የፌዴራል ፓርላማ ዛሬ ኦገስት 4 / ሐምሌ 28 በሚሰየምበት ወቅት መንግሥት ለሚያቀርበው የአየር ንብረት ለውጥ ረቂቅ ይሁንታን ይቸራ ል ተብሎ ይጠበቃል።
ረቂቅ ድንጋጌው የካርበን ብክለትን በ2020 በ43 ፐርሰንት ለመቀነስ የተለመ ነው።
የፌዴራል መንግሥቱ ከግሪንስ ፓርቲ ጋር ባደረገው ስምምነት የአየር ብክለት ቅነሳ ዒላማ ለወደፊቱ ከፍ ሊል እንደሚችል ቃል ሰጥቷል።
የትምህርት ሚኒስትር ጄይሰን ሌየር ከሁሉም ወገን ያሉ የምክር ቤት አባላት ለረቂቅ ድንጋጌው ይሁንታቸውን እንዲቸሩ ጥሪ አስተላልፈዋል።
ይሁንና የተቃዋሚ ቡድኑ ባካሔደው ስብሰባ የሌበር መንግሥትን 43 ፐርሰንት የአየር ብክለት ቅነሳ ዒላማ በድንጋጌነት አልፎ ፅድቅ እንዲቸረው የማይሻ መሆኑን ከውሳኔ ላይ ደርሷል።
ይሁን እንጂ የታዝማኒያዋ የሊብራል ፓርቲ ተወካይ ብሪጂት አርቸር በፓርቲያቸው ውሳኔ እንዳልተስማሙና ድጋፋቸውን ለፌዴራል መንግሥቱ እንደሚሰጡ አስታውቀዋል።
ደቡብ ክልል
አዲሱ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝብ ክልል ምክር ቤት እኩል ደረጃ ያላቸው አራት ዋና ከተሞች እንደሚኖሩት አስታወቀ።
ምክር ቤቱ ይህን ያስታወቀው የብዝኅ ዋና ከተሞች ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅ ላይ ከክልሉ ስድስቱም ዞኖች ከተወጣጡ የኅብረተሰብ ተወካዮች ጋር ውይይት ባደረገበት ወቅት ነው።
የብዝኅ ከተሞች ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅ ቦንጋ፣ ተርጫ፣ ሚዛን አማን እና ቴፒ እኩል ደረጃ ያላቸው የክልሉ ዋና ከተሞች ይሆናሉ ይላል።
ቦንጋ ከተማ የፖለቲካ እና የርዕሰ መስተዳደሩ መቀመጫ፣ ተርጫ የክልሉ ምክር ቤት መቀመጫ፣ ሚዛን አማን የዳኝነት አካል መቀመጫ እንዲሁም ቴፒ የብሔረሰቦች ምክር ቤት መቀመጫ እንደሚሆኑም በረቂቅ አዋጁ ላይ ተቀምጧል።
የክልሉ ዋና ከተሞች አራት እንዲሆኑ የተደረገው ፍትሐዊ የኢኮኖሚ ዕድገትን ለማረጋገጥ እንደሆነም የብዝኃ ከተሞች ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጁ ይጠቅሳል።
ረቂቅ አዋጁ በቀጣይ በክልሉ ምክር ቤት ፀድቆ የሚተገበር ከሆነ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል እኩል ደረጃ ያላቸው አራት ዋና ከተሞች ያሉት የመጀመሪያው ክልል ይሆናል።
የውይይቱ ተሳታፊዎች የክልሉ ዋና ከተሞች አራት እንዲሆኑ በቀረበው ረቂቅ አዋጅ ላይ በሁሉም የክልሉ ማኅበረሰብ ዘንድ እኩል የሆነ ስምምነት ባለመኖሩ ተጨማሪ ውይይቶች ሊደረጉ እንደሚገባ ሐሳባቸውን ሰጥተዋል።
በተጨማሪም የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ወንድሙ ኩርታ በመሩት መድረክ የክልሉ የብሔረሰቦች ምክር ቤት ስልጣና ተግባር ለመዘርዘር የተዘጋጀው ረቂቅ አዋጅም ውይይት ተደርጎበታል።
(ETV)