የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ሁለተኛ ዙር ውኃ ሙሌትን አስመልክቶ የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታ ምክር ቤት በኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብፅ መካከል ባለው ውዝግብ ሊወያይ እንደሚችል የወቅቱ የወርኃ ጅጁላይ የምክር ቤቱ ፕሬዚደንትና በተመድ የፈረንሳይ አምባሳደር ኒኮላስ ዴ ሪቪዪሬ ገለጡ።
በሕዳሴ ግድብ የሁለተኛ ዙር ሙሌት ላይ የተመድ ፀጥታ ምክር ቤት እንዲወያይበት ጥሪ ያቀረቡት የዓረብ መንግሥታት ሲሆኑ፤ የጥሪያቸው አስባብም ያለ ሱዳንና ግብፅ ስምምነት ኢትዮጵያ ለሁለተኛ ጊዜ ግድቡን ልትሞላ ነው የሚል ነው።
በኢትዮጵያ በኩል በተደጋጋሚ የሕዳሴ ግድብን አስመልክቶ ከሱዳንና ግብፅ ጋር ለመወያየት የምትሻው በአፍሪካ ኅብረት በኩል እንጂ በተመድ ፀጥታ ምክር ቤት አማካይነት እንዳልሆነ አስታውቃለች።
የዓረብ አገራቱን የፀጥታ ምክር ቤት በጉዳዩ ላይ ይምከር ጥሪን አስመልክቶ ዴ ሪቪዬሬ ሲናገሩ "የፀጥታ ምክር ቤቱ ማድረግ የሚችለው ነገር ትንሽ ነው። አገራቱን አገናኝቶ ስጋቶቻቸውን በጋራ እንዲገልጡ ከማድረግና ከስምምነት ላይ ለመድረስ ወደ ድርድር እንዲመለሱ ከማበረታት ባሻገር መከወን የሚችለው ነገር የለም" ሲሉ ለሪፖርተሮች መግለጣቸውን ዓለም አቀፍ የብዙኅን መገናኛ አውታራት ዘግበዋል።
ኢትዮጵያ የግብፅንና ሱዳንን ይሁንታ ሳትጠብቅ በሁለተኛ ዙር የውኃ ሙሌት ዕቅዷ እንደምትቀጥልና ግብር ላይም እንደምታውል በተለያዩ የአገር ውስጥና ዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ ገልጣለች።

ይህ በእንዲህ እንዳለም፤ ዓርብ ጁላይ 2 የተመድ ፀጥታ ምክር ቤት ከስድስት ዝግ ስብሰባዎች በኋላ በትግራይ ቀውስ ላይ ግልፅ ውይይት እንዲካሔድ አድርጓል።
በዕለቱም የተመድ ረድኤት ኃላፊ ራሜሽ ራጃሲንግሃም ትግራይ ውስጥ ተከስቶ ያለው የረሃብ አደጋ ከፍ ወዳለ አሳሳቢ ደረጃ መሸጋገሩን አንስተው ቀደም ሲል ለረሃብ በእጅጉ ከተጋለጡት በ50 ሺህ በመጨመር ቁጥራቸው ወደ 400 ሺህ መድረሱን በመግለጥ ለምክር ቤቱ አባላት ልብ አሰኝተዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ባለፈው ሰኞ የወጀውን የተናጠል ተኩስ ማቆም ተመርኩዘው የዩናይትድ ስቴትስ የተመድ አምባሳደር ሊንዳ ቶማስ ግሪንፊልድ የኢትዮጵያ መንግሥት "የተኩስ ማቆም እወጃው ስለ እውነት የሰብዓዊ ቀውሱን በመግታት መንፈስ መሆኑን ማሳየት አለበት" ሲሉ አጠንክረው ተናግረዋል።
ከሶስት በላይ የአፍሪካ አገራትን ወክለው የተናገሩት በተመድ የኬንያ አምባሳደር በበኩላቸው የተኩስ ማቆሙ እወጃን በመልካም ጎኑ እንደተቀበሉትና ተከስተው ያሉ ችግሮችን በአፍሪካውያን ለመክላት ለአፍሪካና ለኢትዮጵያ ዕድል ሊሰጥ እንደሚገባ አሳስበዋል።
በተመድ የኢትዮጵያ አምባሳደር ታየ አጽቀስላሴ በበኩላቸው የተኩስ ማቆሙ የታወጀው የረድኤት ተደራሽነት ይበልጥ የተሻለ ለማድረግ እንደሆነ ጠቁመው ፤ የኢትዮጵያ ወዳጆችም ድጋፋቸውን ከፍ ጫናቸውን ዝቅ እንዲያደርጉ እንደሚያግዝ ተናግረዋል።
ድምፅን በድምፅ የመሻር መብት ያላቸው በተመድ የሩስያና ቻይና አምባሳደራትም በፊናቸው ግጭቱ የኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ መሆኑን በማንሳት በፀጥታ ምክር ቤቱ ለመፍታት የሚደረጉ ሙከራዎች ከጥቅማቸው ጉዳታቸው እንደሚያይል አሳስበዋል።

