የሕዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ውኃ ሙሌት ተጠናቀቀ

የኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን ቴክኒካዊ ውይይቶች ይቀጥላሉ

Amharic News 21 July, 2020

Source: Courtesy of PMOE

በወቅቱ ከፍ ያለ የክረምት ዝናብ ሳቢያ የሕዳሴ ግድብ የመጀመሪያ የውኃ ሙሌት መጠናቀቁንና ከቶውንም ተርፎ መፍሰሱን የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ጁላይ 21 ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

ጽሕፈት ቤቱ የግድቡ የመጀመሪያ የውኃ ሙሌት መከወኑን ያስታወቀው፤ ጁላይ 21 ተጀምሮ ዕለቱኑ የተጠናቀቀውን መለስተኛ የአፍሪካ ጉባኤ ድርድር ሂደትን ተከትሎ ነው።

በመለስተኛ ጉባኤው ላይ ከተደራዳሪ አገራት የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፣ የግብፅ ፕሬዚደንት አብዱል-ፈታህ አል-ሲሲና የሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒስትር አብዱላ ሃምዶክ ሲሆኑ፤ የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋኪ ማሃማትን አክሎ የቢሮው አባላት የሆኑት የኬንያ፣ የዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እና የማሊ መሪዎችና ተወካዮች ተገኝተዋል።

ጉባኤው የተመራው በደቡብ አፍሪካ ፕሬዚደንትና የወቅቱ የአፍሪካ ሕብረት ፕሬዚደንት ሲሪይል ራማፎሳ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የአፍሪካ ሕብረት - ለአፍሪካዊ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔዎችን ለማፈላልግ እያደረገ ላለው ጥረት ከፍ ያለ ዋጋ በመቸር፤ ሶስቱ አገራት ልዩነቶቻቸውን አርቀው ከስምምነት ላይ እንዲደርሱ ላበረከተው ሚናም ምሥጋናቸውን አቅርበዋል።

አክለውም፤ ኢትዮጵያ የዓባይን ወንዝ ፍትሓዊና ሚዛናዊ በሆነ መንገድ ግብፅና ሱዳን ላይ ጉዳት ሳታደረስ ሶስቱም አገራት ተጠቃሚ እንዲሆኑ የምታደርግ መሆኑን ዳግም አስገንዝበዋል።

የግብፁ ፕሬዚደንት አል-ሲሲ በፊናቸው ከጉባኤው በኋላ ባወጡት መግለጫ የሕዳሴ ግድብን ሙሌትና ክንውንን፤ እንዲሁም የዓባይ ወንዝን በሶስትዮሽ የጋራ ትብብር አጠቃቀም አስመልክቶ "ከአስገዳጅ ሕጋዊ ስምምነት ላይ ለመድረስ" እስኪችሉ ድረስ በድርድሩ እንደሚቀጥሉ መስማማታቸውን አስታውቀዋል።

የሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ሃማዶክ በበኩላቸው "ድርድሩን ከእልባት ለማድረስ" እንደሚቀጥሉ ገልጠዋል።

 የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋኪ ማሃማትም "ዓባይ ለሶሶቱ አገራት የሕይወትና የልማት ምንጭ በመሆኑ የሰላም ምንጭም ሆኖ መዝለቅ አለበት" ብለዋል። ሶስቱ አገራት በአፍሪካ ሕብረት አማካይነት ከስምምነት ላይ መድረሳቸውንም ጠቅሰዋል።

የዓባይ ወንዝን አጠቃቀም አስመልክቶ በአፍሪካ ሕብረት አደራዳሪነት በሶስቱ አገራት መካከል ከ80 አስከ 90 ፐርሰንት ከስምምነት ላይ መድረሳቸው ተደጋግሞ ቢነገርም ዝርዝር የስምምነት ውሎቹ ግና ይፋ አይደሉም። 

የሕዳሴ ግድብ ግንባታ ባለፈው ዓመት ከነበረበት ከባሕር ወለል በላይ 525 ሜትር በአሁኑ ወቅት 560 ሜትር ላይ የደረሰ ሲሆን፤ በመጪዎቹ ዓመታት 640 ሜትር ለማድረስ የግንባታ ሥራዎቹ ይቀጥላሉ።   

ምንም እንኳ የሕዳሴ ግድብ የመጀመሪያው ዓመት ሙሌት ቢጠናቀቅም ብዙዎች እንደጠበቁት በዕልልትና በሆታ አልታጀበም።

ግብፅ የውኃ ሙሌቱን አስመልክቶ "እየተካሄደ ያለው ድርድር ዕልባት እስኪበጅለት ድረስ ይፋ የሆነ የግድብ ምረቃ ሥነ ሥርዓት እንዳይካሄድ" ኢትዮጵያን መጠየቋን ጠቁማለች።

 


2 min read

Published

Updated

By Kassahun Seboqa Negewo


Share this with family and friends


Follow SBS Amharic

Download our apps

Watch on SBS

SBS World News

Take a global view with Australia's most comprehensive world news service

Watch now