ጠቅላይ ሚኒስትር ስኮት ሞሪሰን ረቡዕ ዲሴምበር 29 ከአውስትራሊያ ዋና የጤና መኮንን ፖል ኬሊ ጋር ሆነው በኪሪቢሊ ሃውስ በጠሩት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ አንድ በኮቪድ-19 የተጠቃ ግለሰብ ተገኝቷል።
ይህንኑ አስመልክቶ ቃል አቀባያቸው "በኒው ሳውዝ ዌይልስ የጤና መመሪያ መሠረት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወሸባ እንዲገቡ ወይም እንዲመረመሩ ግድ ስለማያሰኝ በቫይረስ የመያዝ አለመያዛቸውን ምልክቶች በመከታተሉ ይቀጥላሉ" ብለዋል።
የረቡዕ ዕለቱ ጋዜጣዊ መግለጫ የተካሔደው ከቤት ውጪ ሲሆን፤ ታዳሚዎቹም የፊት ጭምብሎችን ያጠለቁ ነበሩ።
ኮቪድ-19 ኒው ሳውዝ ዌይልስ
ኒው ሳውዝ ዌይልስ ውስጥ በኮቪድ-19 ሳቢያ ለሆስፒታል የታደረጉ ሰዎች ቁጥር ለመጀመሪያ ጊዜ ከ1,000 አለፈ።
የሆስፒታል ሕሙማን ቁጥር ከሁለት ሳምንታት ባነሰ ጊዜያት በሶስት እጥፍ አሻቅቦ 1,066 ለመድረስ ችሏል።
በፅኑዕ ሕሙማን ክፍሎች ውስጥም 83 ሰዎች የሕክምና እርዳታ እየተደረገላቸው ይገኛል።
ባለፉት 24 ሰዓታት 18,278 ሰዎች በቫይረስ የተጠቁ ሲሆን ሁለት ለሕልፈተ ሕይወት በቅተዋል።
ኮቪድ-19 ቪክቶሪያ
ቪክቶሪያ ውስጥ ዕለታዊ በቫይረስ የተጠቁ ሰዎች ቁጥር ከ7,000 በላይ ሆኖ ቀጥሏል።
ባለፉት 24 ሰዓታት 7,172 ሰዎች በቫይረስ የተጠቁ ሲሆን የሶስት ሰዎች ሕይወት አልፏል።
472 የኮቪድ-19 ሕመምተኞች ሆስፒታል ውስጥ ሲገኙ 98 በፅኑዕ ሕሙማን ክፍሎች 22 በአየር መተንፈሻ መሳሪያዎች እየተረዱ ይገኛሉ።
ኮቪድ-19 ኩዊንስላንድ
ኩዊንስላንድ ውስጥ ሁለት ነፍሰ ጡር ሴቶች በፅኑዕ ሕሙማን ክፍሎች ይገኛሉ።
ኩዊንስላንድ በዛሬው ዕለት 3,587 ነዋሪዎቿ በቫይረስ የተጠቁባት ሲሆን በትናንትናው ዕለት 2,266 ሰዎች በቫይረስ መያዛቸውን አስመዝግባለች።
112 በሆስፒታል ሲገኙ አምስት ሰዎች በፅኑዕ ሕሙማን ክፍሎች ሕክምና እየተደረገላቸው ነው።
የኩዊንስላንድ ዋና የጤና መኮንን ጆን ጄራርድ ነዋሪዎች የሶስተኛ ዙር ተጨማሪ ማጠናከሪያ ክትባቶችን እንዲከተቡ አበረታተዋል። በተለይም እርጉዝና ለመፀነስ ዕቅድ ይዘው ያሉ ሴቶች ከትባቱን እንዲከተቡ አሳስበዋል።
የቫይረሱ መስፋፋት ቁጥርም እንደሚያሻቅብና ነዋሪዎች አስፈላጊውን የኮቪድ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ተነግሯል።
ኮቪድ-19 ታዝማኒያ
ታዝማኒያ በዛሬው ዕለት 404 ሰዎች በኮቪድ 19 እንደተያዙባትና ሶስት ነዋሪዎቿ ለሆስፒታል መዳረጋቸውን አስታውቃለች።
ትናንት ቅዳሜ በቫይረስ የተጠቁ ሰዎች ቁጥር 428 የነበረ ሲሆን፤ በክፍለ አገሪቱ በጠቅላላው1,219 ሰዎች በቫይረስ ተጠቅተዋል።
ፕሪሚየር ፒተር ጋትዊን በዘመን መለወጫ ዕለት ንግግራቸው የታዝማኒያ የክትባት መጠን ደረጃ ከፍ ያለ በመሆኑ ገድደቦ እንደማይጣሉና ወሰኖችም እንደማይዘጉ አመላክተዋል።
ሆኖም ወደ ታዝማኒያ የዘለቁ መንገደኞች ወይም ጎብኚዎች በቫይረስ ከተያዙ ወይም በቅርብ ንኪኪ ከተፈረጁ በራሳቸው ወጪ ወሸባ መግባት ግድ እንደሚላቸው አሳስበዋል።

