (PhD) የምርምር ተማሪ ነች። ፀሃፊዋን በሚከተለው የኢሜይል አድራሻ ማግኘት ይቻላል፡ nadiamonaia@gmail.com

 

 


5 min read

Published

Source: SBS



Share this with family and friends


Follow SBS Amharic

Download our apps

Watch on SBS

SBS World News

Take a global view with Australia's most comprehensive world news service

Watch now