ግብፅ ከኢትዮጵያ የሁለተኛ ዙር ሕዳሴ ግድብ ሙሌት ጅማሮን አስመልክቶ ይፋ ደብዳቤ እንደደረሳት ጠቅሳ በውኃው ሙሌት ላይ ያላትን ተቃውሞ ገልጣለች።
የሁለተኛው ዙር ሙሌት ጅማሮ የፊታችን ሐሙስ ጁላይ 8 በተመድ ፀጥታ ምክር ቤት ላይ የሚነሳውን የሕዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ድርድር ጉዳይ ላይ ተጨማሪ ውጥረትን ያሳድራል ተብሎ ተገምቷል።
ግብፅና ሱዳን በሕዳሴ ግድብ ላይ ሕጋዊ አስገዳጅነት ያለው ውል ከኢትዮጵያ ጋር መፈራረም ይሻሉ።
ይሁንና የሁለቱ አገራት ሕጋዊ አስገዳጅነት ያለ ውል ተደጋጋሚ ጥያቄ በኢትዮጵያ በኩል በተደጋጋሚ ተቀባይነት አላገኘም።
በኢትዮጵያ በኩል የድርድሩ ሂደት በአፍሪካ ኅብረት በኩል እንዲካሄድና ዕልባት እንዲያገኝ የምትሻም ቢሆን ጉዳዩ በፀጥታውን ምክር ቤት ተነስቶ ይመከርበታል።
የሕዳሴ ግድብ ጉዳይ ለፀጥታው ምክር ቤት እንዲቀርብ በግብፅና ሱዳን ስም ጥሪ ያቀረበችው ቱኒዝያ ናት።

የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ሁለተኛ ዙር ውኃ ሙሌት ጉዳይ በፀጥታ ምክር ቤቱ እንዲነሳ መነሳትን አስመልክቶ የወቅቱ የወርኃ ጁላይ የተመድ ፀጥታ ምክር ቤት ፕሬዚደንትና በተመድ የፈረንሳይ አምባሳደር ኒኮላስ ዴ ሪቪዪሬ ባለፈው ሳምንት ሲናገሩ "የፀጥታ ምክር ቤቱ ማድረግ የሚችለው ነገር ትንሽ ነው። አገራቱን አገናኝቶ ስጋቶቻቸውን በጋራ እንዲገልጡ ከማድረግና ከስምምነት ላይ ለመድረስ ወደ ድርድር እንዲመለሱ ከማበረታት ባሻገር መከወን የሚችለው ነገር የለም" ሲሉ ለሪፖርተሮች ገልጠዋል።
ኢትዮጵያ በወርኃ ጁላይ ሙሌት 13.5 ኪዩቢክ ሜትር ውኃ ለማቋር ትልም አላት።

