የሰላም ስምምነትና የጅምላ ይቅርታ በሰብዓዊ መብት ሕጎች መነጽር ሲታይ - ባይሳ ዋቅ ወያ

በቅርቡ 'የተወሰኑ የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት (ኦነሠ) አባላት በሰላም እጃቸውን ሰጥተው ወደ ማኅበረ ሰቡ ለመቀላቀል ተስማምተዋል' የሚል ዜና በሰፊው ተሠራጭቶ ነበር። በአገራችን ሁሉም ነገር ምሥጢር በመሆኑ፣ አሁን እጃቸውን ሠጡ የተባሉት የቀድሞ ዓማጽያን ቁጥር ስንት እንደ ሆነ እና የስምምነቱን ይዘት በተመለከተ ግልጽ የሆነ ነገር የለም። በብዛት የተዘገበው ግን የቀድሞ ዓማጽያኑ ወደየማኅበረ ሰባቸው ተመልሰው ሰላማዊ ሕይወት ለመምራት ችግር እያጋጠማቸው መሆኑን ነው። በዘገባዎቹ መሠረት፣ ችግሩ የመነጨው ከተለመደው የአገሪቷ ፖሊቲካዊ ቀውስ ሳይሆን፣ የቀድሞ ዓማጽያኑ ወደ ሰላማዊ ሕይወት ከመመለሳቸው በፊት በማሕበረ ሰቡ ላይ ከፈጸሟቸው በደሎችና ወንጀሎች ነው። ማኅበረ ሰቡ እያቀረበ ይገኛል ስለሚባለው ስሞታና ውንጀላ ግልጽ የሆነ መረጃም ሆነ ማስረጃ ለጊዜው ስለሌለ በዚያ ላይ ሙያዊ አስተያየት መሠንዘር አይቻልም።

Peace Talks.png

Credit: Getty Images

ስለዚህ ይህኛው ጽሁፌ የሚያተኩረው፣ የኦነሠ የቀድሞ ዓማጽያን በወሰዱት እርምጃ ላይ ብቻ ሳይሆን በዚሁ አሳብቤ በአጠቃላይ በየእርስ በርስ ግጭት/ጦርነት ወቅት ተፋላሚ ወገናት ማክበር ስላለባቸው የሰው ልጆች መብትና በሰላም ስምምነት ውስጥ መካተት ስላለባቸው የነዚህ የተጠቀሱት መብቶች ጥበቃ ላይ ነው።

ዓላማዬ፣ እነዚህ መብቶች ከተጣሱ፣ የቀድሞ ዓማጽያንም ሆኑ የመንግሥት መከላከያ ሠራዊት አባላት በሕግ የሚጠየቁበት ከባድ ወንጀል ስለ ሆነ የእነዚህን መብቶች ምንነትና ከተጣሱ ደግሞ መንግሥት መፈጸም ያለበትን ግዴታን ለሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ ቀለል ባለ መንገድ ለማቅረብ ነው። ጽሁፉ ሳይንሳዊ የሕግ ትንተና አይደለም ለማለት ነው።

ሰብዓዊ መብቶች

ሰብዓዊ መብቶች ተፈጥሮያዊ ናቸው። ባለቤት እንጂ ሰጪ የላቸውም። ሰው ሆነው በመፈጠራቸው ብቻ የሰው ልጆች ሁሉ ከተፈጠሩበት ቀን ጀምሮ እስከ ዕለተ ሞታቸው ድረስ እኩል የሚጎናጸፏቸው መብቶች ናቸው።
ባይሳ ዋቅ ወያ

የመብቶቹ ብቸኛ ባለቤት የሰው ልጅ ሲሆን፣ ይህንን መብት ለማስጠበቅ (ለማክበርና ለማስክበር) ግዴታ ያለበት ደግሞ መንግሥትና በአንዳንድ አጋጣሚዎች ደግሞ መንግሥታዊ ያልሆኑ ግን የተወሰነ ሕዝብ የሚኖርበትን ግዛት የሚቆጣጠሩ ኢ-መንግሥታዊ አካላት ናቸው።

ከእነዚህ መብቶች አንዳንዶቹ እንደየሁኔታው ለተወሰነ ጊዜም ቢሆን ሊገደቡ ይችላሉ። አንዳንዳቹ ግን፣ በሰላምም ሆነ በጦርነት ጊዜ በምንም ተዓምር እንኳን ሊጣሱ ይቅርና ሊገደቡ የማይችሉ ናቸው።

በ1966ቱ የዓለም ዓቀፉ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የሰው ልጆች መብት ቃል ኪዳን (ኮንቬንሽን) ውስጥ ሰባት በዚህ ደረጃ የተመደቡ ሰብዓዊ መብቶች ተጠቅሰዋል። እነዚህ ሰባቱ አይነኬ (non-derogable) የሰው ልጅ መብቶች (በራሴ ገዳዳ ትርጉም)፣

1) በሕይወት የመኖር (the right to life)፣

2) ከአሰቃቂ ድርጊት ነጻ የመሆን (freedom from torture)

3) ከባርነት ነጻ የመሆን (freedom from slavery)፣

4) በፍትሓ ብሔር ጉዳይ አለመታሠር፣

5) ድርጊቱ ሲፈጸም ወንጀል ተብሎ በሕግ ባልተከለከለ ድርጊት ዛሬ ተጠያቂ አለመሆን፣

6) በሕግ ፊት ከማንም ሰብዓዊ ፍጡር እኩል የመሆን (equality before law) እና፣

7) የሓሳብ እና የኃይማኖት ነጻነት ናቸው (Freedom of thought and religion) ናቸው።

እነዚህ መብቶች በሰላማዊም ሆነ በጦርነት ጊዜ ሊጣሱ ቀርቶ በጊዜያዊነት እንኳ ሊገደቡ የማይችሉ በቀላል አማርኛ ፍጹም አይነኬ የሆኑ ተፈጥሮያዊ መብቶች ናቸው። አገራችንንም ጨምሮ፣ በተግባር በየአገራቱ ሲፈጸም የምናየው እንኳ ከዚህ የተለየ ቢሆንም!

በጦርነት ወቅት ሰውን መግደል የተፈቀደ ነው። መግደል እንዲያውም የማንኛውም ጦርነቱ ዓላማ ነው። ተዋጊ ሆነህ የምትገድለው ግን እንዳንተው መሳርያ ያነገተና ዓላማው አንተን መግደል የሆነውን በታቃራኒ ወገን የተሠለፈን ተዋጊ ብቻ ነው።

ዓላማን ለማሳካት በተቻለ መጠን ጠቅላላውን “የጠላት” ወገን ተዋጊዎችን መግደል ያስከብራል፣ ጀግና ያሰኛል፣ የማዕረግ ዕድገት ያስገኛል። ዩኒፎርም ስለ ለበሰና ጠብመንጃ ስላነገተ ብቻ “ጠላት” ነው ብሎ መግደል ግን ወንጀል ነው። ተዋጊ “ጠላት” ተኩሶ ሊጎዳህ በማይችልበት ደረጃ ላይ ከሆነ ለምሳሌ፣ የተማረከ፣ የቆሰለ ወይም በራሱ ፈቃድ እጅ የሠጠ ከሆነ በእንደዚህ ዓይነት “ጠላት” ላይ እንኳን ግድያ መፈጸም ይቅርና አካላዊ ጉዳት ማድረስ አይቻልም።

ይህ እንግዲህ ዓለም ዓቀፋዊ ሕግ መሠረት ነው። የሰው ልጅ ግን በተፈጥሮው ከእንስሳም የከፋ ባሕርይ ስላለው፣ በጦርነት ወቅት “ሕጉ አይፈቅድልኝም ብሎ” እንኳን ምርኮኞችን ይቅርና በጦርነቱ የማይካፈሉትን ሰላማዊ የማኅበረ ሰቡን አባላትን ሳይቀር፣ ለምሳሌ፣ ሴቶችን አስገድዶ ከመድፈር፣ ወይም ደግሞ የአርሶ አደሩን ንብረት ከመዝረፍ፣ ለጠላት ያግዛሉ ብሎ የፈረጃቸውን ሰላማዊ ዜጎች ከመግደል፣ ከማፈናቀል፣ ከማገትና ከሌሎች ተመሳሳይ የወንጀል ድርጊቶችን ከመፈጸም አይቆጠብም።

ጦርነት ዕብደት ስለ ሆነ፣ ተፋላሚ ታጣቂ ኃይላት ጉልበት የለሹን ሰላማዊውን ሕዝብ ክፉኛ እንደሚጎዷቸው ብዙ የታሪክ ምሥክሮች ይገኛሉ። ዛሬ በአገራችንን እየተካሄደ ያለውን የእርስ በእርስ ግጭቶች በተመለከተ፣ የጥሰቱን ይዘትና መጠን በትክክል አናውቀው እንደሁ እንጂ፣ ተፋላሚ ኃይላት ጉልበታቸውን ተጠቅመው በሰላማዊ ሕዝቦቻችን ላይ የተለያዩ ወንጀሎችን እየፈጸሙ እንደ ሆነ መገመት አያዳግትም። በምድራችን በተካሄዱ በአብዛኛው የእርስ በእርስ ጦርነቶች ወቅት ተመሳሳይ ወንጀሎች ይፈጸሙ ስለ ነበር በአገራችን እየተካሄዱ ያሉት የእርስ በእርስ ግጭቶችን ከነዚያ የተለየ የሚያደርጋቸው ያለ አይመስለኝም።

የተፋላሚ ኃይላት የሰላም ስምምነት መፈራረም፣ በጦርነት ሜዳ የመገዳደል ድርጊቱ መቆሙን ሲያበስር፣ መብታቸው ለተጣሰባቸው ሰላማዊ ዜጎች ግን ፍትሕን ለማስገኘት የመጀመርያው ምዕራፍ ነው። የሚወሰዱ የፍትሕ ጎዳናዎች እንደያገሩ ቢለያዩም፣ ዋናው ቁም ነገር ግን፣ መብት ጣሶቹ ተዋጊዎቹ በምንም መልኩ ከፍትሕ አለንጋ እንዳያመልጡ በማድረጉ ላይ ነው። ሁለቱም ወገናት ተመሳሳይ አቋም መውሰድና ይህንን አቋማቸውንም ለመላው የአገሪቷ ዜጎችና ለዓለም ዓቀፉ ማኅበረ ሰብ ግልጽ በሆነ መንገድ በሰላም ስምምነት ሰነዶች ውስጥ በግዴታ ማካተት አለባቸው።

የቀድሞ ዓማጽያንን መልሶ በማኅበረ ሰቡ ውስጥ ለማቋቋም የሚያጋጥሙ ችግሮች፣

በየእርስ በእርስ ግጭት ወቅት ተፋላሚ ኃይላት በተለይም ዓማጺው ቡድን የትጥቅ ትግሉን በጀመረ በአጭር ጊዜ ውስጥ ድሎችን ካላስመዘገበ፣ ለምሳሌ የተወሰነ የአገሪቷን ግዛት ነጻ አውጥቶ የራሱን ባንዲራ በቋሚነት ተክሎ በዚያ ግዛት ያሉትን ሕዝቦች በይፋ ማስተዳደር ካልጀመረ ተዋጊዎቹ ማማረር ይጀምራሉ።

የዱር ሕይወት አመቺ ስላልሆነ በጦርነቱ መራዘም የተዋጊዎች ሞራል ይደክማል። ሕይወትን ያማርራሉ፣ የራሳቸው ግዛት ኖሯቸው ምርት አምርተው ራሳቸውን መቀለብ ስለማይችሉ ከሕዝቡ ቀምተው መብላት ይጀምራሉ። ሰዋዊ የጾታ ፍላጎታቸውን ለመወጣት ሲሉ ሴት ልጆችን ይደፍራሉ። ደጋፊያችን አይደለም ብለው የሚገምቱትን ሰው ያስራሉ፣ ይገድላሉ፣ ያሰቃያሉ። ሌላም ብዙ ብዙ የሰው ልጆች መብት ጥሰት ወንጀሎችን ይፈጽማሉ።

የመንግሥት ወታደሮችም በዓማጽያን ላይ ድል መቀዳጀት ሲያቅታቸው በብስጭት ተመሳሳይ ድርጊት መፈጸም ይጀምራሉ። ይህ ሁሉ ሲሆን ሰላማዊው ማኅበረ ሰቡ ታጣቂ ኃይላትን የሚገዳደርበት አቅም ስለሌለው፣ መብቱ ሲጣስበት አንገቱን ደፍቶ ሳይወድ በግድ የታዘዘውን ሁሉ እየፈጸመ ከሥቃዩ የሚገላገልበትን ቀን እየቆጠረ ይኖራል።

ተፋላሚ ኃይላቱ የሰላም ስምምነትን ከተፈራረሙ፣ እነዚህን ከላይ የጠቀስኳቸውንና ሌሎች ተመሳሳይ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን የፈጸሙ የቀድሞ ዓማጽያንና የመንግሥት ሠራዊት አባላት በሰላማዊ የማኅበረ ሰቡ አባላት ላይ ለፈጸሟቸው ወንጀሎች ተጠያቂ መሆናቸውንና ለፍርድ እንዲቀርቡ የሚገልጽ አንቀጽ(ች) በስምምነት ሰነዱ ውስጥ በማያሻማ መልክ መካተት አለበት።

ዝም ብሎ በቀላሉ “የሽግግር ጊዜ ፍርድ” ወይም “በሕገ መንግሥቱ መሠረት” ወዘተ በሚሉ ሓረጎች ተሸፋፍኖ የሚታለፍ ጉዳይ አይደለም ለማለት ነው። ተበዳዩ ማኅበረ ሰቡ ፍትሕን ማየት ይፈልጋል። ወንጀል የፈጸሙ የቀድሞ ዓማጽያን ሆኑ የመንግሥት ወታደሮች ለፍርድ ቀርበው በፈጸሙት ወንጀል ልክ ተፈርዶባቸው የሞራል ካሳ ማግኘት ይፈልጋል።

አጠቃላይ የሰው ልጆች ማኅበረ ሰብ ደግሞ፣ የሰው ልጆችን መብቶች ጥሰት ወንጀል የፈጸሙ የቀድሞ ዓማጽያንና የመንግሥት ወታደሮች በፈጸሙት ወንጀል ልክ በብሔራዊ ፍርድ ቤት ተገቢው ቅጣት ሲበየንባቸው አይቶ መርካት ይፈልጋል። የቅጣት ዓላማ ደግሞ ለዛሬው ተበዳይ ካሳ መክፈል ብቻ ሳይሆን፣ ለወደፊት ታጣቂዎች ተመሳሳይ ወንጀል እንዳይፈጽሙ ማስተማርያም ስለ ሆነ፣ በዳዮችን ለፍርድ ማቅረብ በምንም መልኩ ለድርድር የማይቀርብ ጉዳይ ነው።

ብዙ ዜጎች፣ የተራዘመና አውዳሚ የሆነው የእርስ በእርስ ጦርነትን በስምምነት ቋጭቶ ለብዙ ጊዜ የደፈረሰውን ሰላም መልሶ በማስፈኑ ብቻ የቀድሞ ዓማጽያንና ሰላማዊው ማኅበረ ሰብ “ይቅር ለእግዚአብሔር” ተባብለው ዓማጽያንን መልሰው ማቀፍና ማቋቋም አለባቸው ሲሉ ይስተዋላል። ይህ ስሕተት ነው።

እጅግ በጣም ውድ የሆኑና በምንም ሰበብ ወይም ምክንያት ሊጣሱ የማይችሉትን የሰው ልጆችን አይነኬ መብቶች የጣሱ የሁለቱም ወገን ተዋጊ ግለ ሰቦች ወይም መሪዎቻቸው በምንም ተዓምር ከምድራዊ የፍትሕ አለንጋ ማማለጥ የለባቸውም።

አዎ! ተፋላሚ ኃይላት ከተጠያቂነት ለማምለጥ ከማለት የሰላም ስምምነቱን ላይፈልጉ ይችላሉ። ይህም ሊሆን ይችላል። ከሰብዓዊ መብቶች መከበር አንጻር ሲታይ ግን፣ ከተዋጊዎቹ መካከል ወንጀል ፈጻሚዎቹ በቁጥር እጅግ በጣም አናሳ ስለ ሆኑ፣ እነዚህን ጥቂት የሰብዓዊ መብት ጣሶች ወንጀለኞችን አሳልፎ ላለመስጠት ተብሎ፣ የሰላም ስምምነቱን ማዘግየት አግባብ አይደለም።

አዎ! በአገራችን ታሪክ ያልተለመደ አሠራር ስለ ሆነ፣ ያው እንደ ለመድነው በሽምግልና፣ ወይም የተለያዩ ባሕላዊ የይቅርታ መፍትሔዎችን ተጠቅመን “ያለፈው አልፏልና ምዕራፉን ዘግተን ይቅር ተባብለን አዲስ ሕይወት እንጀምር” የሚሉ ዜጎች እንዳሉ እገምታለሁ።

ይህ አካሄድ ግን በተለያዩ ጊዜያት በአገራችን በተፈጠሩ የእርስ በእርስ ግጭቶች ወቅት ለዘመናት ስንጠቀምባቸው የነበረ “ጊዜያዊ ማስታገሻ ዘዴ” ቢሆንም፣ ተዋጊ ኃይላት ግን በማን አለብኝነት የሰብዓዊ መብት ጥሰት ወንጀሎቹን ከመፈጸም ስላልተቆጠቡ፣ ዛሬው ወንጀለኞችን ለፍርድ ማቅረብ፣ ተዋጊ ኃይላት ከዚያ ትምሕርት አግኝተው ለወደፊት ሰብዓዊ መብቶችን ማክበር ግዴታቸው መሆኑን እንዲገነዘቡ ይረዳል ባይ ነኝ።

ተዋጊ ኃይላትን በሕግ ሊያስጠይቁ የሚችሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ወንጀሎች፣

ጦርነት የራሱ የሆኑ ሕጎች አሉት። በ1949 ዓ/ም ጄኔቫ ላይ መንግሥታት የተፈራረሙት የሰብዓዊነት ሕግ ውል (humanitarian law) መሠረት በጦርነት ወቅት ተዋጊ ኃይላት ማክበር ስላለባቸው ደንቦች በዝርዝር ተቀምጠዋል። እነዚህ ደንቦች ደግሞ በያገሩ ሕገ መንግሥታት ውስጥ እንዲካተቱና የአባል አገራት መከላከያና ፖሊስ ትምህርት ቤቶችም እንደ ተቀዳሚ ኮርስ ወስድው የደንቦቹን ይዘት በጥልቅ እንዲማሩ ያሳስባል።

በተግባር መዋላቸው ያጠራጥራል እንጂ፣ ኢትዮጵያ እንደ አንድ የኮንቬንሽኑ ፈራሚ፣ ደንቦቹን ከሞላ ጎደል በሕገ መንግሥቱ ውስጥ አካትታለች። ተዋጊ ኃይላት ማክበር ስላለባቸው ደንቦች በጂኔቫውም ኮንቬንሽን ሆነ በያገራቱ ሕገ መንግሥታት በግልጽ የተቀመጡ ቢሆንም፣ የሰው ልጆች ባሕርይ ሆኖ፣ በውጊያ ሜዳ ላይ ዘወትር ሲከሰት የሚስተዋለው የተዋጊዎቹ እንሰሳዊ ባሕሪያቸው ነው። ስለሆነም ተዋጊዎቹ የታጠቀ ጠላትን ብቻ ሳይሆን በአካባቢው የሚኖሩ የሰላማዊ ዜጎችንም ሰብዓዊ መብት ከመጣስ ወደ ኋላ አይሉም።

ከሰላም ስምምነት በኋላ፣ የፍትሕ ሥርዓቱ ሊያተኩርባቸው የሚገባና ሊጣሱ ይችላሉ ተበለው ከሚገመቱ የሰብዓዊ መብቶች መካከል በ1998 ዓ/ም የተቋቋመውና በዓለም ዓቀፍ ደረጃ በሰው ልጆች ላይ የሚፈጸሙትን ሰብዓዊ መብት ጥሰት ወንጀሎችን ለመዳኘት ሙሉ ሥልጣን የተሠጠው የዓለም ዓቀፍ የወንጀል ችሎት (Internatinal Criminal Court)፣ በችሎቱ ደንብ አንቀጽ 7 መሠረት “የጸረ ሰው ልጅ ወንጀል” ማለት ከሚከተሉት የወንጀል ድርጊቶች ውስጥ አንዱ እንኳ መጠነ ሰፊ በሆነና በተቀነባበረ መልኩ በሲቪል ማኅበረሰቡ አባላት ላይ ሲፈጸሙ ነው። (ትርጉም የኔ)

gettyimages-2225752008-612x612.jpg
Close up at the official logo sign and inscription of the International Criminal Court ICC in front of the buildings of the intergovernmental organisation and international tribunal seated in The Hague, Netherlands, in July 2025. THE ICC is the first and only permanent international court with jurisdiction to prosecute individuals for the international crimes of genocide, crimes against humanity, war crimes, and the crime of aggression, intended to complement, not replace, national judicial systems. It can exercise its jurisdiction only when national courts are unwilling or unable to prosecute criminals. The ICC is distinct from the International Court of Justice ICJ an organ of the United Nations that hears disputes between states. Credit: NurPhoto/NurPhoto via Getty Images

ሀ) ግድያ ፣

ለ) ከምድረ ገጽ ላይ ማስወገድ፤

ሐ) በባርነት መያዝ፣

መ) በጉልበት ማፈናቀልና ማዛወር

ሠ) ማሠርና የመንቀሳቀስ መብትን መገደብ ፣

ረ) ማሠቃየት፣ ሰ) አስገድዶ መድፈር፣ ሴተኛ አዳሪ እንዲሆኑ ማድረግ፣ ማምከን እና ሌሎች ተመሳሳይ ጾታዊ ጥቃትን መፈጸም፣

ሸ) በአንድ ቡድን ላይ በማንነት፣ ባሕላዊ እሴት፣ በፖሊቲካ፣ በኃይማኖት ወይም በጾታ ላይ የተመሠረተ ጥቃት መፈጸም

ቀ) አስገድዶ እንዲሰወሩ ማድረግ ፣

ተ) ሌሎች ተመሳሳይ የሆኑና ሆን ተብለው በሆነ ቡድን ወይም ግለሰቦች ላይ የሚፈጸም ትልቅ የአካልና የአእምሮ ጉዳትን ሊያስከትሉ የሚችሉ ኢሰብዓዊ ድርጊቶችን የመሳሰሉትን መፈጸም የሚሉ ናቸው።

የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ወንጀሎችን ከሌሎች ተራ ወንጀል ድርጊቶች የተለየ የሚያደርጋቸው

ሀ) የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ወንጀሎች እንደ ሌሎች ወንጀሎች በይርጋ የሚታለፉ አይደለም። ወንጀሉ የተፈጸመው ከረጅም ጊዜያት በፊት ነውና ዛሬ ላይ እንደ አዲስ ተደርጎ ክስ መመሥረት አይቻልም ወይም አያስፈልግም ተብሎ አይታለፍም። የወንጀሉ ፈጻሚዎች በዚች ምድር ላይ በሕይወት እስካሉ ድረስ ከፍትሕ ሂደት ሊያመልጡ አይችሉም። ወንጀሉ ከተፈጸመበት አገር እንኳ አምልጠው ወደ ሌላ አገር ቢሰደዱ ወይም ቢኮበልሉ፣ ለፈጸሙት የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ዕድሜ ልካቸውን ተጠያቂ ናቸው።

ለ) በመንግሥትና በዓማጽያን መካከል እንኳ ስምምነት ተደርሶ ተኩሱ ቢቆምና የቀድሞ ዓማጽያኑ ወደ ሰላማዊ ኑሮ ቢመለሱም፣ መንግሥት ለሁለቱም ወገኖች ሰብዓዊ መብት ጣሽ ወንጀለኞች የጅምላ ወይም የግል አምኔስቲ አድርጎ ከወንጀል ተጠያቂነት ነጻ ሊያደርጋቸው አይችልም። አዎ! መንግሥት፣ የአገሪቷን ሕገ መንግሥት በመጻረር በጠብመንጃ ብርታት ሥልጣን ለመያዝ ከመሞከር ወንጀል ዓማጽያንን ከተጠያቂነት ነጻ ሊያደርጋቸው ይችላል። በተጨማሪም፣ ተፋላሚ ኃይላት ስለ ፈጸሟቸው የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት በሕገ መንግሥቱ መሠረት ፍርድ ቤቱ የበየነባቸውን ቅጣት ሊያቃልልላቸው ይችላል።

ሐ) የሰው ልጆች ሰብዓዊ መብት ጉዳይ የአንድ አገር መንግሥት ወይም የአገሩ ዜጎች ብቻ የውስጥ ጉዳይ አይደለም። ማንም ፍጡር፣ ግለ ሰብ ወይም ድርጅት በማንኛውም አገር ለተጣሱት ሰብዓዊ መብቶች ጠበቃ ሆኖ ፍትሕን ሊጠይቅ ይችላል። በወንጀሉ ድርጊት የተጠረጠረን ግለ ሰብ ደግሞ በቂ ማስረጃ እስከ ተገኘ ድረስ፣ የማንም አገር ፍርድ ቤት ሊዳኘው ይችላል።

መደምደምያ፣

የሰብዓዊ መብት ጣሾች በዚች ምድር ላይ በሕይወት እስካሉ ድረስ በወንጀል ተጠያቂ ናቸው። ማንኛውም ምድራዊ ኃይል ደግሞ ከተጠያቂነት ነጻ ሊያደርጋቸው አይችልም።

*******

*** ባይሳ ዋቅ-ወያ ቀደም ሲል በራሺያ ፌዴሬሽን - ሞስኮ የተባበሩት መንግሥታት ከፍተኛ የስደተኞች ኮሚሽን ተጠሪ ሆነው ያገለገሉ ናቸው።

ስዊድን፣ ታኅሳስ 2025 ዓ/ም

wakwoya2016@gmail.com


Share

9 min read

Published

Updated

By Bayisa Wak-Woya

Source: SBS


Share this with family and friends


Follow SBS Amharic

Download our apps
SBS Audio
SBS On Demand

Listen to our podcasts
Independent news and stories connecting you to life in Australia and Amharic-speaking Australians.
Ease into the English language and Australian culture. We make learning English convenient, fun and practical.
Get the latest with our exclusive in-language podcasts on your favourite podcast apps.

Watch on SBS
SBS World News

SBS World News

Take a global view with Australia's most comprehensive world news service