ከህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ(ህወሓት) ማዕከላዊ ኮሚቴ የተሰጠ መግለጫ

የህወሓት ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ከሚያዝያ 23 እስከ 25/ 2012 ዓ/ም ባካሄደው ስብሰባው ያሳለፋቸው ውሳኔዎችንና አቅጣጫዎችን በማፅደቅና መሰረት በማድረግ የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ የሚከተሉትን ውሳኔዎችን አሳልፏል፡፡

TPLF's statement

Source: Courtesy of PD

1. የኮረና ቫይረስ መከላከል ስራ ከዚህ በፊት ሲደረግ እንደቆየው አዲስ ለውጦች፣ ተጨባጭ የክልላችን ሁኔታ እንዲሁም ሳይንሳዊ ማሳረጃዎችን መሰረት በማድረግ ህዝባችንን ለማዳን እየተከላከልን ኢኮኖሚያዊ ጉዳት በሚቀንስ መልኩ እየተገመገመ በጥብቅ እንዲመራ ተወስኗል፡፡

 2. የ‘ብልፅግና’ ቡድን ከድሃ ጉሮሮ እና ልማት ቀምቶ ያልተቆጠበ ሃብት በማፍሰስ ሀገር ከጫፍ እስከ ጫፍ ለማበጣበጥ፤ በዶክሜንተሪ ፊልሞች የታገዘ ዘር የማጥፋት ጥሪ እንዲካሄድና ሁሉም መብቶች እንዲረጋገጡ እያደረገ ያለው ጭፍን ፀረ ህዝብና ስልጣንን በገንዘብ የመግዛት ተግባር እንዲቆም ብቻም ሳይሆን ከጥፋት መንገድ ወጥቶ በህገ መንግስት መሰረት የሚመለከተው ወገን ሁሉ ተሳትፎ ባረጋገጠ መልኩ እና ወደ ምክንያታዊ ውይይት እንዲገባ እንዲሁም ጨርሶ ሳይረፍድ ህገመንግስታዊ ስርዓት ከማፍረስ እንዲቆጠብ የህወሓት ማዕከላይ ኮሚቴ ያሳስባል፡፡

 3. ሙሉ ዝግጅትና የህብረተሰቡን ጤና የመጠበቅ ስራ በመስራት በህገ መንግስት በተዘረጋው ስርዓት መሰረት ሁሉንም እኩል ማየት የሚችል ኃይል የሚመራው ሀገራዊ ምርጫ እንዲካሄድ የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ ዳግም ያሳስባል፡፡

 4. ምርጫ በሀገር አቀፍ ይሁን በክልል ደረጃ በሺዎች መስዋዕትነትና ከፍተኛ ዋጋ የተከፈለበት ህገ-መንግስታዊ ዋስትና ያገኘ መብት እንጂ ገደብ የለሽ የስልጣን ጥማት ያለው ግልገል አምባገነን የሚሰጠው ወይም የሚከለክለው ችሮታ አይደለም፡፡ የትግራይ ህዝብ ከድሮም ቢሆን ራሱን በራሱ የማስተዳደር መብቱን በመስዋዕትነቱ ያረጋገጠ፤ በማንኛውንም ሁኔታ በራሱ ላይ ይሁን በሌሎች ህዝቦች ላይ ባርነት እንዲነግስ የማይፈቅድ ህዝብ ነው፡፡

 የትግራይ ህዝብ በመስዋዕትነቱ ያረጋገጠው መብት በማንኛውንም ጊዜ እና ሁኔታ ወደ ድርድር እንደማይቀርብና የዚህን መብት ተግባራዊነት ወደ ኋላ መመለስ የሚችል ማንኛውም ምድራዊ ፖለቲካዊ ኃይል እንደሌለ  የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ አስምሮበታል፡፡ ስለዚህም የፌደራል ስልጣን በአምባገነናዊ አኳኋን ተቆጣጥሮ ያለው ኃይል በተለመደው አካሄዱ የህዝቦችን መብት እየደፈጠጠ መቀጠሉን አጠናክሮ እየገፋበት በመሆኑ ህዝባችን በመስዋዕትነቱ ያረጋገጠው እና የማንም ፈቃድ የማይጠይቅበት፤ ራስን በራስ የማስተዳደር መብት በተግባር ለመተርጎም በክልላችን ምርጫ እንድደረግ እና ይህንን ለማድረግ የተጀመሩ ዝግጅቶች ለማድረግ የተጀመሩ ዝግጅቶች በህግ አገባብ ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ወስኗል፡፡

 የህወሓት ማዕከላይ ኮሚቴ በትግራይ ምርጫ እንዲካሄድ ሲወስን በ‘ብልጽግና’ ጥገኛ ባህሪ ምክንያት የተጀመረው ሕገ መንግስታዊ ስርዓት የማፍረስና ሃገር የመበተን ሂደት ወደ መጨረሻ ምዕራፍ እየደረሰ መሆኑን ይገነዘባል፡፡ አሁንም ቢሆን ሁሉም የኢትዮጵያ ብሄሮች ብሄረሰቦችና እና ህዝቦች የሀገራችንን ህገ መንግስት ያጎናፀፋቸው ራስን በራስ የማስተዳደር መብት እንዳያጡ ትግላቸው ማጠናከር እንደሚገባቸው ህወሓት ያምናል፡፡ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብም ይህንን ተገንዝቦ አዎንታዊ ሚና እንዲጫወት ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡

5. የ‘ብልፅግና’ ቡድን ምርጫ ላለማካሄድና የስልጣን ዕድሜውን ለማራዘም እየወሰዳቸው ካሉ ህገ ወጥ እርምጃዎችና ሴራዎች በተጨማሪ የድርጅታችን ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ በትግራይ ክልል ህግና ስርዓት እንደሚቀጥልና ‘ብልፅግና’ ምርጫ ለማስቀረት እየሰራ በመሆኑ በትግራይ ደረጃ በህግ መሰረት ምርጫ ለማካሄድ ውሳኔ ባሳለፈበት ወቅት የብልጽግና መሪ አሁንም መሰረታዊ የህዝቦች ራስን በራስ የመወሰን መብት ክብር እንደሌለው በሚያሳይ መልኩ የጦርነት አዋጅ ይፋ አድርጓል፡፡ የትግራይ ህዝብ በፉከራና የጦርነት ነጋሪት መጉሰም እንደማይደነግጥና  መብቱን አሳልፎ እንደማይሰጥ የሚታወቅ ሃቅ ነው፡፡ ኃላፊነት በጎደለው አካሄድ እንዲሁም የ‘ብልፅግና’ ቡድን  እና መሪው የሚመጣ ማንኛውንም ጥፋት ብቸኛው ተጠያቂዎች ራሳቸው መሆናቸው መላው የኢትዮጵያ ህዝብና ዓለምአቀፉ ማህበረሰብ መገንዘብ ይገባቸዋል፡፡

 6. በልማት ስራዎች፣ የዴሞክራሲ ባህል እና አስተዳደር የተጀመሩ ለውጦች በጊዜ የለንም መንፈስ በበለጠ ፍጥነት ተጠናክረው እንዲቀጥሉ በየደረጃው ያለው አመራር በከፍተኛ የኃላፊነት መንፈስ እንዲሰራው ተወስኗል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ መላው ህዝባችንና ሁሉም የመንግስትና የድርጅት መዋቅሮች ለርካሽ ዓላማቸው ሲሉ ከልማትና የዴሞራሲ ግንባታ ሃዲድ አውጥተው ወደ ብጥብጥና ጥፋት ሊያስገቡን የሚረባረቡ ብልጽግና ኃይሎች፣ አይዞህ ባዮችና እና ተላላኪዎቹ ለመመከት የተጀመረውን ትግል እንዲጠናከር ተወስኗል፡፡ 7. የራስን ዕድል በራስ የመወሰንና ራስን በራስ የማስተዳደር መብት፣ የህዝባችን ደህንነትና ሰላምን የማረጋገጥ ጉዳዮች ላይ አብሮው ሊሰሩ ዝግጅ ከሆኑ የሀገራችንና የክልላችን የፖለቲካ ኃይሎች የተጀመረውን ዝምድና በፍጥነት ወደ ከፍተኛ ደረጃ እንዲሸጋገርና ትርጉም ያለው ለውጥ ሊያመጣ ወደሚችልበት የህዝባችን ደህንነትና የዴሞክራሲ ባህል ግንባታ ስራዎች እንዲገባ የህወሓት ማእከላይ ኮሚቴ ወስኗል።የህገ መንግስታዊ ስርአትንና መንግስትን አስፈላጊነትና ቀጣይነት በአግባቡ ተረድታችሁ ፣ይህን ለማረጋገጥ የድርሻችሁ ሀገራዊ ግዴታ እንደምትወጡ እና ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ እንቅስቃሰያችሁን አጠናክራችሁ እንደምትቀጥሉ የህወሓት ማእከላይ ኮሚቴ ያምናል።

ግንቦት 23/ 2012 ዓ/ም

መቐለ


Share

Published

Updated


Share this with family and friends


Follow SBS Amharic

Download our apps
SBS Audio
SBS On Demand

Listen to our podcasts
Independent news and stories connecting you to life in Australia and Amharic-speaking Australians.
Ease into the English language and Australian culture. We make learning English convenient, fun and practical.
Get the latest with our exclusive in-language podcasts on your favourite podcast apps.

Watch on SBS
SBS World News

SBS World News

Take a global view with Australia's most comprehensive world news service
ከህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ(ህወሓት) ማዕከላዊ ኮሚቴ የተሰጠ መግለጫ | SBS Amharic