የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ቃል አቀባይ ስቴፋን ዱጃሪክ በቀን በአማካይ 4,000 ያህል ኢትዮጵያውያን ወደ ሱዳን በስደት መዝለቅ ጋር ተያይዞ የስነ ንጽሕና አጠባበቅና የኮሮናቫይረስን መከላከል ጉዳይ ያሳሳሰባቸው መሆኑን ገለጡ።
አቶ ዱጃሪክ በአሁኑ ወቅት ያለ መጠለያ ሜዳ ላይ የሚገኙ ስደተኞ ቤተሰቦችና ሕጻናት መኖራቸውንም ገልጠዋል።
የስደተኞቹን ጉዳይ አስመልክቶ የተመድ ሰብዓዊ ረድኤት አስተባባሪ ባባካር ሲሴ፣ የተመድ ከፍተኛ የስደተኞች ኮሚሽን፣ የዓለም ምግብ ፕሮግራም፣ የተመድ ሕጻናትና የተመድ ስነ ሕዝብ ድጎማ መሪዎች የስደተኞቹን አያያዝ ሁኔታ ለመገምገም በመጠለያ ካምፖች ተገኝተው ተመልክተዋል።
ድርጅቱ 30,000 ያህል ኢትዮጵያውያን ከትግራይ የሱዳንን ድንበር አቋርጠው የዘለቁ መሆኑን ረቡዕ ዕለት ጠቁሟል።
ቃል አቀባዩ "የተመድ ቡድን ሰዎች ወደ ተሻለ የስደተኛ ካምፖች ከመዛወራቸው በፊት በማስተናገጃ ማዕከላት ውስጥ ከሁለት ቀናት በላይ እንዳይቆዩ እንዲደረግ ከሱዳን መንግሥት ጋር እየሠራ መሆኑን" ተናግረዋል።
አያይዘውም ቡድኑ 4,440 ኢትዮጵያውያን ስደተኞች የሚገኙበትን ኡም ራቁባ ካምፕ እንደጎበኘና ካምፑ 10,000 ሰዎችን እንዲያስጠልል መዘጋጀቱን እንዲሁም የማስተናገጃ ማዕከላት ድንበር አቋርጠው የሚመጡ ተጨማሪ ሰዎችን ማስጠለል እንዲችሉ እየተደረገ መሆኑንም አስታውቀዋል።

