የተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት የሕዳሴ ግድብን አስመልክቶ በመጪው ሳምንት ሊታደም ነው

በመጪው ሳምንት ሰኞ ለተባበሩት መንግሥታት የጸጥታ ምክር ቤት መታደም አስባብ የሆነው ግብፅና ሱዳን የሕዳሴ ግድብ ፕሮጄክትን አስመልክቶ ያቀረቡትን የቅሬታ አቤቱታዎች ለመመልከት ነው።

UNSC meeting

Source: Courtesy of AI

ግብፅ ሰኞ ዕለት ይካሔዳል ተብሎ የሚጠበቀው የጸጥታው ምክር ቤት ስብሰባ በዝግ ስብሰባነት እንዲካሄድ ጠይቃለች። 

ግብፅ የሕዳሴ ግድብ ፕሮጄክት በኢትዮጵያ በኩል ተይዞ ባለው ዕቅድ ከቀጠለ "ለህልውናዬ" አስጊ ነው ስትል፤ ሱዳን በበኩሏ በሚሊየን ለሚቆጠሩ ሱዳናውያን ሕይወቶች ጥፋት "ታላቅ አደጋ" ነው ስትል አቤት ብላለች። 

ይሁንና ኢትዮጵያ በሕዳሴ ግድብ ሙሌት ላይ ግብፅና ሱዳን ተስማሙም አልተስማሙም በወርኃ ጁላይ የመጀመሪያ ሙሌቷን ለማካሄድ መወሰኗን በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ ገዱ አንዳርጋቸው በኩል በይፋ አስታውቃለች።

ይህንኑ በሶስቱ አገራት መካከል ተቅስቅሶ ያለውን ሁኔታ አስመልክተው የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ሲናገሩ "እንዲህ ካለ ሁኔታ የመውጫ ብቸኛው መንገድ በባለ ጉዳዮቹ መካከል ውይይት በማካሄድ ነው። በእኛ በኩል ባለጉዳዮችን ለማገልገል ፍጹም ፈቃደኞች ነን" ብለዋል።

የጸጥታው ምክር ቤት የሰኞ ስብሰባውን በይፋ ከማካሄዱ በፊት ከወዲሁ ይፋዊ ባልሆነ መልኩ የሶስቱ አገራት ጉዳዮቹን አስመልክቶ መክሯል።

የመንግሥታቱ ድርጅት ቃል አቀባይ በበኩላቸው " ግብፅን እያበረታታን ነው፤ ኢትዮጵያና ሱዳንንም እንዲሁ ተከስተው ያሉ ልዩነቶቻቸውን ሰላማዊ በሆነ መንገድ ለመግታት ጥረቶቻቸውን ከፍ እንዲያደርጉ እያበረታትን ነው" በማለት ተናግረዋል።

ቃል አቀባዩ አክለውም ሶስቱ አገራት ግድቡን አስመልክተው 'መተማመንን መሠረት ባደረገ መልኩ ዓለም አቀፍ ሕግን ተከትለው ለመተባበርና በጋራ ለመጠቀም' በ2015 የተፈራረሙበትን የመርሆ ሰነድ ጠቀሜታ ልብ እንዲሉ አሳበዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለም፤  ትናንት ዓርብ ሰኔ 20 - 2012 የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ የሕዳሴ ግድብ ሙሌትና የውኃ አጠቃቀም ደንብ ላይ በሶስቱ አገራት መካከል እየተካሄደ ያለውን ድርድር አስመልክቶ ምክክር ማድረጉን በመግለጫው አስታውቋል።

ጽሕፈት ቤቱ ስብሰባው የተጠራው በወቅቱ የአፍሪካ ሕብረት ፕሬዚደንት በሆኑት የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚደንት ሲሪል ራማፎዛ እንደሆነና በስብሰባው ላይም ኢትዮጵያን ጨምሮ የሱዳን፣ ግብፅ፣ ኬንያ፣ ማሊና የኮንጎ ዲሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ መሪዎች መታደማቸውን ገልጧል። 

አያይዞም፤ ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብፅ መግለጫዎቻቸውን ያቀረቡና የወደፊት ቀጣይ ሂደት አቅጣጫዎችም መቀመጣቸውን አስፍሯል።

ይህንንም መሠረት በማድረግ "በግድቡ ሙሌትና አስተዳደር ላይ የሚደረገው ድርድር በሚቀጥሉት ሁለት ሳምንታት እንዲጠናቀቅ ተስማምተዋል። ኢትዮጵያ በመጪዎቹ ሁለት ሳምንታት የግድቡን ቀሪ የግንባታ ሥራዎች በማጠናቀቅ ሙሌት ትጀምራለች" ሲል አስታውቋል።

 

    


2 min read

Published

By Kassahun Seboqa Negewo


Share this with family and friends


Follow SBS Amharic

Download our apps

Watch on SBS

SBS World News

Take a global view with Australia's most comprehensive world news service

Watch now