የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የበላይ ጠባቂ አባቶች ጥቅምት 25 - 2013 ባወጡት ባለ ስምንት ነጥብ መግለጫ የፌዴራልና የትግራይ ክልል መንግሥታት አባታዊ ምክርና መልዕክቶቻቸውን እንዲቀበሉ ጥሪ አቅርበዋል።
- የተከበራችሁ የፌዴራልና የትግራይ ክልል መንግሥታት ከሁሉም በፊት ቅድሚያ ለአገራችን ሰላምና መረጋጋት በመስጠት በመካከላችሁ የተጀመረውን የርስበርስ ወታደራዊ ግጭት ያለምንም ቅድሚያ ሁኔታ እንድታቆሙ በአጽንኦት እንጠይቃለን።
- የተከበራችሁ የብልጽግናና የሕወሓት ፓርቲ አመራሮች በመካከላችሁ የተፈጠረው የፖለቲካ ልዩነት በመነጋገር የሚፈታ ስለሆነ አሁንም አሁንም በጉዳዮቻችሁ ላይ በግልጽ በመነጋገር እንድትፈቱት ጥሪያችንን እናስተላልፋለን።
- የተከበራችሁ በየደረጃው የምትገኙ የሃይማኖት አባቶች በሁለቱ አካላት የተጀመረው የርስ በርስ ጦርነት አስከፊ ውጤት እንደሚያመጣ ተገንዝባችሁ ችግሩ በሰላማዊ ውይይትና ድርድር እንዲፈታ አባታዊ ኃላፊነታችሁን እንድትወጡ አደራ እንላለን።
- የተወደዳችሁ የአገር ሽማግሌዎች፣ አባገዳዎች፣ እናቶች/አባቶችና ተፅዕኖ ፈጣሪ የኅብረተሰብ ክፍሎች በሙሉ በወንድማማቾች መካከል የተጀመረው ግጭት እንዳይባባስና ሁለቱም ወገኖች ወደ ሰላማዊ ድርድር እንዲመጡ በጎ ተፅዕኖ እንድትፈጥሩ ጥሪያችንን እናቀርባለን።
- የተከበራችሁ የብዙኅን መገናኛ ድርጅቶች ይህ ግጭት በሁለት ወንድማማቾች መካከል የሚካሄድ መሆኑን ተረድታችሁ ጉዳዩን በጥንቃቄና በከፍተኛ ኃላፊነት ስሜት እንድትዘግቡ አባታዊ የአደራ መልዕክታችንን እናስተላልፋለን።
- የተወደዳችሁ ወጣቶች በኢትዮጵያውያን ወገኖች መካከል የተፈጠረው ግጭት በወንድማማቾች መካከል የተፈጠረ መሆኑን ተገንዝባችሁ ችግሩን ከሚያባብሱ ሁኔታዎች እንድትቆጠቡ አደራ እንላለን።
- የተከበራችሁ የጸጥታ ኃይሎችና አመራሮች የተፈጠረውን ሁኔታ በከፍተኛ ጥበብና ማስተዋል እንዲሁም በሆደ ሰፊነት እንድትይዙት የአደራ መልዕክታችንን እናስተላልፋለን።
- የተከበራችሁ የማኅበራዊ ሚዲያ አንቂዎች በማኅበራዊ ትስስር የምታስተላልፉት መልዕክት ችግሩን ከማባባስ የተቆጠበና በአንጻሩም ለሰላም ጥሪ የሚያደርግ እንዲሆን እናሳስባለን።
በመጨረሻም በአገራችን የሚታየው የጥላቻና የክፋት መንፈስ እንዲወገድ ሁላችንም እንደየእምነታችን ሥርዓት ፊታችንን ወደ ፈጣሪ በመመለስ ከጥቅምት 26 ጀምሮ ለአንድ ሳምንት የሚቆይ የጸሎትና የምህላ ጊዜ መሆኑን አውቃችሁ በጸሎት እንድትተጉ አደራ እንላለን።
ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ሕዝቧን አብዝቶ ይባርክ
ለአገራችን ሰላም ይሁን
ጥቅምት 25 ቀን 2013 ዓ.ም
Share

