ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጥቅምት 27 - 2013 በሰጡት መግለጫ የአየር ኃይል በወሰደው እርምጃ ትግራይ ውስጥ በተለያዩ ሥፍራዎች ላይ የነበሩ ሮኬቶችን ጨምሮ ሌሎች የተለያዩ ከባድ የጦር መሳሪያዎችን ሙሉ በሙሉ እንዳወደመ አስታውቀዋል።
ሮኬቶቹ እስከ 300 ኪሎ ሜትር መወንጨፍ የሚችሉ በመሆናቸው እና 'በወንጀለኛው ቡድን' ሮኬቶቹን የመጠቀም ፍላጎት በመኖሩ በመቐለና አካባቢዋ በነበረው የከባድ መሣሪያ ማስቀመጫ ላይ የአየር ኃይሉ እርምጃ እንዲወስድ መደረጉን ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመግለጫቸው የጥቃቱን ሶስት ዋነኛ አላማዎችና የተከናወኑ ወታደራዊ ድርጊቶችን አስረድተዋል፡፡
- የመጀመሪያው አላማ ጥቃቱን መግታት ሲሆን፤ ጥቃት የተሰነዘረባቸው አካባቢዎች የመከላከያ ሠራዊት ያልነበረባቸው ቢሆኑም ከተለያዩ አካባቢዎች በመንቀሳቀስ ሙሉ የሎጀስቲክና የኃይል አቅርቦት በማጠናቀቅ የቡድኑን ጎዞ ሙሉ ለሙሉ በመግታት ተጨማሪ ጥቃት መሰንዘር ወደማይችልበት ደረጃ እንዲደርስ ተደርጓል።
- ሁለተኛው አላማ የመከላከያ ኃይልና የፖሊስ ሠራዊት የደረሰበትን ጥቃት ተከትሎ ይህንን ኃይል የመታደግና ወሳኝ አገራዊ ንብረቶችንና ትጥቆች የመታደግ ተግባር ሲሆን፤ በዚያም መሠረት በባድመ ግንባር፣ በጾረና በዛላምበሳ በዋና ዋና ቦታ ተሰልፈው ያሉ የሠራዊት አባላትና ትጥቆቻቸው ከቡድኑት ፍላጎት ውጪ እንዲሆኑ ማድረግ ተችሏል፡፡
- እንዲሁም የቡድኑን አቅም የማዳከሙ ዓላማ ተሳክቷል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመግለጫቸው ይህን ቡድን በአጭር ጊዜ ውስጥ በማስወገድ ለትግራይ ሕዝብ፣ ለመከላከያ ሰራዊትና ለፖሊስ ኃይል እፎይታና ሰላም በመስጠት የእርሻ ስራችንን መሰብሰብ የሚያስችል እቅድ መዘጋጀቱንም ተናግረዋል፡፡
የተጀመረው ዘመቻ ሲጠናቀቅ ዝርዝር መረጃ ለሕዝብ ይፋ እንደሚደረግ አስታውቀዋል፡፡

