የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ደኤታ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴንና የአገር መከላከያ ሠራዊት ግንባታ አስተባባሪ ሌተና ጄኔራል ባጫ ደበሌ ትናንት ጁን 30 በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ የአገሪቱ ዋነኛ ብሔራዊ ደኅንነት ሥጋት ሕወሓት አለመሆኑንና የኢትዮጵያ ለውጭ ሥጋት የመጋለጥ ሁነት የጎላ መሆኑን ገልጠዋል።
ሚኒስትር ደኤታ ሬድዋን የተኩስ ማቆሙ እወጃ ትልሞች የሕግ ማስከበሩን ዘመቻ፣ የአገሪቱን ቀጣይነት፣ የትግራይ ሕዝብን ሥጋቶችና ዓለም አቀፍ ማኅበረሰቡን ያካተተ ስለመሆኑ ተናግረዋል።
አክለውም፤ በዘመቻው ወቅትም የሕወሓትን ታጣቂዎች መምታት፣ የተዘረፉ መሣሪያዎችን ማስመለስ ወይም ማውደም፣ የፌዴራሉን ጦር አባላት ከሕወሓት ማስለቀቅና ወንጀለኞችንም ተጠያቂ እንዲሆኑ መደረጉንና ሕወሓት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ደኅንነትን የሚያሰጋ ጉዳት እንደማያደርስ አመላክተዋል።
ሚኒስትር ደኤታው ለትግራይ መልሶ ማቋቋሚያና የሰብዓዊ ተግባራት ማከናወኛ እስከ 100 ቢሊየን ብር ድረስ ወጪ የወጣ በመሆኑ አገራዊ ኢኮኖሚ ላይ ጉዳት ማድረሱን ሲገልጡ "የወጣው ወጪ የመከላከያን ወጪ ሳይጨምር ነው። ይኼም የትግራይን ዓመታዊ በጀት ለአሥራ ምናምን ዓመታት መሸፈን የሚችል ነው። የትግራይ ዓመታዊ በጀት ስምንት ቢሊየን ብር ነው" ብለዋል።
ሌ/ጄ ባጫ በበኩላቸው፤ ሕወሓት ለአገሪቱም ሆነ ለፌዴራል መንግሥቱ ስጋት የመሆን አቅም እንዳይኖረው መደረጉንና አስፈላጊ ከሆነም በሶስት ወይም ከዚያ ባነሰ ሳምንታት ተመልሶ መግባት እንደሚቻል ጠቁመው፤ የወቅቱ ሥጋት ውጪያዊ መሆኑን አሳስበዋል።
አያይዘውም፤ ጦሩን የማስወጣቱ "ፖለቲካዊ ውሳኔ ከወታደራዊ ትርፍና ኪሳራ አንፃር ዋጋው ከፍተኛ ነው" ብለዋል።
ይሁንና ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይን ጨምሮ በሚኒስትር ደኤታ ሬድዋንና ሌ/ጄ ባጫ ከመቀሌ የወጣነው "የግጭት መስሕብነቷ" በማክተሙ ነው የሚለውን አባባል ሕወሓት በመግለጫው "ፍጹም ሐሰት" ብሎታል።
የፌዴራል መንግሥቱን የተናጠል ተኩስ የማቆም እወጃም "ቧልት" ሲል አጣጥሎታል።
የሕወሓት ቃል አቀባይ አቶ ጌታቸው ረዳ የፌዴራል ሠራዊቱ ከመቀሌ መውጣት "በሽንፈት" እንደሆነ ጠቅሰው "በጦርነቱ ወቅት የወደሙ ወይም የተቋረጡ የኮሙኒኬሽን፣ ትራንስፖርትና ሌሎች አገልግሎቶች ዳግም ግልጋሎቶቻቸውን እስካልጀመሩ ድረስ ከኢትዮጵያ ጋር ድርድር አናካሂድም" ሲሉ ለአሶሺየትድ ፕሬስ በሰጡ መግለጫ አስታውቀዋል።
በሌላ በኩል የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳዮች ኮሚቴ ሊቀመንበር ግሪጎሪ ሚክስ "ሕወሓት ወደ ኤርትራ ለመዝለቅ ዛቻዎችን እያደረገ ስለመሆኑ ሪፖርቶችን እየሰማሁ ነው። ይህን ማድረግ ግጭትን እንደሚያባብስ ግልፅ የሆነና አደገኛም ነው። እንዲህ ዓይነት ጥረቶችን በእጅጉ አወግዛለሁ። በሕወሓትም ሆነ በማናቸውም ታጣቂ ቡድን አመፅ የማባባስ ሙከራዎች ላይ ግልፅ መሆን እፈልጋለሁ። አመፅን መቀነስ እንሻለን፤ ተኩስ ማቆምን እንፈልጋለን" ሲሉ አሳስበዋል።

