ኖቫክ ጆኮቪች የፍርድ ቤት ውዝግቡን አሸንፎ ከኢሚግሬሽን ማቆያ ወጣ።
የፌደራል ሰርኪዩት ኮርት የተሰረዘውን የኖቫክ ጆኮቪች ቪዛ ውሳኔ እንዲቀለበስ በመወሰኑ ማምሻውን ከኢሚግሬሽን ማቆያ ወጥቷል።ነገር ግን በተያያዥ ቪዛው ሊሰረዝበት እና ለመጪው ሶስት አመታት ወደ አውስትራሊያ እንዳይገባ ሊከለከል እንደሚችል ተገምቷል ።
በወንዶች ቴኒስ ቁጥር አንድ ደረጃ ላይ የሚገኘው እና የኮቪድ - 19 ክትባትን ያልተከተበው ጆኮቪች ባለፈው ሀሙስ ቪዛው እንዲሰረዝ የተደረገው በፌደራል መንግስት ውሳኔ ሲሆን፤ ምክንያቱም “ ወደ አገሪቱ ሲገባ ሊያሟላ የሚገባውን ትክክለኛ መረጃዎችን አላሟላም ” በሚል ሰበብ ነበር ።
ጉዳዩ በፍርድ ቤት እስኪታይ ድረስም በኢሚግሬሽን ማቆያ ስፍራ እንዲቀመጥ ተደርጓል።
በጆኮቪች ጠበቃ እና በሆም አፌርስ ሚኒስትር ካረን አንድሪውስ ፤ ዳኛው አንተኒ ኬሊ መካከል በተደረሰው ስምምነት መሰረትም ፤ ሰኞ ከቀትር በኋላ የተሰረዘው የቪዛ ውሳኔ እንዲቀለበስ እና በአስቸኳይ ነጻ እንዲሆን ውሳኔ ተላልፏል።
የሰኞ የፍርድ ቤት ስሚው እስኪደርስ በታገተበት የኢሚግሬሽን ማገቻ ቆይታው ከፍተኛ የሆነ አለማቀፋዊ ሽፋንን እና ውዝግቦችንም ፈጥሮም ነበር። በመንግስት በኩል ያሉት ጠበቆችም ባለፈው ሀሙስ ጠዋት የቪዛውን መሰረዝ አስመልከቶ ምላሽ እንዲሰጥ በቂ የሆነ ጊዜ እንዳልተሰጠው አምነዋል ።
ነገር ግን መንግስትን ወክለው የሚከራከሩት ጠበቃ ክርስቶፈር ትራን ለፍርድ ቤት እንዳስረዱት የኢሚግሬሽን ሚኒስትሩ አሌክስ ሆክ ፤ የሚኒስትሩን ጣልቃ የመግባት መብት በመጠቀም እንደገና ቪዛውን የመሰረዝ መብታቸውን አሁን ለመጠቀም ማሰብ ይችላሉ ብለዋል ።
ዳኛው ኬሊ በበኩላቸው ሚኒስትሩ ያላቸውን መብት ተጠቅመው ቪዛውን ከሰርዙት የ 34 አመቱ ሰርቢያዊ የቲኒስ ተጫዋች ለመጪዎችት ሶስት አመታት አውስትራሊያ እንዳይገባ ይታገዳል ብለዋል።
የአውስትራሊያ የድንበር ህግ ሁለቱን ክትባቶች ያልተከተቡ የውጭ አገር ሰዎች እንዳይገቡ የሚከለክል ሲሆን ፤ ነገር ግን ይህን ለማለፍም ካስፈለገ የህክምና ማስረጃ ማቅረብ የግድ ይላል።
ጆኮቪች ከሃኪሞች እና ፤ ከተለያዩ ባለስልጣናት ፤ ከቪክቶርያ ተወካዮች እና ቴኒስ አውስትራሊም ጭምር ወደ አውስትራሊያ እንዲጓዝ ፈቃድን ያገኘ ሲሆን ከዚህ በላይ ምን ያድርግ ሲሉ ዳኛው ኬሊ ተናግረዋል ።

መንግስትን ወክለው የሚከራከሩ ጠበቃዎች በበኩላቸው የጆኮቪች አለመከተብ በአውስትራሊያ ህዝብ ጤና እና ደህነነት ላይ አደጋ ይጥላል ሲሉ የመከራከሪያ ሃሳባቸውን አቅርበዋል ።

ቁጥራቸው በርካታ የሆነ ደጋፊዎቹም ታግቶ በቆየበት ፓርክ ሆቴል ተቃውሟቸውን ሱያሰሙ ቆይተዋል ።
የጆኮቪች ነጻነት ማለት በቅርቡ የሚጀመረውን የአውስትራሊያ ኦፕንን ዘውድ ለመጫን እና ግራንድ ስላምን ለ21ኛ ጊዜ ለማሸነፍ እጅግ የቀረበ እንደሆነ ማረጋገጫ ነው ተብሎለታል።

