አውስትራሊያ ውስጥ ከፍተኛ አዲስ ሬከርድ በሆነ ሁኔታ ኒው ሳውዝ ዌይልስ ውስጥ 5,715 ሰዎች በአንድ ቀን በኮቪድ-19 ተይዘዋል።
የኒው ሳውዝ ዌይልስ መንግሥት የቤት ውስጥ ፈጣን የኮሮናቫይረስ መመርመሪያ በነፃ ለነዋሪዎች በየመኖሪያ አድራሻቸው ለመላክ፣ በችርቻሮና የመስተንግዶ ግልጋሎት መስጫ ሥፍራዎች የQR check-ins መልሶ ግብር ላይ ለማዋል ወጥኗል።
ይሁንና ፕሪሚየር ዶሜኒክ ፔሮቴይ ከመኖሪያ ቤት ውጪ ባሉ ቤቶች ውስጥ ነዋሪዎች የፊት ጭምብል እንዲያጠልቁ ለመደንገግ እስካሁን ድረስ ፈቃደኛ ሆነው አልተገኙም።
ለሆስፒታል የተዳረጉ ሰዎች ቁጥር 347 ሲደርስ 45 ሰዎች በፅኑዕ ሕሙማን ክፍሎች ይገኛሉ።
ይህ በእንዲህ እንዳለም ቪክቶሪያ 2,005 ነዋሪዎቿ በኮቪድ-19 መጠቃታቸውንና 10 ለሕልፈተ ሕይወት መዳረጋቸውን ዛሬ አስታውቃለች።
ቪክቶሪያ በኮቪድ 19 ሳቢያ ለሆስፒል የሚዳረጉ ሰዎችን ቁጥር ለመቀነስና የቫይረስ ተዛማችነትን ለመከላከል ከዛሬ 11:59 pm ጀምሮ ከመኖሪያ ቤት ውጭ ባሉ ቤቶች ውስጥ ዕድሜያቸው 8 እና ከዚያ በላይ በሆኑ ሁሉ የፊት ጭምብሎችን ማጥለቅ ግዴታ መሆኑን ደንግጋለች።
እንዲሁም በፅኑዕ ሕሙማን ክፍሎች ሕሙማን ክፍሎችና 39 በአየር መተንፈሻ መሳሪያዎች እየታፈዙ ያሉትን አክትቶ 398 ሆስፒታል ውስጥ ይገኛሉ።
ኩዊንስላንድ በበኩሏ 369 ነዋሪዎቿ በቫይረስ መጠቃታቸውንና አንድ ሰው ለሆስፒታል መዳረጋቸውን አስመዝግባለች።
ሰቆጣ
የዋግ ኅምራ ዞን ዋና ከተማ ሰቆጣ በትናንትናው ዕለት ከሕወሓት ተዋጊዎች እጅ ወጥታ በመንግሥት እጅ መዋሏን የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ።
የኮሙዩኒኬሽን አግለግሎቱ የመንግሥትና አጋር የፀጥታ ኃይሎች በቆቦ ግንባር ወደ አላማጣ፤ በሌላም በኩል ወደ መረዋና ኮረም እያመሩ መሆኑን አክሎ ገልጧል።
በሕወሓት በኩል አካባቢዎቹን በስም ባይጠቅስም በሶስት አካባቢዎች የመንግሥት ሠራዊትና አጋር የፀጥታ ኃይሎች ጥቃት መፈጸማቸውን በቃል አቀባዩ በኩል አስታውቋል።
የቴኒስ ቲኬቶች
የአውስትራሊያ ቴኒስ ኦፕን አዘጋጆች የመግቢያ ቲኬት ዋጋዎችን በ50 ፐርሰንት መቀነሳቸውን አስታወቁ።
በዚህም መሠረት በሮድ ላቨር አሬና በሚካሔደው የወንዶችና ሴቶች ፍፃሜ ግጥሚያዎች መግቢያ ቲኬት 148 ዶላርስ ብቻ ይሆናል።
ቶርናመንት ዳይሬክተር ክሬይግ ታይሊ ለ 3-A-W እንደገለጡት ኮቪድ በርትቶ ባለበት ወቅት ቲኬቶች በጣም ጥሩ በሆነ ሁኔታ እየተሸጡ እንደሆነ ተናግረዋል።

