አሜሪካ በዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለዉጥ ውስጥ ምን አስባለች?

ለመሆኑ የአሜሪካ የአየር ንብረት ለዉጥ ፖሊሲና እና የዓለም አቀፉ እዉነታ ምን ይመስላል በሚለዉ ላይ የአሜሪካ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የፕረስ ማዕከል /FOREIGN PRESS CENTER/ አማካኝነት ከመላው ዓለም ለተውጣጡና በተለይም በአየር ንብረት ለውጥ ላይ አተኩረው እየዘገቡ ለሚገኙ 50 ጋዜጠኞች አሜሪካ በተለያዩ ፈጠራዎች በመታገዝ እየሰራች ያለችውን ጥረት በተመለከተ ልዩ የበይነ መድረክ ጉብኝት ( virtual tour ) ተዘጋጅቷል።

Climate change

The sun rises on mountains surrounding Emerald Bay that are devoid of snow on April 12, 2021, in South Lake Tahoe, California. Source: Getty

በአሁኑ ወቅት  በዓለም አቀፍ ደረጃ የሰዉን ልጅና የምድርን ህልዉና እየተፈታተኑ ከሚገኙ ጉዳዮች አንዱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ የመጣዉ የአየር ንብረት ለዉጥ እንደሆነ የዘርፉ ተመራማሪዎችና ሳይንቲስቶች ይናገራሉ፡፡

በተለይም ዓለም በበካይ ጋዞች ልቀት፣ በቴክኖሎጂና በሌሎችም ጫናዎች ምክንያት የቀድሞ ገጽታዋን እየተነጠቀችና በፍጥነት እየተለወጠች በመምጣቷ  ምናልባትም ከጥቂት ዓመታት በኋላ፤  ምድሪቱ ለሰዉ ልጆችም ሆነ ለመላዉ ስነ ፍጥረት መኖሪያ ምቹ ላትሆን ትችላለች የሚል የስጋት ደዉልን ሳይንቲስቶች በተደጋጋሚ ሲያስተጋቡ ከከረሙ ቆይተዋል።

ለአየር ንብረት መለዋወጥና ለአካባቢ   ብክለት ከፍተኛዉን ድርሻ  የሚወስዱት በቴክኖሎጂ የበለፀጉ አገራት እንደሆኑ የሚታወቅ ሲሆን በተለይም ቻይና፣ ህንድ እና አሜሪካ የአንበሳዉን ድርሻ የሚወስዱ አገራት ናቸዉ፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ የካርበን ልቀት የሚያወጡ አገራትን ስንመለከት ቻይና በ27 በመቶ  ቀዳሚዋ ስትሆን አሜሪካና ህንድ ደግሞ በ11 በመቶና በ6.6 በመቶ  ከሁለት  እስከ ሶስት ያለዉን ደረጃ እንደሚይዙ ጥናቶች ያመላክታሉ፡፡

ታዲያ በቅርቡ ወደ ስልጣን የመጡት የአሜሪካዉ ፕሬዝዳንት  ጆ ባይደንና ካማላ ሃሪስ አገራቸዉ ወደ ከባቢያዊ አየር የምትለቀዉን በካይ ጋዝ  ለመቀነስና ቻይናንና ሩሲያን ጨምሮ በቴክኖሎጂ  የበለጸጉ አገራትም  የአየር ንብረት ለዉጥን ለመዋጋት  ዉይይት አካሂደዉ በርካታ መሪዎች ቃል መግባታቸዉ የሚታወስ ነዉ፡፡

ለመሆኑ የአሜሪካ የአየር ንብረት ለዉጥ ፖሊሲና እና የዓለም አቀፉ  እዉነታ ምን ይመስላል  በሚለዉ ላይ የአሜሪካ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የፕረስ ማዕከል /FOREIGN PRESS CENTER/ አማካኝነት ከመላው ዓለም ለተውጣጡና በተለይም በአየር ንብረት ለውጥ ላይ አተኩረው እየዘገቡ ለሚገኙ 50 ጋዜጠኞች አሜሪካ በተለያዩ ፈጠራዎች በመታገዝ እየሰራች ያለችውን ጥረት በተመለከተ ልዩ የበይነ መድረክ ጉብኝት ( virtual tour ) ተዘጋጅቷል።

በመጀመሪያ የበይነ መረብ ጉብኝትና ውይይት ከአሜሪካዉ ፕሬዝዳንት የአካባቢ ጉዳዮች መስሪያ ቤት ከተፍተ አማካሪና የአካባቢ ጉዳዮች ፕሮግራም ዳይሬክተር ዶክተር ዮናታን ፐርሺንግ ጋር የተደረገው ይገኝበታል።

በዉይይቱ ላይ ልዩ አማካሪው ዶክተር ፐርሺንግ እንዳብራሩት በእርግጥ በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴያችን አዳዲስ የቴክኖሎጂ እና የኢንዱስትሪ ዉጤቶችን እያስገኘን ቢሆንም በዚያዉ ልክ ግን አካባቢያችን እየጎዳን ዋጋ ሊያስከፍሉን የሚችሉ ጉዳዮች ከፊታችን ተደቅነዋል ብለዋል፡፡

አሁን ላይ የሰዉ ልጅ በስነ ምህዳር ታሪክ ዉስጥ አይቶት የማያዉቀው ነገር ከፊቱ ተደቅኗል የሚሉት ዶክተር ፐርሺንግ ፤ ይህም የሰዉ ልጆችና ተፈጥሮ መቋቋም  ከሚችሉት በላይ በፍጥነት እየተራመደ እንደመጣ ያሳስባሉ፡፡

የአየር ንብረት ለዉጥን ተከትለዉ በሰዉ ልጆች የሚመጡ ወረርሽኞች እና በሽታዎች እንደሚጨምሩ የሚናገሩት ተመራማሪዉ ይህም ከወባ በሽታና  ከዚካ ቫይረስ ከመሳሳሉ ወረርሽኞች የከፉ በሽታዎች  ይከሰታሉ ይላሉ፡፡

በተለይም ደግሞ በርሃማነት  በፍጥነት  እየተስፋፋ በመምጣቱ መካከለኛዉ ምሥራቅን የመሳሳሉ እጅግ ሞቃታማ አካባቢዎች የሚገኙ  ሰዎች  በሙቀቱ ምክንያት ከቤታቸዉ እስከመዋል የሚደርሱበት ጊዜ ሊመጣ ይችላል ይላሉ፡፡

የዓለም አገራት በአየር ንብረት ለዉጥ ላይ አፋጣኝ ምላሽና ተገቢዉን እርምጃ የማይወስዱ ከሆነም እኤአ በ2030 እና በ2050  ባሉት ጊዚያት ዉስጥ የሰዉ ልጅና ተፈጥሮ ህልዉናቸዉ አደጋ  ላይ ይወድቃል ሲሉ  ዶክተር ፐርሺንግ ያሳስባሉ፡፡

በተለይም ደግሞ በሙቀት መጨመሩ ምክንያት  የበረዶ ግግሮች እየቀለጡ ወደ ባህር  ስለሚተሙ  ችግሩን ያጎላዋል ባይ ናቸዉ፡፡

እንደ ተመራማሪው ሃሳብ ከሆነ በአየር ንብረት መለዋወጥ ምክንያት የሚመጣዉ ችግር ከፍተኛ የሆነ የሙቀት መጠን ብቻም ሳይሆን የምንስበዉ አየር የተበከለና መርዛማ በመሆኑ ህልዉናችን ለአደጋ  ይጋለጣል፡፡

እናም በሰዉ ልጅ እና በአጠቃላይ በተፈጥሮ ላይ የተጋረጠዉን አደጋ ለመከላከል የዓለም አገራት የአየር ንብረት ለዉጥን በመዋጋት ፤ የተለያዩ አማራጮችን ሊወስዱ እንደሚገባም ነዉ  ዶክተር ፐርሺንግ ያሳሰቡት፡፡

ታዲያ ለችግሩ  መባባስ ኃያላን አገራት በተለይም የአሜሪካ ባይደን- ሃሪስ አስተዳደር ምን እየሰራ ፣ ምንስ አቅዶ ይሆን?

እንደሚታወቀው የዓለም አገራት የአየር ንብረት ለዉጥን ለመዋጋት እ. ኤ አ በ2015 ( Cop25)  በፈረንሳይ መዲና ፓሪስ ላይ አንድ ስምምነት ላይ ደርሰዉ እንደነበር አይዘነጋም፡፡ ይህም የፓሪሱ የአየር ንብረት ለዉጥ ጉባኤ በመባል ይታወቃል፡፡

ይሁን እንጅ ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ ተሰናብተዉ ዶናልድ ትራምፕ ወደ ነጩ  ቤተመንግስት ከገቡ በኋላ ካሳለፉት ዉሳኔ መካከል አገራቸዉን ከፓሪሱ የአየር ንብረት ለዉጥ ስምምነት ማስወጣት የሚለዉ ይገኝበታል፡፡ ያንንም አደረጉትና ታላቋን አገር አሜሪካ ለወቀሳ ዳረጉ።

አሁን  ዶናልድ ትራምፕ ስልጣን ላይ የሉም። በምትካቸዉ ፕሬዝዳንት ጆይ ባይደንና ምክትላቸው ካማላ ሃሪስ  አገሪቱን በመምራት ላይ ሲሆኑ ትራምፕ ያሳለፏቸዉን ዉሳኔዎች እንደገና አፅንኦት ሰጥተዉ በመመልከት የተለያዩ የማሻሻያ ስራዎችን በመስራት ላይ ይገኛሉ፡፡

እንደ ዶክተር ፐርሺንግ ሃሳብም በአሁኑ ወቅት  ዋሺንግተን በፕሬዝዳንት ባይደን አማካኝነት የአየር ንብረት ለዉጥን ለመከላከል በተለይም አገሪቱ ወደ ከባቢያዊ አየር የምትለቀዉን የካርበን ክምችት ለመቀነስ ብዙ የቤት ስራዎችን መስራት እንደጀመረች አንስተዋል፡፡

ከነዚህም መካከል አሜሪካ ወደ 2015ቱ የፓሪስ ስምምነት የተመለሰች ሲሆን በቅርቡ የተከበረዉን የዓለም የምድር ቀንን አስመልክተዉ ፕሬዝዳንት ባይደን የተለያዩ አገራት መሪዎችን በመጋበዝ በጉዳዩ ላይ ውይይት ማድረጋቸዉን ተመራማሪዉ በገለፃቸዉ ወቅት አስታዉሰዋል፡፡

ዶክተር ፐርሺንግ ለጋዜጠኞች እንዳብራሩት ባይደን በምድር ቀን ዉይይት ላይ ቃል ገብተዋል፤ ይኸውም አገራቸዉ "የካርበን ልቀትን ለመቀነስ ካቀደችዉ ዕቅድ በ2030 በ50 በመቶ ለመቀነስ ትሰራለች" የሚለዉ ይገኝበታል፡፡

Johnathan Pershing.
Johnathan Pershing, Senior Advisor to the Spectial Presidential Envoy for Climate Change. Source: Demeke Kebede

ከዚህ ባለፈም እ .ኤ አ  በ2050 አሜሪካ የካርበን ልቀትን ሙሉ በሙሉ ለማጥፋት ዕቅድ እንዳለት ነዉ የባይደን-ሃሪስ አስተዳደር ያስታወቀዉ፡፡

ይህንን ዕቅድ ከግብ ለማድረስ ደግሞ  አገሪቱ የተያዩ ስራዎችን እንደምትስራ የገለፁት ዶክተር ፐርሺንግ በተለይም ኢንዱስትሪዎች ታዳሽ ኃይልን እንዲጠቀሙ ማድረግ እንዲሁም በነዳጅ የሚሰሩ ተሸከርካሪዎችን  በኤሌክትሪክ በሚሰሩ ተሸርካሪዎች መተካት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

ከአሜሪካ በተጨማሪም ለአየር ንብረት ለዉጥ መባባስ ትልቅ አስተዋፅኦ ከሚያበረክቱ አገራት መካከል አብዛኞቹ የካርበን ልቀታቸዉን ለመቀነስ መስማማታቸዉ ታዉቋል፡፡

ከእነዚህም መካከል የቦሪስ ጆንሰኗ ብሪታንያ በ2030 የካርበን ልቀቷን በ75 በመቶ ለመቀነስ ያቀደች ሲሆን በአጠቃላይ አዉሮፓ ደግሞ በተጠቀሰዉ ዓመት በ55 በመቶ ለመቀነስ ማቀዷን ልዩ አማካሪው ያስታወቁት፡፡

የላቲን አሜሪካዎቹ ብራዚል፣ ኮሎምቢያና ኮስታሪካም የበኩላቸዉን ድርሻ ለመወጣት እንሰራለን ያሉ ሲሆን የሩሲያዉ ፕሬዝዳንት ቪላድሚር ፑቲን በበኩላቸዉ አገራቸዉ የአየር ንብረት ለዉጥን ለመዋጋት በአረንጓዴ አሻራ ላይ ትኩረት ሰጥተዉ እንደሚሰሩ ቃል መግባታቸውን መረጃዎች የሚጠቁሙት፡፡

ነገር ግን እነዚህን እቅዶች ወደ ተግባር ለመለወጥ አሁን ወቅቱ ነዉን? የሚለዉን ጥያቄ ዶክተር ፐርሺንግ ያነሳሉ፡፡

ምክንያቱም አሁን ላይ ኮሮና ቫይረስ ዓለምን እያናወጠ የሚገኝ በመሆኑ የዓለም አገራት ትኩረታቸዉን ሁሉ ወረርሽኙን መከላከል ላይ ናቸዉ፡፡

ያም ቢሆን ግን ለሰዉ ልጆችና ለሌሎችም ስነ ፍጥረታት ምቹ መኖሪያ የሆነችዉን ምድር ከአየር ንብረት ለዉጥ መከላከሉ ቅድሚያ የሚሰጠዉ ጉዳይ እንደሆነ የአየር ንብረት ለውጥ ልዩ አማካሪውና ተመራማሪው ዶክተር ፐርሺንግ ዮናታን አሳስበዋል፡፡

( ደመቀ ከበደ ፡ የ SBS በይነ መረብ ጉብኝቱ ተሳታፊ ዘጋቢ )


5 min read

Published

By Demeke Kebede


Share this with family and friends


Follow SBS Amharic

Download our apps

Watch on SBS

SBS World News

Take a global view with Australia's most comprehensive world news service

Watch now