በነገው ዕለት እሑድ ፌብሪዋሪ 7 2001 የበላይነህ ክንዴ ኮርፖሬት ፊቤላ የዘይት ፋብሪካውን እንደሚያስመርቅ ባለ ንብረቱ አቶ በላይነህ ክንዴ ቡሬ በሚገኘው የዘይት ፋብሪካ ለተገኙ ጋዜጠኞች ገለጡ።
አቶ በላይነህ ስለራሳቸው አንስተው ሲናገሩ "የቀድሞ የኢትዮጵያ ሰራዊት ሲበተን እኔም አንዱ ነበርኩ። የዛሬ 29 ዓመት በቀን አራት ብር የቀን ስራ ሰርቻለሁ። በ29 ብር ለኮከብ ዱቄት ፋብሪካም ተቀጥሬ ሰርቻለሁ። ነገ ከ4.5 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ ያደረኩበትን ፊቤላ የምግብ ዘይት ፋብሪካ አስመርቃለሁ" ብለዋል።
በእገው ዕለት የሚመረቀው ፊቤላ ስር የሚገኙ ፋብሪካዎች:-
1. በቀን 1500 ቶን ያህል የምግብ ዘይት ማጣራት እና መሙላት የሚችል የዘይት ፋብሪካ
• በአማራ ክልል በቡሬ ከተማ ይገኛል።
• ግንባታው በ2006 ዓም ተጀመረ።
• ግንባታው 30 ሄክታር ላይ አርፏል።
• 4.5 ቢሊዮን ብር ወጭ ተደርጎበታል።
• ፋብሪካው በቀን እስከ 1500 ቶን የምግብ ዘይት ያመርታል።
• የሐገሪቱን እስከ 60 በመቶ የ ዘይት ድርሻ ይሸፍናል።
• ለምግብ ዘይት ይወጣ የነበረውን የሐገሪቱን 30 በመቶ የውጭ ምንዛሬ ያስቀራል።
• በሙሉ አቅሙ ማምረት ሲጀምር ለ 3,000 ዜጎች የስራ ዕድል ይፈጥራል።
• እያንዳንዳቸው 45 ቶን ያህል የመጫን አቅም ያላቸው 160 የዘይት ድፍድፍ የሚያጓጉዙ ተሽከርካሪዎች አሉት።
2. በቀን 200 ቶን ያህል በተለያየ ደረጃ ላይ ያለ የሰሊጥ ምርት ማቀነባበር የሚችል ፋብሪካ
• ጥሬ ሰሊጥ ላይ እሴት በመጨመር ወደ ውጭ ይልካል።
3. በቀን 96 ቶን ያህል ማምረት የሚችል የሳሙና ፋብሪካ
• ደረቅ ሳሙና፣ፈሳሽ ሳሙናና ዲተርጀንት ያመርታል።
4. የአትክልት ቅቤ እና የማርጋሪን ማምረቻ ፋብሪካ
5. የተለያዩ መጠን ያላቸው በቀን ከ10 ሺህ በላይ የጀሪካን እና ፕላስቲክ ጠርሙሶች ማምረቻ ፋብሪካ
6. የካርቶን ፋብሪካ

በላይነህ ክንዴ ኮርፖሬት ከበላይነህ ክንዴ ግሩፕ ውስጥ አንዱ ሲሆን፤ በኢትዮጵያ ካሉ ጠንካራ የንግድ ኮርፖሬቶች ውስጥ አንዱ ነው።
ወደ ንግድ ሥራ የተሠማራው በ1984 ነው። በወቅቱም መነሻ ካፒታሉ አንድ ሰውና 4600 ብር ነበር።
በአሁኑ ወቅት ኮርፖሬቱ፤ በትራንስፖርት፣ በግንባታ፣ በሆቴልና ቱሪዝም፣ በአምራች ዘርፍ (Manufacturing)፣ በእርሻ እና በወጪና ገቢ ንግድ (Import and Export) ተሰማርቷል።
ኮርፖሬቱ ባሉት ድርጅቶቹ ውስጥ ከ3,000 በላይ ሰራተኞችን እያስተዳደረ ነው።
በገላን ከተማ ያስገነባው የከባድ መኪና መገጣጠሚያ ለደረቅና ፈሳሽ ማመመላሽ የሚሆኑ ከባድ መኪኖችን፣ ቅንጡ የትራንስፖርት አውቶቡሶችን፣ ቅንጡ የቤት መኪኖችን ይገጣጥማል።ለዘይት ፋብሪካው የሚሆኑ 160 ቦቴ መኪኖች በዚሁ ፋብሪካ የተገጣጠሙ ናቸው።
ላለፉት 11 ዓመታት የግብርና ኤክስፖርት ዘርፍ ቀዳሚ፣ እንዲሁም በፎርብስ የ2017 ቀዳሚ የኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሬ የሚያስገኝ ሆኖ የተመሰከረለት ነው።
የኢትዮጵያ ምርት ገበያ የተከታታይ አስር አመት ግንባር ቀደም ደንበኛ ሆኖ እውቅናን አግኝቷል።
ለታላቁ ህዳሴ ግድብ እስካሁን ከ33 ሚሊዮን ብር በላይ የቦንድ ግዥ ፈፅሟል።
ለገበታ ለሀገርና ገበታ ለሸገር 35 ሚሊዮን ብር አስተዋፅኦ ያበረከተ ሲሆን፤ የሀገሪቱን ስፖርት ለማጠናከር እስካሁን ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ አድርጓል።
በመላው ኢትዮጵያ በሰው ሰራሽና በተፈጥሮ አደጋዎች ጉዳት ላጋጠማቸውና ለተፈናቀሉ ወገኖች ላለፉት አምስት ዓመታት ከ200 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የዓይነትና የፋይናንስ ድጋፍ አድርጓል።
የጤናውን ዘርፍ ለመደገፍም እስካሁን ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ሲያደርግ፤ በሰከላ ወረዳ የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ማሰልጠኛ ተቋም ገንብቶ ለህዝብ አስረክቧል።

