ዶናልድ ትራምፕ በሚሊየን የሚቆጠሩ የመራጮች ድምፅ ተቆጥረው ሳያበቁ ራሳቸውን የፕሬዚደንታዊ ምርጫ አሸናፊ አድርገው ሰየሙ

*** "ይህን ምርጫ ለማሸነፍ በጥርጊያ መንገድ ላይ ነን" - ጆ ባይደን

US Election

A supporter of the Democratic party attends a watch party in Miami, Florida. Source: AFP

የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ በሚሊየን የሚቆጠሩ የመራጮች ድምፅ ተቆጥረው ሳያበቁ ራሳቸውን የ2020 ፕሬዚደንታዊ ምርጫ አሸናፊ አድርገው ገልጠዋል።

በዋሽንግተን ሰዓት አቆጣጠር ከንጋቱ 2.30am ፕሬዚደንት ትራምፕ ዋይት ሃውስ ውስጥ በሰጡት መግለጫ "ይህ በአሜሪካን ሕዝብ ላይ የተፈጸመ ማጭበርበር ነው። ለአገራችን ሐፍረት ነው። ይህን ምርጫ ለማሸነፍ ስንዱ ነበርን። በእውነቱ፤ ይህን ምርጫ አሸንፈናል" ብለዋል።

አክለውም ምንም እንኳ ድል ማድረጋቸውን ቢገልጡም የድምፅ ቆጠራው እንዲቆም ለዩናይትድ ስቴትስ ጠቅላይ ፍርድ ቤት አቤት እንደሚሉ ተናግረዋል።

በሌላ በኩል የዲሞክራት ፕሬዚደንታዊ ዕጩ ጆ ባይደን ከዊሚንግተን - ዴላዌር ከፕሬዚደንቱ ቀደም ብለው ባደረጉት ንግግር "አሁን ባለንበት ሁኔታ ጥሩ ስሜት ነው የሚሰማን። ዛሬ ማምሻውን እዚህ ተገኝቼ የምነግራችሁ ይህን ምርጫ ለማሸነፍ በጥርጊያ መንገድ ላይ መሆናችንን ነው። ታይቶ የማይታወቀው የቅድሚያ ድምፅ፣ የፖስታ ድምፅ ጊዜ እንደሚወስድ እናውቃለን። እናም አድካሚ የሆነው የድምፅ ቆጠራ እስኪጠናቀቅ ድረስ ትዕግሥት ሊኖረን ይገባል። እያንዳንዱ ድምፅ፣ እያንዳንዱ የምርጫ ሳጥን ተቆጥሮ እስከሚያበቃ ድረስ ምርጫው አያበቃም" ብለዋል። 

ፕሬዚደንቱ ያሻቸውን ቢናገሩም የድምፅ ቆጠራው ያልተጠናቀቁባቸው የምርጫ ጣቢያዎች ቆጠራቸውን የሚቀጥሉ ሲሆን፤ የምርጫው ውጤት በባይደን ወይም በትራምፕ ወገን ወደ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ካመራ የ2020 ፕሬዚደንታዊ ምርጫ አሸናፊን በይፋ ለመግለጽ ቀናት ወይም ሳምንታት ሊፈጅ ይችላል።

ይህ በእንዲህ እንዳለም የዩናይትድ ስቴት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ወንበሮችን የዲሞክራቲክ ፓርቲ በአምስት ተጨማሪ ወንበሮች ዳግም እንደሚያሸንፍ በፎክስ ኒውስ በኩል ቅድሚያ ትንበያ ተነግሯል። የዩናይትድ ስቴት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን በአብላጫ ለማሸነፍ 218 ወንበሮችን ማሸነፍ ያሻል።

በሕግ መወሰኛ ምክር ቤቱ በኩል እስካሁን በተካሄደው ድምፅ ቆጠራ ሁለቱም የሪፐብሊካንና ዴሞክራት ፓርቲዎች 47-47 ወንበሮችን በማግኘት መሳ ለመሳ ሆነዋል። 51 ወንበሮችን ያሸነፈ (50+ ምክትል ፕሬዚደንት) የሕግ መወሰኛ ምክር ቤቱን በአብላጫነት ሊመራ ይችላል።  

 

 

 


2 min read

Published

Updated

By NACA

Presented by Kassahun Seboqa Negewo



Share this with family and friends


Follow SBS Amharic

Download our apps

Watch on SBS

SBS World News

Take a global view with Australia's most comprehensive world news service

Watch now