የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ(አብን) ጳጉሜ 2 ቀን 2012 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ ከድርጅቱ ምሥረታ ጀምሮ ባለፉት ሁለት ዓመታት ለአማራ ሕዝብ ያበረከታቸውን የትግል አስተዋፅዖዎች በመንቀስ በአማራ ሕዝብ ላይ ተፈጽሟል ያላቸውንም በደሎችና የዘር ጥቃቶች አመላክቷል።
አክሎም "የዘር ፍጅቱን ተከትሎ የኦሮሚያ ክልልም ሆነ የፌዴራሉ መንግስት ወንጀሉን በስሙ በመጥራት ወንጀለኞችን ለሕግ ከማቅረብ ይልቅ ድርጊቱን ተራ ግጭት በማስመል ወደ ማስተባበል ገብተዋል፡፡ ከዘር ፍጅቱ የተረፉ ተጠቂ ወገኖችንም በተገቢው ሁኔታ በማቋቋም ረገድ ዳተኝነት ይስተዋላል" ሲልም ከሷል።
ንቅናቄው ሶስት ዋነኛ ባላቸው ጉዳዮች ላይም ጥብቅ አቋሙን ገልጧል።
1.2. የአብን አቋም፦
በአጠቃላይ አብን በጥናቱ ባረጋገጠው መሰረት በኦሮሚያ ክልል የተደረገው የዘር ማጥፋት ተገቢውን ትኩረት ያለማግኘቱና ችግሩን በአጭር ጊዜም ይሁን በዘለቄታ ለመፍታት የሚታየው ዳተኝነት ፓርቲያችንን ክፉኛ ያሳስበዋል፡፡ ስለሆነም፦
ሀ) የተፈፀመው ወንጀል የዘር ማጥፋት መሆኑ ታምኖበት በስሙ እንዲጠራና ለተፈፀመው ወንጀልም ይፋዊ ይቅርታ እንዲጠየቅ፤
ለ) መንግሥት የተፈፀመውን የዘር ፍጅት የሚያጣራና የሚመረምር ልዩ የምርመራ ኮሚሽንና አቃቤ ሕግ ጽ/ቤት እንዲያቋቁምና ወንጀለኞች የሚዳኙበት ልዩ ችሎት እንዲሰይም፤
ሐ) መንግሥት በንፁሃን ዜጎች ላይ የተፈፀመውን አሰቃቂ ወንጀል የሚዘክር ቋሚ መታሰቢያ እንዲያቆም፤
መ) ችግሩን በዘለቄታ ለመፍታት በክልሉ በሚኖሩ የተለያዩ ማህበረሰቦችና ህዝቦች መካከል የእርቅና የመግባባት ስራዎች እንዲጀመሩ ፤
ሠ) የኦሮሚያ ክልልም በክልሉ ለሚኖሩ ኦሮሞ ያልሆኑ ማህበረሰቦችና ህዝቦች ሰብአዊና ህገ መንግሥታዊ መብቶቻቸው የሚከበሩበት ዋስትና እንዲሰጥ ፤
ረ) መንግሥት የዘር ፍጅቱን በመዘገባቸው ምክንያት ያሰራቸውን የአስራት ሚዲያ ጋዜጠኞች ያለምንም ቅድመሁኔታ በአስቸኳይ እንዲለቅ አብን ይጠይቃል፡፡
2. በአዲስ አበባ የሚፈፀሙ ወንጀሎችና ብክነቶችን በተመለከተ፦
ፓርቲያችን አብን በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና በፌዴራል መንግስቱ በከተማዋ ውስጥ የሚፈፅሙትን ወንጀሎች ፣ ሙስናና ብክነቶች የሚመረምር ቡድን በማቋቋም ሰፊ ጥናት እያካሄደ ይገኛል፡፡ ከዚህ ጥናት የተገኘ መረጃን መሰረት በማድረግ በከተማዋ ከፍተኛ ሕገ-ወጥ የመሬት ወረራ፣ ተቋማትን በአንድ ብሔር ተወላጆች የመሙላት፣ ሕገ-ወጥ የመታወቂያ እደላና በርካታ ተያያዥ ወንጀሎች እንደተፈፀሙ አረጋግጧል፡፡ ይህም በተለይ ከሰኔ 2011 ወዲህ እጅግ የተባባሰ እንደነበር ተገንዝቧል፡፡
2.1. ሕገ-ወጥ ወረራ፣ ሰፈራና ማፈናቀል
የአዲስ አበባ ነዋሪዎች በአንጡራ ሃብታቸው ያቆሙት ጎጇቸውና ድርጅቶቻቸው ያለርህራሄና ያለሕግ አግባብ የሚፈርሱባትና ዜጎች ሜዳ ላይ የሚወረወሩበት፤ ከፊሎች ደግሞ በዘር፣ በፖለቲካ ወገንተኝነትና በጥቅም ትስስር በገፍ መሬት የሚቸራቸው፤ የከተማዋ ነዋሪ ከእለት ጉርሱ ቀንሶ የገነባው የጋራ መኖሪያ ቤት በልዩ መብት የሚታደላቸው ከተማ ሆናለች፡፡
አብን በከተማዋ የሚፈፅሙትን ሕገወጥነቶች ከማውገዝና በተለያዩ መድረኮችና መገናኛ ብዙሃን አማካኝነት ከማጋለጥ ባሻገር አቅም በፈቀደ መጠን የሰብአዊ ርዳታዎችን በማቅረብ ኢትዮጵያውያን ወገኖችን ለመታደግ ጥረት አድርጓል፡፡ መላው ሕዝባችን በተለይም ለህዝብና ለአገር ጥቅሞች ፣ መብቶችና ፍላጎቶች ቆመናል የሚሉ የፖለቲካ ኃይሎች ከንቅናቄያችን አገርን የማዳን ታሪካዊ ጥሪ ጎን እንዲቆሙ ወትውተናል፡፡
ከዚህም ባለፈ ንቅናቄያችን ጉዳዩን ትኩረት ሰጥቶ በማጥናት ለአገሪቱ ከፍተኛ የመንግሥት አካላት በተደጋጋሚ አቤት ብሏል፡፡ ታህሳስ 2 ቀን 2011 ዓ.ም በብሔራዊ ቤተመንግስት በመገኘት ጉዳዩ በቀጥታ ከሚመለከታቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ ጋር እስከመወያየት ደርሷል፡፡ በወቅቱም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ችግሮች መኖራቸውን በማመን አስቸኳይ መፍትሔ እንደሚበጅላቸው ቃል ቢገቡም አንዳችም ሳይደረግ አሁን ካለንበት ሁኔታ ላይ ተደርሷል፡፡
ሰለዚህም አብን ይህ እጅግ አሳሳቢ ጉዳይ በአስቸኳይ መፍትሄ ካላገኘ ፅኑ ብሔራዊ ቀውስ የሚፈጥር በመሆኑ፦
ሀ) አዲስ አበባ ላይ የተፈፀመውን ሁሉንአቀፍ ወረራ በተመለከተ የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ጨምሮ ሌሎች የሚመለከታቸውን ባለድርሻ አካላት ያካተተ አንድ አጣሪ ኮሚቴ እንዲቋቋም፤
ለ) ባለፉት ሁለት ዓመታት የነበረውን የመሬት አስተዳደርና ማስተላለፍ፣ የመታወቂያ አወጣጥ፣ የቅጥርና ዝውውር እንዲሁም ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን እንዲያጣራ/ኦዲት እንዲደረግ፤
ሐ) በኦዲት ግኝቱ በሚመጣው መሰረት ጥፋተኛ ሆነው የሚገኙ ሁሉም አካላት ለፍትኅ እንዲቀርቡ፤
መ) በኦዲት ግኝቱ ለተለዩ ጉድለቶች አጣሪ ኮሚቴው በሚያቀርበው ምክረ ሐሳብ መሰረት የማስተካከያ የእርምት እርምጃ እንዲወሰድ፤ እንዲሁም
ሠ) ምርጫ ተካሂዶ ቅቡልነት ያለው ሕጋዊ የከተማ አስተዳደር ምክርቤትና ካቢኔ እስኪዋቀር ድረስ አሁን ያለው የሽግግር አስተዳደር ዘላቂ ውጤት ሊኖራቸው ከሚችሉ ውሳኔዎች እንዲታቀብ፤ አብን ጥሪውን ያቀርባል፡፡
2.2. ሜጋ ፕሮጀክቶችን በተመለከተ፦
ፓርቲያችን የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ በጠቅላይ ሚኒስቴር ፅ/ቤትና በከተማ አስተዳደሩም በኩል የሚሰሩ ዋና ዋና 15 ሜጋ ፕሮጀክቶችን ሁኔታ በንቃት በመከታተል ስለፕሮጀክቶቹ ዝርዝር መረጃዎችን ሲያሰባስብ ቆይቷል፡፡
በዚህም መሰረት በጀታቸው/ወጪያቸው የታወቁ ፕሮጀክቶች የገንዘብ መጠን በአጠቃላይ 5.737 ቢሊዮን ዶላር (ወቅታዊ ምንዛሪው ከ212 ቢሊዮን ብር በላይ) እና ተጨማሪ 59.2 ቢሊዮን ብር በአንድ ላይ ወደ 271 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ እንደሆነ ተረድቷል፡፡ በጀታቸው ካልታወቁ ጋር ሲደመር ከዚህ ከፍተኛ መሆኑ አያጠራጥርም፡፡
አዲስ አበባ ተመራጭ የቱሪዝም መዳረሻ ከተማ እንድትሆን የሚደረገውን መንግስታዊ እንቅስቃሴ በመርኅ ደረጃ አብን ይደግፋል፡፡
ይሁንና የሜጋ ፕሮጀክቶቹ እጅግ የተጋነነ ወጭ የሚወጡባቸው በመሆናቸው (White Elephant Projects)፤ ይኸው ከፍተኛ በጀት አገራችን በብድርና እርዳታ የምታገኘው በመሆኑ፤ አንዳንዶቹ ፕሮጀክቶች አገራችን አሁን ካለችበት ሁኔታ አንፃር የቅደም ተከተል ችግር ያለባቸው መሆናቸው ፤ ከአዋጭነት፣ ባለድርሻዎችን ከማሳተፍ፣ ከዲዛይንና ግንባታ አካሄድ፣ ከብክነትና ሙስናን ከማስቀረት፣ በግልጽ ጨረታ የግንባታ ኮንትራክተሮችን ከመለየት እንዲሁም በየጊዜው ስለፕሮጀክቶቹ ለሕዝብ ግልጽ መረጃ ከመስጠት አንፃር ክፍተቶች ያሉባቸው መሆናቸውን አብን ያምናል፡፡
መንግስት ይህን ያህል ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ግልጽነት ባልተሞላበትና የቅድሚያ ቅድሚያ የሚሰጣቸውን አንገብጋቢ ጉዳዮች ባላስቀመጠ መልኩ ማዋሉ ፓርቲያችንን ክፉኛ ያሳስበዋል፡፡ ስለሆነም፦
ሀ) መንግስት ስለፕሮጀክቶቹ ለህዝብ ግልፅ ማብራሪያ እንዲሰጥ፤
ለ) በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት የአገራችን ኢኮኖሚ ክፉኛ እየተደቆሰ በመሆኑ ቀውሱ አገርን ለከፋ አደጋ የሚዳርግ ማኅበራዊ ቀውስ ከማደጉ በፊት አስፈላጊ የኢኮኖሚ ድጋፍ ማእቀፎችን ቀርፆ ወደ ሥራ እንዲገባ፤
ሐ) የተጋነኑና አንገብጋቢ ያልሆኑ ሜጋ ፕሮጀክቶችን በማጠፍ በጀቱን የነፍስ አድን ርዳታ ለሚፈልጉ ወደ 18 ሚሊዮን ዜጎች ድጋፍ እንዲያውለው፤
መ) በአገራችን ያለው የሥራ አጥነት በአስከፊ ሁኔታ ላይ መገኘቱን በማጤን መንግስት ጊዜውንና አቅሙን ለወጣቶች ሥራ እድል ፈጠራና ለኢኮኖሚ ሽግግር እንዲያውል አብን ጥሪውን ያቀርባል፡፡
3. ብሔራዊ ውይይትና መግባባትን በተመለከተ፦
አብን የአገራችን የፖለቲካ ቀውስ በምርጫ ብቻ እልባት ያገኛል የሚል አቋም የለውም፡፡ ስለዚህም ከምርጫ በፊት እንደ አገር መደማመጥ፣ መከባበርና መተማመን እንዲቻልና አሁን የተፈጠረው የሽግግር ጊዜም እንዳለፉት ዘመናት እድሎች እንዳይከሽፍ ሁሉን አቀፍ አገራዊ የሰለጠነ ውይይት፣ ምክክርና ድርድር እንዲዘጋጅ፤ ለዚህም ግልጽ ማእቀፍ እንዲኖርና ሁሉንም ባለድርሻ አካላት ያሳተፈ የብሔራዊ ውይይት መድረክ እንዲከፈት ወትውቷል፡፡
መንግሥት ለእውነተኛ የፖለቲካ ድርድርና ብሄራዊ መግባባት ዳተኝነት በማሳየቱ ምክንያት ፅንፈኛ ኃይሎች አገር አፍራሽ ድርጊታቸውን በማናለብኝነት እንዲቀጥሉ እድል ሰጥቷቸዋል፡፡ በዚህ ረገድ ትሕነግ የሚዘጋጅበት ሕገ-ወጥ ምርጫ በወረራ በተያዙ የአማራ መሬቶች በወልቃይት፣ ጠገዴ፣ ጠለምትና ራያ የሚኖረው ህዝባችን ላይ የሚያደርሰውን ፅኑ አፈናና ግፍ መንግሥት እንዲያስቆም በተደጋጋሚ ጥሪ አቅርበናል፡፡
የፌዴሬሽን ም/ቤት ዘግይቶም ቢሆን የወሰነውን ውሳኔ የፌዴራል መንግሥቱ በአስቸኳይ ተግባራዊ እንዲያደርግና ትህነግ በህገወጥ ምርጫ በወልቃይትና ራያ ህዝባችን ላይ የሚያደርሰውን ሰብአዊ ቀውስ እንዲያስቆም አብን ጥሪ ያቀርባል፡፡
በተጨማሪም ፡-
ሀ) አገርን ወደ ዴሞክራሲ ለማሻገር ሁሉም ባለድርሻ አካላት የማይተካ ሚና እንዳላቸው በማመን መላው የፖለቲካ ኃይሎች የአገራችን አደገኛ ወቅታዊ ሁኔታ ባጤነ መልኩ በኃላፊነት እንዲንቀሳቀሱ፤
ለ) መንግስት በውል የታወቀና የታቀደ ሁሉንአቀፍ ብሔራዊ ውይይት፣ ምክክርና ድርድር የማስተባበርና የማመቻቸት ኃላፊነቱን እንዲወጣ፤
ሐ) ሁሉም ዜጎች በተለይም ሲቪክ አደረጃጀቶች፣ የሚዲያ ተቋማት፣ ምኁራን፣ የኃይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ ታዋቂ ግለሰቦች፣ ወጣቶችና ሴቶች እንዲሁም ባለኃብቶች ለሚደረገው ብሔራዊ ውይይት፣ ምክክርና ድርድር ውጤታማነት የየድርሻቸውን አስተዋፅኦ እንዲኖራቸው፤
መ) የዓለምአቀፍ ማኅበረሰቡ የሁሉንአቀፍ ብሔራዊ ውይይት፣ ምክክርና ድርድር ሂደት እንዲደግፍና መንግስት የሚጠበቅበትን ኃላፊነት እንዲወጣም ጫና እንዲፈጥር የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ(አብን) ታሪካዊ ጥሪውን ያስተላልፋል፡፡
‹‹አንድ አማራ ለሁሉም አማራ ፤ ሁሉም አማራ ለአንድ አማራ!››
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ(አብን)፤
አዲስ አበባ፣ ሸዋ፤ ኢትዮጵያ!
ጳጉሜ 2 ቀን 2012 ዓ.ም