ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ትዕግስት ገዛኸኝ መንግሥቱ በቶኪዮ ፓራሊምፒክ 2020 የሴቶች 1500 T13 ምድብ 4:23.24 በመጨረስ ለኢትዮጵያ በታሪክ የመጀመሪያ የሆነውን የወርቅ ሜዳል አስገኝታለች።
የትዕግስትን ታሪካዊ የፓራሊምፒክ ድል አስመልክተው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ "ትዕግስት ገዛሀኝ መንግሥቱ በሴቶች 1,500 በማሸነፍና በፓራሊምፒክ ውድድር የወርቅ ሜዳልያ ለማስገኘት #በኢትዮጵያ የመጀመሪያዋ አትሌት በመሆኗ እንኳን ደስ ያለሽ። #ኢትዮጵያ ኮርታብሻለች!" ብለዋል።
በዚሁ ቅዳሜ ኦገስት 28 ምሽት በብሔራዊ ኦሎምፒክ ስታዲየም በተካሄደው የአራተኛ ቀን ውድድር የ21 ዓመቷን ትዕግስትን ተከትለው የዩናይትድ ስቴትሷ ሊዛ ኮርሶ ሁለተኛ፤ የቱኒዚያዋ ሶማያ ቦዩሳድ ሶስተኛ ሆነው የብርና የነሐስ ሜዳል አሸናፊዎች ሆነዋል።
ትዕግስት ባስገኘችው የወርቅ ሜዳል ኢትዮጵያ በሜዳል ሠንጠረዥ 48ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።
አውስትራሊያ 7 የወርቅ 10 የብር 11 የነሐስ በጥቅሉ 28 ሜዳሊያዎችን በአሸናፊነት በማግኘት በሜዳል ሠንጠረዥ 5ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።
በግንባር ቀደም የሜዳል ሠንጠረዥ ቻይና በአጠቃላይ 77 ፣ እንግሊዝ 43 ፣ የሩስያ ፓራሊምፒክ ኮሚቴ 41 ሜዳሊያዎችን በማግኘት በመሪነት ደረጃ ላይ ይገኛሉ።

