ሞት ይሙት፤ መኖር ይኑር! ለውይይት መነሻ

የዛሬ አርባ ዓመት ገደማ ይመስለኛል ወዳጄ ዶ/ር ደረጀ ከብዙ ዓመት እሥራት በኋላ አብረው ከተያዙት ብዙ የትግል ጓደኞቹ መካከል በተዓምር ተርፎ ሲለቀቅ በጻፈው አንድ መጣጥፍ መደምደምያ ላይ “ሞት ይሙት” ብሎ ያለው ሁሌም ከአዕምሮዬ አይጠፋም።

gettyimages-186765081-612x612.jpg

Street signs showing war and peace. Credit: Dimitri Otis/Getty Images

ያኔ ገና በወጣትነት ዕድሜዬ አፍጋኒስታን ለተመድ ሥራ ተመድቤ ብዙዉን ጊዜዬን የማሳልፈው ከሙጃሄዲን ተዋጊዎች ጋር ነበርና፣ ጦርነትና ግድያን ፊት ለፊት ባልጋፈጥም፣ ማታ ማታ ከተዋጊዎቹ ጋር ተሰብስበን በአስተርጓሚዬ ዕርዳታ ስናወራ፣ ጦርነት ምንኛ አስከፊና አስፈሪ መሆኑን ሲያወጉ እሰማ ነበር።

ዋና አዛዣቸውን፣ የዘመኑ ታላቅ የደፈጣ ውጊያ ጥበብ አባት ተብሎ የተዘፈነለትን የሰሜን አፍጋኒስታኑ “የፓንጅሺር አንበሳ” ኮማንደር አህመድ ሻህ ማሱድን ካንዴም ሶስቴ አግኝቼ ሳወራው፣ “ጦርነት በጎ ጎን የለውም፣ ሰላም ቢኖር ኖሮ እንደዚህ እንደ እንስሳ ቀኑን ሙሉ ተራራ ውስጥ ተደብቀን ስንዞር ማታ ማታ ደግሞ ድንጋይ ተንተርሰን ማደር ሳይሆን፣ ቤተ ሰብ መሥርተን እንደ ማንኛውም ሰዋዊ ፍጡር ተደስተን እንኖር ነበር” ይለኝ የነበረው ምን ጊዜምን አይረሳኝም።

በአንድ ጎደሎ ቀን፣ የተቀናቃኝ ተዋጊ ቡድን ተላላኪ፣ ጋዜጤኛ መስሎ ገብቶ በቦምብ ገደለው። የፓንጅሺሩ አንበሳም የተመኘውን ሰላማዊ ሕይወት ሳይኖር ተገደለ፣ ሕይወትን ሳይኖራት ሞተ!

ከአፍጋኒስታን በኋላ የዩጎዝላቭቢያ ጦርነት ተጀምሮ እስኪያልቅ ድረስ በቦታው ስለ ነበርኩ፣ ለዘመናት አብረው በሰላም ይኖሩ የነበሩ አንድ የስላቪክ ሕዝቦች፣ ጽንፈኛ ብሔርተኞች በሚመግቧቸው ያለፉ የታሪክና የትርክት ቁርሾዎች ሰበብ እርስ በእርስ ሲገዳደሉ በቦታው ሆኜ የማየት መጥፎ ዕድል ገጥሞኝ ነበር።

ያኔ በወጣትነት ዕድሜዬ ሆኖ ነው እንጂ ዛሬ አንድ ሚሊዮን ዶላር የወር ደመወዝ ይከፈልሃል ቢሉኝ በምንም ተዓምር ተመልሼ የምሄድ አይመስለኝም። ጦርነት ምን እንደ ሆነና ጦረኞቹም አእምሮያቸው የተረበሸ፣ ጠላት ብለው የፈረጁትን ቡድን ወይም ግለ ሰብ ለመግደል ቅንጣት ታክል ሰብዓዊነት የማይሰማቸው ከአውሬ የማይተናነሱ ክፉዎች መሆናቸውን የታዘብኩበት ያ ክስተት የሕይወቴ አካል ሆኖ ቀርቶአል።

ዛሬ በአገራችን በተለያዩ ምክንያቶች ልክ እንደ አሕመድ ሻህ ማሱድ ወይም እንደ ዩጎዝላቭ ተዋጊዎች ለሆነ “ዓላማ” ብለው የሰው ልጅን ለመግደል ጠብመንጃ አንስተው የገዛ ወገናቸውን ለመግደል ወደ ዱር የሚሰማሩ፣ ሕይወትን የማይኖሩ ሞትን ግን በየቀኑ ፊት ለፊት እንደ ተጋፈጡ ቀናትን የሚቆጥሩ ብዙ ሺህ ኢትዮጵያውያን ወጣት የደፈጣ ተዋጊዎችን ሕይወት ሳስብ፣ በወጣትነት ዕድሜዬ አፍጋኒስታንና ዩጎዝላቪያ ውስጥ ከሙጃሄዲንና ከስላቪክ ተዋጊዎች ጋር ያሳለፍኩት ጊዜ ፍንትው ብሎ ይታየኝና እጅግ በጣም ያሳዝኑኛል።

ሕይወትን ሳይኖሩ የሚሞቱ ወገኖቻችን!

ጦርነት፣ የሰው ልጅ ከፈጠራቸው ያለመግባባት መቋጫ መፍትሔዎች መሃል እጅግ በጣም አጥፊና ምድራዊ ተወዳዳሪ የማይገኝለት እርኩስ ድርጊት ነው። ሳያድለን ቀርቶ ግን፣ የሰው ልጅ፣ ቃየል በተራ ቅናት የገዛ ወንድሙን አቤልን ከገደለበት ቀን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ከፊተኛው ትውልድ የወረስነውን “ለዓላማ” ብሎ የመግደል ወይም የመሞት “ግዴታችንን” በተሻሻለ ዘዴና ዘመናዊ መሣርያ ድጋፍ እየተወጣነው እንገኛለን።

ድሮ ድሮ በጦርና ቀስት እንጋደል የነበርን ሕዝቦች ዛሬ ግን ምድር ላይ በክላሽኒኮቭ፣ ሰማይ ላይ ደግሞ በአይሮፕላንና በድሮን በሃሳብ ከማንግባባቸው ሰዎች ጋር እየተጋደልን ነው። ይህ ዓይነቱ አሟሟት እንግዲህ ፈጣሪ ራሱ ከቆረጠልን፣ ለሁሉም አይቀሬው ከሆነው ተፈጥሮያዊ ሞት በተጨማሪ መሆኑ ነው።

የሚያሳዝነው ደግሞ፣ ተፈጥሮ ራሱ በዚህች ምድር ላይ እንድንኖር የፈቀደልን ግፋ ቢል አንድ መቶ ዓመት ሲሆን፣ ይቺም በዛች ተብላ ደግሞ የሰውን ልጅ በመግደል ከዚያች ላይ ስንቀንስ ማየቱ ነው።

በተለምዶ አንድ ማኅበረ ሰብ የውጪ አገር ወራሪ ሲመጣበት፣ የማኅበረ ሰቡ አባላት በባዕድ የውጭ ኃይል አስተዳደር ሥር ከመኖር ይልቅ በተቻለ መጠን ተደራጅተው የተገኘውን መሣርያ በመጠቀም አገራቸውን ከወራሪው ኃይል ይከላከላሉ። ወራሪውን ኃይል ይገድላሉ፣ ይደመስሳሉ።

ይህ ዓይነቱ አገዳደል እንኳን በጥንት ዘመን ይቅርና ዛሬም ድረስ በዓለም ዓቀፍ ግንኙነት ውስጥ የተለመደና የማይወገዝ ነው። የአንድ አገር ሕዝብና ግዛት ሏዓላዊነት አይነኬ በመሆኑና አገር ከሌለ ሕዝብ የለም የሚል ብሂል በመላው የዓለም ዓቀፉ ማኅበረ ሰብ ዘንድ ዕውቅና ያገኘ ነውና!

በአንድ አገር ውስጥ የሚኖሩ የአንድ አገር ሕዝብና ዜጎች በሚያስተናግዷቸው አስተሳሰቦች ልዩነት ምክንያት ብቻ ጎራ ለይተው መገዳደሉ ግን በማንም ጤነኛ አእምሮ ባለው ሰው የማይደገፍና መወገዝ ያለበት ቢሆንም፣ የሰው ልጆች ግን በተለይም በአገራችን፣ አለመግባባትን በሰላም መንገድ ፈትተው የእርስ በርስ ግጭትን ለማስቆም ስላልቻሉ ወይም ስላልፈለጉ፣ ዛሬ በተለያዩ ክልሎቻችን እየተካሄዱ ያሉት ግጭቶችና ተጓዳኝ ግድያዎች የዚህ መጥፎ ክስተት ዓይነተኛ መገለጫዎች ሆነው እናገናቸዋለን።

ጦርነት እና ሞት

ሞት የሌላን ቤት ሲያጠቃ አያስደነግጥም እንጂ የራስን ቤት ሲመታ ሁሌም አዲስና ለማንም የማይመኙት አሳዛኝ ተፈጥሮያዊ ክስተት ነው። ይህ እንግዲህ ፈጣሪ ራሱ በቆረጠልን ቀን ይቺን ምድር ስንለቅ ነው።

የሰው ልጅ ግን በማያገባው የፈጣሪ ሥራ ጣልቃ ገብቶ፣ ያለ ፈጣሪ ፈቃድ አንድን የአምላክ ፍጡር ሲገድል ለዘመድ ወዳጅ የዘላለም ሃዘን ይሆናል። በተለይም የተገደለን ጓደኛ፣ ዘመድ ወይም የቤተሰብ አባል፣ ባሕሉና እምነቱ በሚፈቅደው መሠረት በክብር ለመቅበር ሳይቻል ሲቀር! ወይም ደግሞ የተገደለን ዘመድ ወይም ጓደኛ ሬሳ ከተገደለበት ቦታ ወስዶ ለመቅበር፣ የተገደለበትን ጥይት ዋጋ መጀመርያ ክፈል ሲባል! ከደርግ ጊዜ ጀምሮ በተግባር እያዋልን ያለው አሳፋሪና እጅግ በጣም አስከፊ ባሕል!

የጦርነት ቅዱስ የለም።

በመጀመርያ ደረጃ አንድ ታጣቂ ግለ ሰብ፣ ጠብመንጃ አንግቶ ዱር ከገባበት ወይም በጠብመንጃ ብርታት የፖሊቲካ ሥልጣን ከያዘበት ቀን ጀምሮ ዋነኛ ዓላማው ጠላት ብሎ የፈረጀውን ዜጋ ለመግደል ስለ ሆነ፣ ወይ ሥልጣኑን ለማደላደል አለያም ደግሞ ሥልጣን ላይ ያለውን አውርዶ ራሱ እንዲተካው ከማለት ተቀናቃኞቹን ይገድላል።

ብዙ “ጠላቶችን” የገደለ ደግሞ ጀግና ተብሎ ይወደሳል፣ ይሾማል፣ ይሸለማል። የወደፊት ሙያዊ ዕድገቱም የሚወሰነው በሚገድላቸው “ጠላቶች” ቁጥር ብዛት ስለ ሆነ ብዙ ዜጋ መግደልን እንደ ስኬት ይቆጥራል። ከግድያው በተጨማሪ ደግሞ አጋጣሚዎችን እየተጠቀመ በተለያዩ ሰበቦች ሴቶችን አስገድዶ ይደፍራል፣ ጠብመንጃ ያላነገቱትን ወጣቶች፣ “ለጠላት ድጋፍ ሠጥታችኋል” ብሎ ያሥራቸዋል፣ ይገርፋቸዋል፣ ይገድላቸዋል።

እነዚህ ሁሉ የወንጀሎች ዝርዝር ጠብመንጃ ባነገተ ግለ ሰብ “የድርጊት ሜኑ” ውስጥ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የተጠቃለሉ ናቸው። አንዳንድ የዋህ የፖሊቲካ ተንታኞች፣ “ተዋጊ ኃይሉ ወይም መከላከያ ሠራዊቱ” “ሰላማዊ ዜጎችን ጨፈጨፈ” “ሴቶችን ደፈረ” “ንብረት አወደሙ” ወዘተ ሲሉ ይሰማሉ። ይህ የዋኅነት ነው። ጦርነት አይጀመር እንጂ ከተጀመረ፣ ጠብመንጃ አንጋቾች “ጠላትን” ይጎዳል ወይም ያዳክማል ብለው ካመኑበት፣ መግደልን፣ ማሠቃየትን፣ ሴቶችን መድፈርን፣ ማገትን፣ ማሰርን፣ ንብረት የማውደምን፣ ወዘተ ተግባር ከመፈጸም ወደ ኋላ አይሉም።

አዎ! ጦርነቱ ካለቀ በኋላ፣ የጦር ወንጀሎች መፈጸማቸው ከተረጋገጠ፣ ገዳዮቹ በዓለም ዓቀፋዊና በአገሩ ሕገ መንግሥት መሠረት ተከስሠው ለፍርድ ሊቀርቡ ይችላሉ። ያም ቢሆን በዛሬው የዓለም ዓቀፍ ሁኔታ ተፈጻሚነቱ በጣም ውስን ነው።

በትግራይ ጦርነት ጊዜ ለተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰትና የጦር ወንጀሎች እስከ ዛሬ ድረስ አንድም ግለ ሰብ ወይም የቡድን መሪ ተጠያቂ አለመሆኑ ከላይ ላልኩት ውስንነት አንዱ አመላካች ነው።

ለዚህም ነው፣ ጦርነት አይነሳ እንጂ ከተነሳ ዋነኛ መገለጫው ሞት ሥቃይና ውድመት ብቻ ስለሆነ ጦርነት እንዳይነሳ ቀስቅስን የሰውን ልጅ ከመገደል ማዳን አለብን ብዬ ሁሌም የምወተውተው።

ጠብመንጃ መጀመርያውኑ ሲፈጠር ብቸኛ ዓላማው የሰው ልጅ እንዲገደልበት ነው። ሌላ ምንም ጠቄሜታ የለውም። በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ጥይት ለጥፋት እንጂ ለልማት ውሎ አያውቅም። ጥይት ማረሻ ሆኖ አይታረስበትም። ወይም መድኃኒት ሆኖ የሰው ልጅን ከሞት አያድንም።

አዎ! አገር ስትወረር፣ ወራሪውን በመከላከል ሂደት የሰው ልጅ “ወራሪ ጠላትን” መግደል ወንጀል አይደለም። የእርስ በርስ ግጭትን በተመለከተ ግን፣ ጠብመንጃ ምንጊዜም ለጥፋት እንጂ ለልማት ውሎ አያውቅም።

አንዳንድ ፖሊቲከኞቻችን “የዚህኛው ታጣቂ ቡድን ዓላማ እኮ ለኢትዮጵያ የግዛት አንድነት ስለሆነ ሊወገዝ አይገባም” ሲሉ ሌላው ወገን ደግሞ “ያኛው ቡድን እኮ የሚታገለው ለብሔሩ ነጻነትና እኩልነት እንጂ የሌላውን ሕዝብ ለመጉዳት ስላልሆነ፣ ትግላቸው ለቅዱስ ዓላማ ነው” ይላል።

ዓላማቸው ትክክል ይሁን አይሁን ሌላ ጉዳይ ነው፣ ግን ክላሽኒኮቭ በፋኖም ሆነ፣ በኦነግ ወይም በሕወሓት ታጣቂ ሲተኮስ የሚተፋው ባሩድ የሌላውን ኢትዮጵያዊን ነፍስ ከመግደል ውጪ አንዳችም ሌላ ተልዕኮ የለውም። የሁላቸውም ክላሽኒኮቭ እኩል ይገድላል።

ግድያ ሰብዓዊነት የለውም።

የሚገደለው ኢትዮጵያዊ ሲሆን ለግድያ የዳረገው በደል ደግሞ ከገዳዩ የተለየ አስተሳሰብን ማስተናገዱ ብቻ ነው። ገዳዮቹ ግን የማይረዱት ወይም ሊረዱ የማይፈልጉት ጉዳይ፣ መንግሥትን ተቃውሞ መሸፈት መብት የሆነውን ያህል፣ መንግሥትን መደገፍና አብሮ መሥራትም መብት እንደ ሆነ ማወቅ የተሳነን ሕዝቦች መሆናችንን ነው።

መንግሥትም ሆነ ተቃዋሚ ኃይላት ለሚፈጽሙት የሰብዓዊ መብት ጥሰት ወይም የጦር ወንጀሎች እኩል ተጠያቂ መሆናቸው እንደ ተጠበቀ ሆኖ!

የሚያሳዝነው ደግሞ፣ ተፋላሚ ወገናት የሚችሉትን ያህል ከገደሉ በኋላ፣ መጨረሻ ላይ “የሰላም ስምምነት ሲፈራረሙ” እና እየተሳሳቁ ተጨባብጠው በሻምፓኝ ሲራጩ፣ የሰላማዊው ማኅበረ ሰብ አባላት ግን እንደ ወጡ የቀሩ የቤተሰብ አባሎቻቸውን ሬሳ አግኝተው በክብር የመቅበር ዕድል እንኳ ማጣታቸውን አቤት የሚሉበት የፍትሕ ተቋም አጥተው ነጋም ጠባ፣ ዘላለማቸውን ዕንባቸውን እየረጩ ፍትሕን ከፈጣሪ እየጠበቁ ቀሪውን ሕይወታቸውን ለመጨረስ ሲገደዱ ማየት ነው።

ገዳዮች ሰላማዊ ሰውን ሲገድሉ፣ ሲያስሩና ሲያሠቃዩ ለፈጸሙት ወንጀል ተጠያቂ የሚያደርግ “ጥርስ ያለው” የፍትሕ ተቋም ስለሌለ፣ ተጠያቂነት ለመጥፋቱ ብቻ ሳይሆን፣ ለወደፊትም ተመሳሳይ ጥፋት እንዳይደገም አስተማሪ የሆነ ቅጣት የሚበይን አካል አለመኖሩ እጅግ በጣም ያሳዝናል።

ነፍስ ገዳዮች በወንጀል ተከስሰው ለፍርድ ቀርበው በጥፋታቸው ልክ ስለማይቀጡ፣ ተከታታይ ትውልድም ተመሳሳይ ወንጀል ከመፈጸም ወደ ኋላ የሚልበት ምክንያት አይኖርም።

በዩጎዝላቪያ ጦርነት ወቅት ከክሮኤሺያ ወገን ሆነው ሴርቦችን ለመውጋት የመጡና በአንድ አጋጣሚ ቦስኒያ ውስጥ ያገኘኋቸው ሶስት የዴንማርክ ቅጥረኛ አነጣጥሮ ተኳሽ ነፍስ ገዳይ ወጣቶች እንደ ነገሩኝ ከሆነ፣ በግድያ ሂደት ውስጥ ዋናው ችግር የመጀመርያውን ሰው መግደል ነው እንጂ ከዚያ በኋላ የፈለግኸውን ያህል ብትገድል የኅሊና ጭንቀት አያሳድርም።

ቅጥረኛ ነፍሰ ገዳዮቹ በየቀኑ ስለሚገድሏቸው የሳራዬቮ ኗሪዎች ሲያወሩኝ አደን ሄደው በለስ ቀንቷቸው የተመለሱ ያሕል ስኬታቸውን በደስታ ይገልጹታል እንጂ፣ የሰው ልጅን ሕይወት የቀጠፉ መስሎ በጭራሽ አይታያቸውም ነበር።

መጀመርያ ቀን አነጣጥረው የሰው ልጅን የገደሉ ዕለት ማታ ሲቃዡ እንዳደሩ ግን አልደበቁኝም። በየቀኑ እየደጋገሙ በገደሉ ቁጥር ግን፣ ጭንቀታቸው እየቀነሰ አዕምሮያቸው እየደነዘዘ፣ እንዲያውም አለመግደልን እንደ ክስረት የሚያዩ መሆናቸውን ገዳዮቹ ይነገሩኝ የነበረው ያላንዳች ፀፀት ነበር።

ዛሬ በተለያዩ የኢትዮጵያ ክልሎች ረዘም ላለ ጊዜ ተቃዋሚን በመግደል ሙያ ላይ የተሠማሩ ታጣቂዎችንና የመንግሥት ወታደሮችን የቀን ተቀን ሕይወትና የአዕምሮ ጭንቀት ምንኛ ጥልቅ እንደ ሆነ ከዚሁ ተነስቶ መገመት ይቻላል።

አለመግባባትን በውይይት እንጂ በጉልበት ሊፈቱ የማይሞክሩ መሪዎች እናገኝ ይሆን?

ዛሬ በአገራችን እየተከሰተ ላለው ሁለንተናዊ ቀውስ ዋነኛው ምክንያት የፖሊቲከኞቻችን ልዩነቶቻቸውን በውይይት ለመፍታት አለመቻላቸው ነው እንጂ የሃሳብ ልዩነቱ ለመገዳደል የሚያበቃ ምክንያት ሆኖ አይደለም።
ባይሳ ዋቅ-ወያ
እያንዳንዱ ተፋላሚ ቡድን መንግሥትንም ጨምሮ “ለኢትዮጵያ ችግር ብቸኛው መፍትሔ ያለው እኔ ጋ ብቻ ነው” ይላል። ከዚህ የተለየ ሃሳብ የሚያስተናግደው ተቃዋሚ ደግሞ እንደ ኢትዮጵያ ጠላት ይቆጠራል።

ተቃዋሚው ወገንም የኢትዮጵያ ችግር መፍቻው ቁልፍ ያለው እኔ ዘንድ ብቻ ነው ይላል። ስለዚህ ተቃዋሚ ኃይላትና መንግሥት ቦታ ቢቀያየሩ በአገራችን ሰላምና መረጋጋት ወዲያውኑ ሰፍኖ መገዳደል ሊቆም ይችላል የሚል ግምት ያላቸው ወገኖች ብዙ ናቸው።

ግምት ነውና ሊሆንም ላይሆንም ይችላል። በኔ ግምት ግን በዛሬው የኢትዮጵያ ሁኔታ ኦነግም ሆነ ፋኖ፣ ሕወሓትም ሆነ ሌላ የታጠቀ ቡድን የፖሊቲካ ሥልጣን መንበሩን ዛሬ ቢረከቡ፣ ሊያመጡ የሚችሉት ለውጥ እዚህ ግባ የማይባል ይሆናል ባይ ነኝ።

የፊተኞቹ ተከታታይ መንግሥታት ያደርጉ እንደ ነበረው፣ በመጀመርያ ቀን ጧት በሬዲዮ ባዶ ካዚና መረከባቸውን ለሕዝብ ያውጃሉ። የፖሊቲካ እሥረኞችን ይፈታሉ። ፓርላማ ይበትናሉ። ሕገ መንግሥት ያፈርሳሉ። ለታማኞቻቸው ከፍተኛ ሹመት ይሠጣሉ። የፊተኛውን መንግሥት ባለ ሥልጣናት በተለያዩ ወንጀሎች ከስሰው ለፍርድ ያቀርባሉ። ለተወሰነ ጊዜም ቢሆን የፕሬስ ነጻነት ይፈቅዳሉ።

ከእሥራት ለማምለጥ የቻሉ የቀድሞ የመንግሥት ባለ ሥልጣናት፣ የፓርቲ አባላት ወይም ደጋፊዎች ደግሞ በተራቸው የተቃውሞ እንቅስቃሴ ይጀምራሉ። ቢቻል በሰላማዊ መንገድ፣ ካልሆነ ደግሞ በጠብመንጃ ድጋፍ አዲሱን መንግሥት መውጋት ይጀምራሉ።

ተዋናዮቹ መድረክ ይቀያየራሉ እንጂ ድርጊቶቹ ተመሳሳይ ናቸው ማለት ነው። ቀልቀሎን በአቆማዳ መተካት!

ተቃዋሚ ኃይሎች ከፊተኛው መንግሥት የተሻለ ለውጥ አያመጡም ስል በምክንያት ነው።

በየግል ካላቸው ባሕርይ አኳያ ሳይሆን እንደ ተቋም፣ ዲሞክራቶች ሆነው፣ ከተቃዋሚ ወገን ጋር ሃሳብን በሃሳብ ሞግቶ በሠለጠነ መንገድ ተወያይቶ ለመስማማትና ካልተስማሙም ደግሞ ላለመስማማት ተስማማቶ አብሮ ለመኖር የሚያስችል የፖሊቲካ ባሕል እንደሌላቸው ሁላችንም እንደምናውቅ ስለማውቅ ነው።

ለምሳሌ ዛሬ እያስተዋልን ያለው፣ የአገራችን ተቃዋሚ ኃይላት የጋራ ጠላት እንጂ የጋራ ፍኖተ ካርታ መንደፍ ስላልቻሉ፣ በአንድ በሚቃወሙት ጠላት (መንግሥት) ላይ አንድ የጋራ አቋም ወስደው በአንድ የጋራ ድርጀት ሥር መሰባሰብ እንኳ አቅቷቸው እርስ በእርስ ሲወነጃጀሉና ሲጋደሉ እያየን ነው።

መንግሥትም ሆነ ተቃዋሚ ኃይላት የዚሁ የቀነጨረ ኋላ ቀር ባሕልን ከሚያስተናግድ “የጀግኖች” ማኅበረ ሰብ የተመረቱ ስለ ሆነ፣ በግለ ሰብ ተፈጥሮያዊ ባሕርይ ሊለያዩ እንኳ ቢችሉም፣ ልዩነትን አቻችሎ በሰላም አብሮ ከተቃዋሚ ጋር መኖርን በተመለከተ ግን አንዳቸው ከሌላው የተሻሉ ይሆናሉ ብሎ መገመት የዋህነት ይመስለኛል።

ዛሬ አገራችን እያስተናገደች ያለው ሁለንተናዊ ቀውስ ሁሉ ቢደማመር፣ እንደ ምክንያት (ዓላማ) ተቆጥሮ የገዛ ወገንን ነፍስ ለማጥፋት የሚያደርስ አይመስለኝም።

አዎ! ሌሎች የዓለማችን ማኅበረ ሰቦችም፣ በሆነ ጊዜ ልክ እንደ እኛው ወይም ከኛ በከፋ ዓይነት በጭካኔ ይገዳደሉ እንደ ነበር ከታሪክ መዛግብት እንረዳለን። በሂደት ግን የሰው ልጅ ነፍስ ከሁሉም በላይ ክቡር መሆኑን ተረድተው፣ ሰው ሰውን እንዳይገድል የሚረዳ የኅሊና ማዳበርያ ትምሕርት ላይ በማተኮራቸው ዛሬ ግድያን የሚጸየፍ ትውልድ ለማፍራት ችለዋል።

ዜጎቻቸውን ገና ከመዋዕለ ሕጻናት ጀምሮ፣ ሃሳብን በሃሳብ ሞግቶ ማሸነፍ ወይም ተሸንፎ መቀበል እንጂ ጉልበትን መጠቀም እንስሳዊ ባሕርይ መሆኑን ስለሚያስተምሯቸው፣ የአለመግባባቶች መፍትሔው ውይይት እንጂ መግደል እንዳልሆነ በደንብ ያውቃሉ።

ሕጻናት አድገው ፖሊስ ሲሆኑ፣ ግዴታቸው ዜጎችን ከጥቃት ለመከላከልና፣ ዳኛ ከሆኑ ደግሞ የዜጎችን ሰብዓዊና ሕገ መንግሥታዊ መብቶችን የማስከበር ዜጋዊ ግዴታቸው እንደ ሆነ ጠንቅቀው ይረዱታል። በቀላል አማርኛ፣ ገና ከሕጻንነታቸው ጀምሮ ሰው እንዲሆኑ አስተምረው ያሳድጓቸዋል ማለት ነው።

የኛ ማኅበረ ሰብ ግን፣ የተለየ አስተሳሰብ የሚያስተናግድን ዜጋ በሃሳብ ሳይሆን በጉልበት ማነጋገር እንዳለብንና በሃሳብ ከሚለዩት ዜጋ ጋር በሰላማዊ መንገድ ተወያይቶ አለመግባባትን ለመፍታት መሞከር የፍርሃትና የመሸነፍ ምልክት መሆኑን ነው አስተምሮ ያሳደገን።

የፖሊቲከኞቻችን ዋናው ችግር ለውጥን በራሳቸው ዕድሜ ዓይተው ከመሞታቸው በፊት ለማጣጣም ያላቸው ጉጉት ነው።

ይህን ለዘመናት የተጣበቀብንን በጉልበት የመግዛትና የማስተዳደር ባሕል አስወግደን በቦታው ልዩነትን አቻችሎ በሰላም የመኖርን ባሕል ለማዳበር ቀላል የቤት ሥራ አይሆንም። ረጅም ጊዜና መሠረታዊ የአስተሳሰብ ለውጥ እንዲኖረን ይጠይቃል።

ማኅበረ ሰባዊ ለውጥ ደግሞ ሊመጣ የሚችለው ወይ በዓመጽ (ሕዝባዊ ዓመጽ ወይም በትጥቅ ትግል) ወይም ደግሞ በዘገምተኛ ጥገናዊ ለውጥ ነው። ፖሊቲከኞቻችን ደግሞ ለውጥን ቢቻል ዛሬውኑ በራሳቸው ዕድሜ አይተውና ኖረውት አጣጥመውት ለማለፍ ስለሚፈልጉ፣ ለረጅሙ የጥገናዊ ለውጥ ሂደት ጊዜ የላቸውም።

በጠብመንጃ ድጋፍ የፖሊቲካ ሥልጣን ወንበር ላይ ለመቆናጠጥ በርግጥ የትግሉን ጉዞ ርቀት ሊያሳጥረው ይችል ይሆናል። በዚህ ዘዴ የሚመጣውን ለውጥ ደግሞ ከአጼ ቴዎድሮስ ጀምሮ እስከ ዛሬ ያሉን ተከታታይ መንግሥታት የመጡበት መንገድ ስለሆነ ይዘቱን በደንብ እናውቃለን።

ከማያባራ ግጭትና ጦርነት እንዲሁም ድኅነትና ውድቀት በስተቀር ከጉልበት ፖሊቲካ ያተረፍነው አንዳችም በጎ ነገር የለም።
ባይሳ ዋቅ-ወያ
ስለዚህ ኢትዮጵያ ሰላም፤ ዲሞክራሲና ፍትሕ የሠፈነባትና ዜጎች በሃሳብ ልዩነት ምክንያት የማይገዳደሉባት አገር እንድትሆን ከተፈለገ ተቀዳሚው ሥራችን ጠብመንጃ ከኢትዮጵያ ፖሊቲካ ወጥቶ ፖሊቲከኞች ሃሳብን በሃሳብ ብቻ መሞገት የሚችሉበትን ማሕበረ ሰብ ለመፍጠር የሚረዳ ፍኖተ ካርታ ማዘጋጀት አለባቸው።

“በጀግኖች አገር” ጠብመንጃ ይጥፋ በማለቴ አገር ወዳድ “አርበኞች” እንደሚያወግዙኝ የማውቀውን ያህል፣ የፈለግሁትን አስተሳሰብ የማስተናገድ ተፈጥሮያዊ መብቴ ደግሞ እንዲከበርልኝ ከወዲሁ እጠይቃለሁ።

ምን መደረግ አለበት?

የእርስ በርስ ጦርነት የሚያስከትለውን ጉዳት በአመክንዮ ሳይሆን በአፍጋኒስታን፣ ዩጎዝላቪያ፣ ቼችንያ፣ ጂዮርጂያ፣ ኮንጎ፣ ዩክሬይን፣ ሚያንማር (በርማ) እና ሞልዶቫን በመሳሰሉ አገራት በሥራዬ ጠባይ ምክንያት ስዘዋወር፣ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በየቦታው ተገኝቼ በዓይኔ ስላየሁ፣ አፌን ሞልቼ “ሞት ይሙት” “ሰላም ይኑር”“መገዳደል ይቁም”፣ ስል የአስተሳሰብ ልዩነት ለመገዳደል ምክንያት አለመሆኑን ስለ ተረዳሁ ነው።

ዛሬ እያገዳደለን ያለው “ታላቁ አጄንዳ” የማንነት ጥያቄ ነው።

ይህ ጥያቄ ደግሞ በዓለማችን ያሉ ሕዝቦች ሁሉ በተወሰነ ደረጃ ያስተናገዱትና እያስተናግዱ ያሉ ቢሆንም ጥያቄው ከመወያያ አጄንዳ አልፎ የመገዳደያ መሆኑን ካበቃ ሰንብቷል።

በበኩሌ አፌን ሞልቼ ለማለት የምችለው ለምሳሌ፣ ማንነትን አስመልክቶ የተለየ አስተሳሰብን ስላስተናገደ ብቻ አንድ ኢትዮጵያዊ ከሌላው ኢትዮጵያዊ የሚያንስበት ወይም የሚበልጥበት አንዳችም ምክንያት የለም።

መንግሥትን የሚደግፍ ወይም ገለልተኛ መሆን የመረጠ አንድ ኦሮሞ፣ አማራ ወይም ትግራይ፣ መንግሥትን ከሚቃወም የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት፣ ፋኖ ወይም ሕወሓት ደጋፊ እኩል ኦሮሞ፣ አማራ ወይም ትግራይ ነው።

በሌላ አነጋገር፣ “የምንሞትላትና የምንገድልላት” ኦሮሚያ፣ አማራ ወይም ትግራይ፣ ዳቦ ቢሆኑና ቢቆራረሱ፣ መንግሥትን የሚደግፈው፣ ገለልተኛውና ተቃዋሚውም የዳቦው እኩል ተቋዳሽ ናቸው።

ስለዚህ የኔ ዓላማ ብቻ ቅዱስ ነው ብሎ አንድን ዜጋ መግደል፣ ማፈናቀል፣ ማገትና ማሠቃየት በሰማዩም ሆነ በምድራዊው ሕግ የወንጀሎች ሁሉ ወንጀል ነው።

በዚህ “በማንነት” አጄንዳ ሳቢያ እየተካሄደ ባለው የመገዳደል ፕሮጄክት መተግበር ሂደት ውስጥ አንድ በጣም የሚያሳዝን ነገር ደግሞ፣ ከግጭት ቀጠናው ርቀው ባሕር ማዶ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን፣ በመንግሥትና በታጣቂ ኃይላት መካከል የተፈጠረው አለመግባባት በሰላም እንዲፈታ እንደ መስበክ፣ ቁሳዊና ሃሳባዊ ድጋፍ እየሰጡ የመገዳደሉን እሳት ከባሕር ማዶ ሆነው ሲሞቁት መታየታቸው ነው።

መንግሥትን ወይም ታጣቂዎቹን ደግፈው ከሁለቱም ወገን የሚሠዉት ኢትዮጵያዊያን ዜጎች መሆናቸው የተረሳቸው ባይሆንም፣ የሚገደለው ኢትዮጵያዊ “ጠላት” ተብሎ ከተፈረጀው ወገን እስከ ሆነ ድረስ የዜጋው መገደል ለአገራችን ችግር መፍትሔ አወንታዊ አስተዋጽዖ አለው ብለው ይገምታሉ።

የማይገባቸው ወይም እንዲገባቸው የማይፈልጉት ነገር ግን፣ በግጭት ቀጠናው የሚገደሉ ወጣቶች ዜጋ መሆናቸውን፣ የሚደፈሩት ሴቶች ልጆች ወይም ሚስቶች ኢትዮጵያውያን መሆናቸውን፣ የሚቃጠለው ሰብልና ተንቀሳቃሽ ወይም ቋሚ ንብረት የሆነ የውጪ ጠላት ንብረት አለ መሆኑን እንዲሁም የሚቃጠሉና ወደ ወታደራዊ ካምፕ የሚቀየሩ ት/ቤቶች የአገሪቷ ተስፋ የሆኑ የኢትዮጵያ ሕጻናት የሚማሩባቸው እንጂ የጠላት ንብረት አለመሆናቸውን ነው።

"ጀግንነት የወንጀሎች ሁሉ መነሻ ነው" ይላል ዶ/ር ደረጀ።

በአገራችን የእርስ በርስ ግጭት ወቅት ከሚዘወተሩና የጭካኔያችንን ደረጃ ከሚገልጹ የኋላ ቀር “የጀግንነት” ባሕል አንድ መገለጫው፣ አንዴ የጦርነት ነጋሪት ከተጎሰመ በኋላ፣ ስለ ሰላም ማውራት አሳፋሪ መሆኑን ነው።

ታሪኩ ጋንካሲ (ዲሽታ ጊና) በመስቀል አደባባይ “ጦርነት ይጥፋ፣ ሰላም ይኑር” በማለቱ ብቻ በቴሌቪዥን ቀርቦ የኢትዮጵያን ሕዝብ በአደባባይ ይቅርታ እንዲጠይቅ የሚያስገድድ ማኅበረ ሰብ ነው ያለን።

በዚህ ዓይነት የአዕምሮ ቀውስ ውስጥ፣ ማለትም ስለ ሰላም ማውራት የፍርኃት መገለጫ ሆኖ የሚታይበት “የጀግኖች” ማኅበረ ሰብ ምርት ስለሆንን፣ በሃሳብ የማይስማማንን ዜጋ በሃሳብ ሞግቶ ከማሸነፍ ይልቅ በጉልበት አሸንፎ ከማንበርከክ ውጪ ሌላ የግጭት መፍቻ መፍትሔ መጠቆም እንደ ኃጢያት ስለሚቆጠር፣ ዛሬ እኔ “ሃሳብን በሃሳብ ብቻ እንሞግት” ስል፣ የፈሪ ጎራ መፈክር ነው ብለው ቢኮንኑኝ ያልተጠበቀ አይደለም ማለቴ ነው።

መደምደምያ

ዛሬ አርባ አራት ዓመት ገደማ በሶቪዬት ኅብረት ትምሕርቴን ጨርሼ ወደ ኢትዮጵያ ለመግባት፣ በሞስኮ የኢትዮጵያ ኤምባሲ በፀረ አብዮትነት ወንጅሎኝ ነጥቆኝ በነበረው ፓስፖርት ምትክ ወደ ኢትዮጵያ እንድገባ የሚረዳኝ መታወቂያ ወረቀት (laissez-passer) ለማግኘት በኤምባሲው ረዘም ላለ ጊዜ ተመላልሼ ስማጸን ያስተወለኝ አንድ የኤምባሲው ባለ ሥልጣን ቀርቦኝ “አትፈለግም ተብለሃል እኮ ለምን ወደ ኢትዮጵያ ካልተመለስኩ ብለህ ትነፋረቃለህ፣ ይልቁንስ ወደ ሌላ አገር ሂድና ለአገሪቷ የሚጠቅም ሌላም ትምሕርት ጨምረህ ተማር፣ የእናት አገራችን ችግር እንደሆነ በቅርቡ የማይቀረፍ ስለሆነ የዛሬ አምሳ ዓመትም ተመልሰህ ብትመጣ ኢትዮጵያ እንዳለች ከነችግሮቿ ታገኛታለህ” ብሎ የመከረኝን፣ ከብዙ ዓመታት የውጪ አገር ኑሮ በኋላ ወደ አገሬ ስመለስ ነው የምክሩ ይዘቱ በደንብ የገባኝ።

የአገራችን ቀውስ ማለቂያ ያለው አይመስልም። ቢያንስ ቢያንስ ለሚቀጥሉት ሁለት ወይም ሶስት ትውልድ ዕድሜ የሚቀጥል ይመስለኛል።
ባይሳ ዋቅ-ወያ
እሱንም እኛ የዛሬው ትውልድ አባላት፣ ሃሳብን በሃሳብ ሞግቶ ማሸነፍ ወይም መሸነፍን ተለማምዶና አብሮ ለመኖር የመቻቻል ባሕልን መሠረተ ድንጋይ መትከል ዛሬ ከጀመርን። መሠረተ ድንጋዩን የትና እንዴት እናስቀምጥ? የመሠረተ ድንጋዩ ሲሚንቶና ድንጋይስ ከየት መምጣት አለበት? መሠረተ ድንጋዩንስ ማን ወይም እነማን ያስቀምጡታል? ወዘተ ጥያቄዎች እንደሚነሱ እርግጠኛ ነኝ።

አንደኛው፣ በኔ ብሔር ባሕል መሠረት ይሁን ሲል ሌላው ደግሞ አይ፣ በኔ ብሔር ባሕል መሠረት መሆን አለበት ስንባባል ገና ከጅምሩ ሳንግባባ ቀርተን ወደ ለመድነው የመጠላላት ልምዳችን እንመለስ ባዩ በዝቶ መፍትሔ ፍለጋው ተስፋ አስቆርጦን የምናቆም መስሎኝ ያስፈራኛል።

ዛሬ ተምረዋል በምንላቸው ወገኖቻችን መካከል እየተከሰተ ያለው የጸጉር ስንጠቃ እንካ ስላንቲያ ያሁኑ ትውልድ ለቀውሱ መፍትሔ ፍለጋ የሚረዳ የውይይት መሠረተ ድንጋይ ለመጣል ዝግጁ አለመሆኑን በግልጽ ያሳያል።

ታዲያ ነገያችን እንደዚህ የጨለመ፣ ከርቀት እንኳ የተስፋ ጭላንጭል የማይታየን ከሆነ፣ ተስፋ ቆርጠን እጃችንን አጣጥፈን ከፊተኛው ትውልድ የተረከብነውን የችግሮች ቅርጫት እንዳለ ለሚቀጥለው ትውልድ አስረክበን ወደዚያኛው ዓለም እንለፍ? ወይስ፣ እንደ ምንም ብለን ተወያይተን፣ ሃሳብን በሃሳብ ብቻ የመሞገት ባሕልን መሠረተ ድንጋይ ዛሬውኑ ለመጣል እንሞክር?

በግሌ “ከቀረ የዘገየ ይሻላል” ባይ ነኝ።

ስለሆነም፣ ወቅታዊው የአገራችን ሁኔታ እጅግ በጣም ተስፋ አስቆራጭ ቢሆንም ወይም መስሎ ቢታየንም፣ “እግዜር ያመጣውን እግዜር ይመልሰውን” እንደ ዋነኛ መመርያ ቆጥረን እጃችንን አጣጥፈን መቀመጡን አላምንበትም።

ፈጣሪ ወደ ምድር ወርዶ ምድራዊ ውጊያን ለአንዱ ወግኖ ተዋግቶ አያውቅም፣ ለእኛም አይዋጋልንም። በአንጻሩ ግን፣ ለዚሁ ዓላማ ብሎ “ጭንቅላት” የሚባል ትልቅ የማሰቢያና የመወሰኛ ተቋም ለያንዳንዳችን ባርኮ ስለ ሠጠን፣ እኛው በፍላጎታችን ለምንፈጥራቸው ምድራዊ ችግሮች ፈጣሪ ወርዶ እንዲፈታልን የምንማጸንበት ምክንያት የለም ባይ ነኝ።

ቅነነቱና ፍላጎቱ ካለ፣ ችግሮቻችን ሰው ሰራሽ እስከ ሆኑ ድረስ፣ እኛው ራሳችን ሰው ሰራሽ መፍትሔ እንደምናገኝላቸው ዕሙን ነኝ።

ጠብመንጃ አልባውን የፖሊቲካ ማኅበረ ሰብ ለመፍጠር ይጠቅማል ብዬ በአዕምሮዬ የሳልኩት ፍኖተ ካርታ አለኝ።

ፖሊቲካዊ ስኬት ደግሞ አጠቃላይ መመርያ እንጂ አንድ ወጥ የሆነ ሂሳባዊ ፎርሙላ ስለሌለው መቶ በመቶ ተግባራዊ ለመሆኑ ግን ዕርግጠኛ አይደለሁም። ከኔ የተሻሉ ሌሎች ሃሳቦችን ደግሞ የሚያስተናግዱ ዜጎች እንዳሉም አምናለሁ።

ምርጥ ሃሳቦች ደግሞ ሁሌም የሚፈልቁት ከጤናማ ውይይት ውስጥ ተጨምቀው ስለ ሆነ፣ ዛሬ ከእኛ የሚጠበቀው ተቀዳሚው የቤት ሥራ፣ እያንዳንዳችን የየግላችንን ወይም የቡድናችንን ሃሳብ ወደ አንድ መድረክ አምጥተን ለመወያየት ዝግጁ መሆን ነው።

አዎ! ለመተግበር ረጅም ጊዜ የሚፈጅ የሰላም ፍኖተ ካርታ ላይ መወያየቱ፣ ዛሬ ፖሊቲከኞቻችን የፖሊቲካ ሥልጣንን ለመጨበጥ ወይም የያዙትን ላለመልቀቅ በሚያካሄዱት የጉልበት ፖሊቲካ (መንግሥትና ተዋጊዎች ዛሬ የተዘፈቁበት የመገዳደል ድርጊት) ላይ ቀዝቃዛ ውሃ እንደ መቸለስ ተቆጥሮ ሊያስወግዘን ይችላል።

ይሁን! ምኞት አይከለከልም ሆኖ ነው እንጂ፣ መለኮታዊ ኃይል ቢኖረኝ ኖሮ ተፋላሚ ወገኖቹ የሚለዋወጡት የክላሽኒኮቭ ጥይቶች በረዶ ሆነው የዜጎችን ነፍስ በአጭር እንዳይቀጩ ባደርግ ደስታዬ ወሰን አይኖረውም!

ስለዚህ እኛ በጠብመንጃ አልባ ፖሊቲካ የምናምን ፖሊቲከኞች፣ አክቲቪስቶችና ልሂቃን፣ ዛሬውኑ አንድ የውይይት መድረክ ፈጥረን መውሰድ ስላለብን እርምጃዎች ላይ መወያየት ታሪካዊ ግዴታችን ይመስለኛል።

ሌሎቻችሁ ከዚህ የተለየ ወይም የተሻለ አስተሳሰብ ሊኖራችሁ እንደሚችል አምናለሁ። ስለዚህ እባካችሁ ሃሳባችሁን ወደ መድረክ አምጡና ተወያይተን አዳብረናቸው ለጋራ በጎነት ጥቅም እናውል።

ወጣቶቻችንን አላስፈላጊ ከሆነ ግድያ ለማዳን፣ እህቶቻችንን እንዳይደፈሩ፣ የሰላማዊው ሕዝብ ንብረት እንዳይወድም፣ ማሳዎች በበሬ እንጂ በዲሽቃ እንዳይታረሱ፣ ሕዝቦቻችን በሰላም እንዲዘዋወሩና እንዳይታገቱ የምንፈልግ ከሆነ ዛሬውኑ እርምጃ እንውሰድ እላለሁ!

ምን ትላላችሁ?

********

*** ባይሳ ዋቅ-ወያ ቀደም ሲል በራሺያ ፌዴሬሽን - ሞስኮ የተባበሩት መንግሥታት ከፍተኛ የስደተኞች ኮሚሽን ተጠሪ ሆነው ያገለገሉ ናቸው።

ስዊድን፣ ዴሴምበር 2025 ዓ/ም wakwoya2016@gmail.com

Share

16 min read

Published

Updated

By Bayisa Wak-Woya

Source: SBS


Share this with family and friends


Follow SBS Amharic

Download our apps
SBS Audio
SBS On Demand

Listen to our podcasts
Independent news and stories connecting you to life in Australia and Amharic-speaking Australians.
Ease into the English language and Australian culture. We make learning English convenient, fun and practical.
Get the latest with our exclusive in-language podcasts on your favourite podcast apps.

Watch on SBS
SBS World News

SBS World News

Take a global view with Australia's most comprehensive world news service