"የመከላከያ ሠራዊታችን፣ የፌደራል ፖሊስና የብሔራዊ መረጃና ደኀንነት አካላት ሕገ-መንግስታዊ ተልዕኳችሁን እንድትወጡ በድጋሚ እናሳስባለን" - የአማራ ክልል ብልፅግና ፓርቲ

*** "ጭካኔ በተሞላበት መንገድ በአንድ ስፍራ ህይወታቸው እንዲያልፍ ባደረገው የኦነግ ሸኔ ቡድን ላይ እርምጃ እንወስዳለን" - የኦሮሚያ ክልል መንግሥት

Statment

Source: PP and ORS

በምዕራብ ወለጋ ሰላማዊ ዜጎች ላይ የደረሰውን ግድያ አስመልክቶ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥትና የአማራ ክልል ብልፅግና ጽሕፈት ቤት በየፊናቸው መግለጫዎችን አውጥተዋል።

የኦሮሚያ ክልል መንግሥት ባወጣው መግለጫ ግድያው የተፈጸመበት ሥፍራና ሕይወታቸው ያለፈውን ሰዎች ቁትርና ማንነት ሳይገልጥ "ጭካኔ በተሞላበት መንገድ በአንድ ስፍራ ህይወታቸው እንዲያልፍ ባደረገው የኦነግ ሸኔ ቡድን ላይ እርምጃ" እወስዳለሁ ብሏል። 

አክሎም "የኦነግ ሸኔ ሽፍታ ከሕወሓት ጋር በመሻረክ በኦሮሚያ ክልል እና በሀገሪቱ ሰላም እና መረጋጋት እንዳይኖር ሲሰሩ መቆየታቸውን ያስታወሰው መግለጫው፤ በተለያዩ ወቅቶች የግጭት አጀንዳዎችን በማዘጋጀት በሚዲያ በማሰራጨት እንዲሁም በህገ ወጥ መንገድ በገቡ የጦር መሳሪያዎች በፀጥታ ሀይሎች፣ በመንግስት መዋቅር እና በተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ላይ የግድያ እርምጃ በመውሰድ ችግሮችን ሲፈጥሩ ቆይተዋል"

"በተለይም በምዕራብ ኦሮሚያ አቅጣጫ በሚገኙ ዞኖች ህፃናት፣ ሴቶች፣ አዛውንቶች እና ወጣቶችን ጨምሮ ጭካኔ በተሞላበት መንገድ እንዲገደሉ፣ በእሳት እንዲቃጠሉ፣ የአካል ጉዳት እንዲደርስባቸው እንዲሁም የስነ ልቦና ጉዳት እንዲደርስባቸው ማድረጉ ይታወቃል"

"በተፈፀመው ጥቃት ለተሰው ወገኖች የተሰማውን ሀዘን የገለፀው የክልሉ መንግስት ለቤተሰቦቻቸው መጽናናትን" እንደሚመኝ ገልጧል።

በሌላም በኩል የአማራ ክልል ብልፅግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ባወጣው መግለጫ፤

"በትላንትናው ምሽት በምዕራብ ወለጋ ዞን ጉሊሶ ወረዳ ዘርን መሠረት ያደረገ የአማራን የቡድን ጥቃት መፈፀሙን አረጋግጠናል። የጥቃቱን መጠንና ዝርዝር ሁኔታዎች ከፌዴራሉና ከክልሉ መንግሥት ጋር በመተባበር እያጣራን ሲሆን፤ በዚህ ጭካኔ በተሞላበት ድርጊት የአማራ ህዝብና ድርጅታችን የአማራ ብልጽግና ፓርቲ ክፉኛ አዝኗል፤ ተቆጥቷል፡፡ በመሆኑም ይህ ድርጊት የሚወገዝ ከመሆኑም በላይ አጥፊዎቹ እንደየስራቸው በህግ አግባብ ሊዳኙ ይገባል ብለን እናምናለን፡፡ ስለሆነም ከዚህ በታች የሚከተሉት አካለት ሕገ መንግስታዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ እናሳስባለን" በማለት ባለ አምስት ነጥብ አቋሞቹን አስታውቋል።

 1) የፌደራሉ መንግሥት በአማራ ህዝብ ላይ በየአካባቢው እየደረሰ ያለውን ተደጋገሚ ዘር ለይቶ የማጥቃት ወንጀል ዋነኛ የብሔራዊ ደኀንነት አደጋ አድርጎ ሊወስደው ይገባል። ስለሆነም የኢፌዴሪ ብሔራዊ የደኀንነት ምክር ቤት የአደጋውን መጠንና ቀጠናዊ መዘዝ በማጤን ዘርን መሠረት ያደረገው የአማራ ጥቃት በአስቸኳይ እንዲያስቆም፤ ስለ ጥቃቱም ዝርዝር መረጃ ለመላ ኢትዮጵያዊያን እንዲሰጥ፤ በአማራው ጥቃት ላይ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የተሳተፉ የጥፋት ኃይሎች ላይ ሕጋዊና ተመጣጣኝ እርምጃ እንዲወሰድ በጥብቅ እንጠይቃለን፤

2) የአማራ ህዝብ የሚኖርባችው ክልሎች በተለይም በኦሮሚያ፣ ቤንሻንጉልና በደቡብ ብሔሮች፣ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥታት የምትገኙ የፖለቲካ አመራሮችና የጸጥታ አካላት፣ እናንተንና የአካባቢውን ወንድም ህዝብ አምነው አገር አለን ብለው፤ ሕግና ሥርዓት አለ በሚል ኢትዮጵያዊ መተማመን ከናንተው ጋር ለዘመናት የኖሩትን የአማራ ተወላጆች ከመቸውም ጊዜ በላይ ጥበቃ እንድታደርጉላቸውና ሕዝባዊ ኃላፊነታችሁን እንድትወጡ እንጠይቃለን፤

3) በአማራ ህዝብ ላይ እየደረሰ ያለውን ተከታታይ ጥቃት ከምንጩ ለማድረቅ፤ የችግሩ ዋነኛ መንስኤ አማራን በየ አቅጣጫው በመውጋት በንጹሃን ደም የፖለቲካ ቁማር የሚሰራው የመቀሌው ግዞተኛ የትህነግ ቡድን በመሆኑ፣ ይህ ኃይል የብሔራዊ ደኀንነታችን የስጋት ምንጭ ከመሆን አልፎ የሽብርና የቀውስ ማዕከል ስለሆነ ለኢትዮጵያና ለቀጠናው ዘላቂ ሰላም ሲባል ከመለሳለስና ከመሸከም ፖለቲካ ወጥቶ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ስርአት እንዲያስይዝ ለማድረግ ጊዜው አሁን ስለመሆኑ እናስረግጣለን፤

4) የኢትዮጵያ ዘብ የመሆን ሕገ-መንግሥታዊ ተልዕኮ ያለባችሁ የመከላከያ ሠራዊታችን፣ የፌደራል ፖሊስ እና የብሔራዊ መረጃና ደኀንነት አካላት የአማራ ህዝብና ሌሎች ብሔሮች በማንነታቸው ጥቃት እንዳይደርስባቸው ስትከፍሉት የቆያችሁትን መስዋዕትነት መቼም አንዘነጋውም። ዛሬም ከሀገራዊ ለውጡ በተቃራኒ የቆሙ ጸረ-ሕዝብ የሆኑ ኃይሎች አማራውን ዘሩን መሰረት አድርገው ጥቃት እየተፈጸሙበት መሆኑን አውቃችሁ፤ በየአካበቢው ለሚኖረው አማራ ተገቢውን ጥበቃና ድጋፍ በመስጠት፤ ሕገ-መንግስታዊ ተልዕኳችሁን እንድትወጡ በድጋሚ እናሳስባለን፤

5) የአማራ ህዝብ፣ ምሁራን፣ የማህበረሰብ አንቂዎችና የፖለቲካ ኃይሎች በሙሉ፦  በህዝባችን ላይ እየደረሰ ያለው ጥቃት የረዥም ጊዜ የተዛባ ትርክት ውጤት መሆኑን በመገንዘብ፤ ችግሩን በዘለቄታ ለመፍታት፣ ለሦስት አስርታት የገጠመንን መዋቅራዊ ማነቆ ለመቅረፍ በሚመጥን ልክ የመፍትሄ ሃሳብ በማመንጨት የበኩላችሁን እንድትወጡና በጋራ በመቆም የአማራ ህዝብ ከተደቀነበት የህልውና ስጋት እንድታደገው 'የአማራ አንገቱ አንድ ነው' በሚል ወገናዊ ጥሪያችን እናቅርብላችኋለን፡፡ 

ከዚህ ጋር ተያይዞም በዘለቄታዊ መፍትሄው ላይ እንደ አማራ ለመምከር በቅርቡ ሁሉን አሳታፊ የሆነ የሕዝብ መድረክ የምናዘጋጅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

የአማራን ህዝብ ማህበራዊ እረፍት በመንሳት የራስን ሰላም ማግኘት አይቻልም!

አማራን ዘሩን ለይቶ በማፈናቀልና በመግደል ኢትዮጵያን ማፍረስ አይቻልም!

ክብርና ሞገስ በአማራነታቸው መስዋዕት ለሆኑ ወገኖቻችን!

የአማራ ብልጽግና ፓርቲ!

ጥቅምት 23/2013 ዓ.ም


3 min read

Published


Share this with family and friends


Follow SBS Amharic

Download our apps

Watch on SBS

SBS World News

Take a global view with Australia's most comprehensive world news service

Watch now