የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ ኢትዮጵያ እሳቸው ያመቻቹትን ውል አልፈርምም ብላ ራሷን በማግለሏ ሳቢያ የእርዳታ ገንዘብ እንደነፈጓትና ግብፅ የሕዳሴ ግድብን ማጋየት እንደነበረባት ተናግረዋል።
ፕሬዚደንቱ ይህን ያሉት በእሥራኤልና ሱዳን መካከል በዩናይትድ ስቴትስ አማካኝነት የሰላም ስምምነት ላይ መደረሱን ትናንት ዓርብ ከዋይት ሃውስ ኦቫል ቢሮ ጋዜጠኞች በተገኙበት ባደረጉት ንግግር ነው።
አቶ ትራምፕ በንንግራቸው ወቅት የታላቁ ሕዳሴ ግድብን አስመልክተው ሲናገሩ "ይህ በጣሙን አደገኛ ሁኔታ ነው፤ ስለምን ግብፅ በዚህ ዓይነት መኖር አይቻላትምና" ብለዋል።
አያይዘውም፤ ግብፅ "ግድቡን ለማጋየት" ልትበቃ እንደምትችልና እሳቸውም ግብፆች "ያን ግድብ እንደሚያጋዩት" ጉልህና ግልፅ በሆነ መልኩ ስለመናገራቸው ተናግረዋል።
ከቶውንም ግድቡ ሲገነባ ግብፅ ለምን ዝም ብላ እንደተመለከተች ባግራሞት መጠየቃቸውንና ከግብፅ በኩል በወቅቱ "አነስተኛ የሆነ አብዮት" ገጥሟቸው የነበረ መሆኑን ስለመረዳታቸው ተናግረዋል።
አክለውም "ግብፅ አንድ ነገር ማድረግ አለባት" ብለዋል።
ኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን ፊርማቸውን እንዲያኖሩበት በዩናይትድ ስቴትስ የተሰናዳውን የውል ረቂቅ ኢትዮጵያ እምቢኝ ማለቷ ስህተት ስለመሆኑና በዚያም ሳቢያ የእርዳታ ገንዘብ ለኢትዮጵያ መንፈጋቸውን ሲገልጡ " ያ ትልቅ ስህተት ነበር። ያን በማድረጋቸውም በርካታ እርዳታ ገትተንባቸዋል፤ ያን ስምምነት ካልተቀበሉ ገንዘቡን በጭራሽ አያገኙትም። ሆኖም ውኃ ወደ ዓባይ እንዳይፈስ የሚገታ ግድብ ገንብተዋል። ግብፅ በመጠኑ ብስጩ ብትሆን ልትወቅሷት አትችሉም - አይደል?" በማለት የአስተዳደራቸውን አቋም አስታውቀዋል።
ለሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክም ኢትዮጵያ ስምምነቱን እንድትቀበል እንዲያግባቡ አሳስበዋል።
እስካሁን በኢትዮጵያ መንግሥት በኩል ይፋ የአፀፋ ምላሽ ባይደመጠም የቀድሞው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በቲዊተር ገፃቸው እንዲህ ባለው ኃላፊነት በጎደለው ንግግር ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን እንደማይደናገጡ ገልጠዋል።


