የፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም የሽኝት ስነ ስርዓት በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ልደት አዳራሽ

*** "ፕሮፌሰር መስፍን አገራቸውን የሚወዱ ፣ ለእድገትዋም የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ያበረከቱ ናቸው" - አርቲስት ደበበ እሸቱ

Mesfin Woldemariam

Source: SBS Amharic

ዛሬ የቀብር ስነ ስርዓታቸው የሚፈጸመው የፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም የሽኝት ስነ ስርዓት በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ልደት አዳራሽ እየተካሄደ ነው።

በስነ ስርዓቱ ላይ ከ500 የሚበልጡ እንግዶች እንዲገኙ ጥሪ የተደረገላቸው ሲሆን በስፍራው ቤተሰቦቻቸው እና ወዳጆቻቸውን ጨምሮ በርካታ ሰው ተገኝቷል።

የአንጋፋው ፕሮፌሰር ልጅ ዶ/ር መቅደስ መስፍን፣ የቅርብ ጓደኛቸው አርቲስት ደበበ እሸቱ እንዲሁም የተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ በመርሃ ግብሩ ላይ ንግግር አድርገዋል።

ፕሮፌሰሩ ለአገራቸው መስዋዕትነት የከፈሉና ጽናትን ያስተማሩ ናቸው ያሉት አፈጉባኤ ታገሰ ጫፎ ለቤተሰቦቻቸውና ወዳጅ ዘመዶቻቸው መጽናናትን ተመኝተዋል።

የፕሮፌሰር መስፍን የቅርብ ወዳጅና የቀብር ሥነ ሥርዓት አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል አርቲስት ደበበ እሸቱ በበኩሉ "ፕሮፌሰር መስፍን አገራቸውን የሚወዱ ፣ ለእድገትዋም የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ያበረከቱ " ናቸው ብሏል።

የኢትዮጵያዊነትን ሀሳብ የሚያቀነቅኑት፣ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታና ሠብዓዊ መብቶች መከበር ባደረጉት ትግልም አሻራቸውን ያሳረፉ ፕሮፌሰር መስፍን ( ነፍስ ኄር  ) በረጅም ጊዜ የአካዳሚክ ሕይወታቸውም በድርቅና ረሃብ፣ በማህበራዊና ሌሎች መስኮች ጥናትና ምርምሮችን አካሂደዋል።

ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም በሕክምና ሲረዱ ቆይተው መስከረም 19 ቀን 2013 ዓ.ም በ90 ዓመታቸው ህይወታቸው ማለፉ የሚታወስ ነው።

በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በመካሄድ ላይ የሚገኘው የአስክሬን ሽኝት እንደተጠናቀቀ ወደ መንበረ ጸባኦት ቅድስት ስላሴ ካቴድራል በማምራት ስርዓተ ቀብራቸው ይፈፀማል፡፡

[ ደመቀ ከበደ ፡ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ]

 


1 min read

Published

By Demeke Kebede


Share this with family and friends


Follow SBS Amharic

Download our apps

Watch on SBS

SBS World News

Take a global view with Australia's most comprehensive world news service

Watch now