በጅሮንድ ጆሽ ፍራይደንበርግ በኮሮናቫይረስ ቀውስ ምክንያት አውስትራሊያ ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት ወዲህ የአገሪቱ ፋይናንስ ወጀብ የገጠመው መሆኑን አስታውቀዋል።
ይህንንም በአኃዝ አስደግፈው ሲገልጡ "አውስትራሊያ ኮሮናቫይረስን ለመከላከል በወሰደቻቸው እርምጃዎችና የገቢ ማሽቆልቆል ሳቢያ በ2019-2020 የ $85.8 ቢሊየን በ2020-2021 የ $184.5 ተረፈ ፈሰስ ጉድለት" እንደገጠማት ተናግረዋል።
ባለፈው ወርኃ ጁላይ $488.2 ቢሊየን ደርሶ የነበረው ብሔራዊ የተጣራ ዕዳ መጠን በሚቀጥለው ዓመት $677.1 ቢሊየን ወይም ከጠቅላላው የአገሪቱ ምጣኔ ኃብት ከሶስት እጅ የበለጠ እንደሚሆንም አመላክተዋል።
የሥራ አጥነት ቁጥር መጠንም በዲሴምበር 9.25 ፐርሰንት እንደሚደርስ ጠቁመዋል።
ባለፈው ወርኃ ጁን የሥራ አጥነት ቁጥር 7.4 መድረሱ ይታወሳል።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ የአውስትራሊያ ማኅበራዊ አገልግሎት ምክር ቤት በዲሴምበር ከ10 አውስትራሊያውያን አንድ ለሥራ አጥነት እንደሚዳረግ የፌዴራል መንግሥቱን ሪፖርት ዋቤ በመንቀስ፤ የጉዳዩ አሳሳቢነት በሚሊየን ለሚቆጠሩ አውስትራሊያውያን የከፋ በመሆኑ መንግሥት በሥራ ፈጠራ ላይ በእጅጉ ሊታትር እንደሚገባና ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን ወገኖች ሊያረጋጋ እንደሚገባ አሳስቧል።
የፌዴራል መንግሥቱ $164 ቢሊየን ለድጎማ ለማዋል አቅዷል። ይፋ ከተደረገውም ውስጥ $84 ቢሊየን ለሥራ ጠባቂ የደመወዝ ድጎማና $17 ቢሊየን ለሥራ ጠያቂ ድጋፍ ይውላል።
የቪክቶሪያ በሁለተኛ ዙር የኮሮናቫይረስ ገደቦች ስር መግባትም ከብሔራዊ ምጣኔ ሃብቱ ላይ የ$3.3 ቢሊየን እጦት አሳድሯል።

