"የዋና ጽሕፈት ቤታችን ብርበራና በፀጥታ አካላት ቁጥጥር ስር መዋል ስጋት አሳድሮብናል" - ኦነግ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እየደረሰብን ያለውን ሕገወጥ ድርጊት እንዲያስቆምልንና ጉዳዩን መርምሮ ወደ ዐቃቤ ሕግ እንዲመራልን እንጠይቃለን

OLF

Source: Courtesy of PD

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) በዋና ጽሕፈት ቤቱ ላይ ብርበራና የቢሮ መዘጋት የገጠመው ስለሆነ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መፍትሔ እንዲያፈላልግለት በትናንትናው ዕለት ኦገስት 10 - 2020 የአቤቱታ ደብዳቤ ጽፎ አስገብቷል። 

ድርጅቱ የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ ምግባር አዋጅ 1162/2019 ስር በተደነገገው መብትና ግዴታ መሠረት እየተንቀሳቀሰ ቢገኝም ዘርፈ ብዙ ፈተናዎችና ዕንቅፋቶች እየደረሱበት መሆኑን አመላክቷል።

ከሁሉም በላይ ግና በቅርቡ በገዢው ፓርቲ የፀጥታ አካላት "በዋናው ጽሕፈት ቤታችን ላይ በተደጋጋሚ ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ እየተደረገ ያለውን ሕገ ወጥ የዋና ጽሕፈት ቤታችን ብርበራና ጽሕፈት ቤታችን በእነኚሁ ፀጥታ አካላት ቁጥጥር ስር መዋሉ ሥጋት ያሳደረብን መሆኑ[ን] በአፅንዖት እንገልጻለን" ሲል በአቤቱታ ደብዳቤው ላይ አስፍሯል።

ኦነግ በአዋጅ ቁጥር 1162/2019 ሰር የተደነገጉት መብቶቹ እንደተጣሱበት ጠቁሞ ዋነኛ ማሳያ ያላቸውንም በሶስት ነጥቦች አጣቅሶ አስፈሯል።

  1. ማንኛውም ሕጋዊ ሰውነት ያገኘ የፖለቲካ ፓርቲ በራሱ ጉዳይ ነፃነት እንዳለው በአዋጁ አንቀጽ 75 (2) ስር ተደንግጓል። እንዲሁም ቅርንጫፍ መሥሪያ ቤቶችንም በየትኛውም የአገሪቷ አካባቢ መክፈት እንደሚችል በአንቀጽ 76 ስር በግልጽ ተቀምጧል። ነገር ግን እኛ ተጨማሪ ቅርንጫፍ መሥሪያ ቤት መክፈት ይቅርና ሐምሌ 25 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ ገዢው ፓርቲ ባሰማራቸው የጸጥታ አካላት በዋና ጽ/ቤታችን ላይ ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ሕገ ወጥ ብርበራ ከማድረጋቸውም በተጨማሪ የድርጅቱ ሊቀመንበር የሆኑትን አቶ ዳውድ ኢብሳን ጨምሮ ሌሎች አባላትም ከቢሮአቸው እንዲወጡ ከተደረገ በኋላ የጸጥታ አካላቶቹም እኛ በማናውቃቸው ምክንያት ከፓርቲው አመራሮችና ሠራተኞች ውስጥ በከፊል ወደ ጽሕፈት ቤቱ ግቢ እንዲገቡ፤ ምንጩ ያልታወቀ የስም ዝርዝር ይዘው ከፊሎቹን ደግሞ ወደ ግቢ እንዳይገቡ በማድረጋቸው የፓርቲው ወቅታዊ ሥራ እንዲስተጓጎል ተደርጓል።
  2. በአዋጁ አንቀጽ 143 ስር በተደነገገው መሠረት ማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ላይ ማስፈራራት ወይም ወከባ ማድረግ የተከለከለ መሆኑን በግልጽ የሚያቀምጥ ቢሆንም በገዢው ፓርቲ እየተወሰደ ያለው እርምጃ ከድርጅቱ ሊ/መንበር ጀምሮ እስከ ታችኛው የድርጅቱ አባሎቻችን እንዲሁም የኦነግን የፖለቲካ አመለካከት የሚደግፉ ግለሰቦችን ጨምሮ ማስፈራሪያና አፈና እየደረሰባቸው ነው። ይህ ደግሞ በተለመደው አሰራር ጠንካራና ሰፊ የሕዝብ ድጋፍ ያላቸውን የፖለቲካ ፓርቲዎች የመንግሥትን ስልጣን ያለ አግባብ መጠቀም የሚከለክለውን አንቀጽ 135(1) (ለ) ስር የተደነገውን በመጣስ ከውድድር ውጪ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ያሳያል።
  3. በመሆኑም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በአዋጁ አንቀጽ 148 ስር በተደነገገው መሠረት እየደረሰብን ያለውን ሕገወጥ የጽ/ቤት ብርበራ፤ ወደ ጽ/ቤት እንዳንገባ እየተደረገ ያለውንና ሕገወጥ ድርጊት እንዲያስቆምልን፣ የእርምት እርምጃ እንዲያስወስድልን እየጠየቅን የጉዳዩን ስፋትና ጥልቀት መርምሮ ካመነበት ወደ ዐቃቤ ሕግ እንዲመራልን በትህትና እንጠይቃለን

በግልባጭም ይህንኑ አቤቱታውን ለተለያዩ የሰብዓዊ መብቶች ድርጅቶች፣ የመንግሥት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶችና ለዓለም አቀፍ የዲፕሎማሲ ማኅበረሰብ አካላት አስታውቋል።         


2 min read

Published

By Kassahun Seboqa Negewo


Share this with family and friends


Follow SBS Amharic

Download our apps

Watch on SBS

SBS World News

Take a global view with Australia's most comprehensive world news service

Watch now