በባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ የጠራው ሰላማዊ ሰልፍ በከተማ አስተዳደሩ ተቀባይነት ያላገኘ መሆኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ፡፡
ኮሚሽኑ በፌስቡክ ገፁ እንዳሰፈረው "የአዲስ አበባ ከተማ የከንቲባ ፅ/ቤት አስተዳደር ጉዳዩች ዘርፍ ጥር 18 ቀን 2013 ዓ/ም በቁጥር አ/አከፀ 18 /03/ 128 ለባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ በፃፈው ደብዳቤ ሰልፉ በልዩ ልዩ ምክንያቶች ተቀባይነት እንዳላገኘ ምላሽ የሰጠ ሲሆን ለአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽንም በግልባጭ አሳውቋል። ሰልፉ ተቀባይነት እንዳላገኘ ለባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ የተገለፀ ቢሆንም በአንዳንድ ማህበራዊ ሚዲያዎች ሰልፉ እንደሚደረግ መልእክት እየተላለፈ ይገኛል፡፡" ብሏል።
"ተቀባይነት ያላገኘ ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግ የህግ ተጠያቂነትን የሚያስከትል መሆኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታውሶ ጥር 23 ቀን 2013 ዓ/ም በአዲስ አበባ ከተማ ሰላማዊ ሰልፍ እናደርጋለን የሚሉም ሆነ መረጃውን እያሰራጩ የሚገኙ አካላት ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ" ሲል ኮሚሽኑ አሳስቧል፡፡ "ተላልፈው ሰልፍ ለማድረግ እንቅስቃሴ የሚያደርጉ አካላት ላይ በህግ አግባብ እርምጃ ለመውሰድ እንደሚገደድ" የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታውቋል፡፡
ትናት አርብ ምሽት ፖሊስ ኮሚሽኑ የሰልፉን መከልከል በተመለከተ በፌስቡክ ገፁ ተጨማሪ ማብራሪያ ሰጥቷል።
"ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ የጠራው ሰላማዊ ሰልፍ ሰልፉ በብሔር ፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች መካከል አሉባላታን በማናፈስ በዘረኝነት ላይ የተመሰረተ ጥላቻን ለማራመድ እና ባስ ሲል ደግሞ በሕዝቦች መካከል ግጭት የሚያነሳሳ ይዘት ያለው በመሆኑ እና በህግ ጉዳያቸው እየታዬ የሚገኙ የድርጅቱ ኃላፊዎች ያለምንም ቅድመ ሆኔታ እንዲፈቱ በመንግስት እና በፍትህ ስርዓቱ ላይ አሉታዊ ጫና የሚያሳድር እና የፍትህ ሂደቱን የሚያዛባ ሆኖ በመገኘቱ ሰልፉ እውቅና አልተሰጠውም፡፡ በአጠቃላይ ሀገራችን ካለችበት ነባራዊ ሁኔታ ጋር መንግስት ህግን የማስከበር ተልእኮውን አጠናቆና አጥፊዎችን ህግ ፊት ለማቅረብ በተለይ ደግሞ የሀገርን ህልውና ለማስከበር የውጪ ወራሪ ሀይልን ለመመከት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ባለበት እንዲሁም ከተማችን የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ለማዘጋጀት ቅድመ ዝግጅት ላይ እያደረገች ባለችበት እና የፀጥታ ኃይሉ ሙሉ ትኩረቱን በእነዚህ ጉዳዩች ላይ ባደረገበት ሰልፉ መደረጉ አሉታዊ ጎን እንዳለው ግልፅ ሲሆን በእነዚህ ምክንያቶች ሰልፉ እውቅና አለማግኘቱን ኮሚሽኑ ያስታውቃል፡፡" ብሏል ኮሚሽኑ።
በተያያዘ ኢዜማ የባልደራስን ሰልፍ መከልከል አውግዟል።
ኢዜማ "ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ መብት በሕገ መንግሥቱ እውቅና የተሰጠውና ክልከላ ሊደረግበት የሚገባ መብት አይደለም ብሎ ያምናል" ብሏል ባወጣው መግለጫ።
ኢዜማ " ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ መብት በሕገ መንግሥቱ እውቅና የተሰጠውና ክልከላ ሊደረግበት የሚገባ መብት አይደለም ብሎ ያምናል፡፡ ይህ መብት በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀፅ 30 የተደነገገ ሕገ መንግሥታዊ መብት ነው፡፡ ይህ መብት ፈቃጅና ከልካይ የሌለው መብት ሆኖ ሳለ የከተማ አስተዳደሩ ፈቃጅም ሆነ ከልካይ ሆኖ ቀርቦ ይህንን ሕገመንግሥታዊ መብት መጣሱ አግባብ አይደለም፡፡ " ሲል ክልከላውን ኮንኗል።
ኢዜማ እንዳለው "ዜጎች በሰላማዊ መንገድ ቀርበው ሀሳባቸውን የመግለፅም ሆነ የመሰብሰብ መብት አላቸው ፣ የከተማ አስተዳደሩ አሁን ላይ ሰልፉን ከአቅም በላይ በሆነ ምክንያት ማድረግ አይቻልም ብሎ ካመነ እንኳ ለሰልፉ አስተባባሪዎች ምክንያቱን ጠቅሶና አስረድቶ ሰልፉ የሚካሄድበትን ተለዋጭ ቀን ያመቻቻል እንጂ ሰልፉን የማስተጓጎልም ሆነ የመከልከል ስልጣን የለውም፡፡"
ኢዜማ በመግለጫው " ይህን መሰል ሕገ ወጥ ተግባር በፅኑ ይኮንናል፡፡ " ብሏል።
ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ በመጪው እሁድ ጥር 23/2013 በአዲስ አበባ ሰላማዊ ሰልፍ እንደሚያደርግ ትላንት በሰጠው መግለጫ ገልጿል።
ፓርቲው "በ4 መሰረታዊ ጉዳዮች ላይ ማለትም የፓርቲውን አመራሮች እስር፣ በአገሪቷ የተከሰተውን ማንነትን መሰረት ያደረገ ግድያ፣ የኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ እየፈፀመ ነው የሚለውን የመሬት ወረራ እንዲሁም የሱዳን ኃይል የድንበር ጥሰትን መቃወም የሰልፉ ዋነኞቹ አጀንዳዎች ናቸው" ማለቱ ይታወሳል፡፡

