የአፍሪካ ኅብረት ከዩክሬን ለመውጣት በጣሩ አፍሪካውያን ላይ 'አስደንጋጭ ዘረኝነትና የዓለም አቀፍ ሕግ ጥሰት' ተፈጽሞባቸዋል ሲል ድርጊቱን አወገዘ

*** የናይጄሪያ ፕሬዚደንት አማካሪ የዩክሬይን ድንበር ባለስልጣናት የናይጄሪያ ዜጎችን ድንበር ከመሻገር እንዳገዱና አንዲት ህፃን ያቀፈች ናይጄሪያዊት እናት በኃይል ተጎትታ ወንበሯን እንድትለቅ የተደረገች መሆኑን ተናግረዋል።

News

Chair of the African Union and President of the Republic of Senegal, Macky Sall. Source: Getty

የወቅቱ የአፍሪካ ኅብረት ሊቀመንበርና የሴኔጋል ሪፐብሊክ ፕሬዚደንት ማኪ ሳል እና የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማሃማት ዩክሬይንን ለቅቀው ድንበር ለመሻገር በጣሩ አፍሪካውያን ላይ የደረሰው የመብት ጥሰት አዋኪ መሆኑን ፌብሪዋሪ 28, 2022 በኅብረቱ ስም ባወጡት መግለጫ አስታወቁ። 

ሁለቱ ሊቃነመናብርት ማንኛውም ሰው በብሔራዊ ወይም የዘር ማንነቱ ሳይለይ በግጭት ወቅት ዓለም አቀፍ ድንበሮችን የማቋረጥ መብት እንዳለው አመላክተዋል። 

አፍሪካውያንን በመለየት የተፈጸመው ድርጊት "አስደንጋጭ ዘረኝነትና የዓለም አቀፍ ሕግም ጥሰት ነው" በማለት ሁሉም አገራት ዓለም አቀፍ ሕግን እንዲያከብሩና ዘር ሳይለዩ ለሁሉም ሰዎች እኩል አዘኔታን በመቸር እገዛ እንዲያደርጉ አሳስበዋል።  

የናይጄሪያ ፕሬዚደንት አማካሪ ጋርባ ሺሁ የዩክሬይን ድንበር ባለስልጣናት የናይጄሪያ ዜጎች ድንበር ለመሻገር አውቶቡሶችና ባቡሮች ላይ ከመሳፈር እንዳገዱ በደረሳቸው ሪፖርት መሠረት ባለስልጣናቱ የናይጄሪያ ዜጎችን እኩል እንዲያስተናግዱ አሳስበዋል።  

አቶ ሻሁ አንዲት ህፃን ያቀፈች ናይጄሪያዊት እናት በኃይል ተጎትታ ወንበሯን እንድትለቅ መደረጓንም አንስተዋል።

የፖላንድ ባለስልጣናትም ከዩክሬይን የመጡ ናይጄሪያውያን ድንበር እንዳይሻገሩ ማገዳቸውን ሪፖርቶች አመልክተዋል። 

ይሁንና በናይጄሪያ የፖላንድ አምባሳደር ጆአና ታርናውስካ "ማንኛውም ሰው የተስተናገደው በእኩልነት ነው። የተወሰኑ ናይጄሪያውያን ድንበር ተሻግረው ፖላንድ መግባታቸውን አረጋግጥላችኋለሁ" በማለት አስተባብለዋል። 

በርካታዎቹ ዩክሬይን ይኖሩ የነበሩት አፍሪካውያን ዓለም አቀፍ ተማሪዎች ሲሆኑ፤ ያሉበት ሁኔታ ለጊዜው ባይገለጥም ከ400 እስከ 500 የሚደርሱ ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች ዩክሬይ ይኖሩ እንደነበር ተነግሯል።  


1 min read

Published

By Kassahun Seboqa Negewo


Share this with family and friends


Follow SBS Amharic

Download our apps

Watch on SBS

SBS World News

Take a global view with Australia's most comprehensive world news service

Watch now