የጆ ባይደን አስተዳደር ለግብፅ ይቸር ከነበረው $300 ሚሊየን ዶላርስ ወታደራዊ ልገሳ ውስጥ $130 ሚሊየን ዶላርስ ችሮታውን ከሰብዓዊ መብቶች አያያዝ ጋር በተገናኘ ሁኔታ አቅቦ መያዙ ተገለጠ።
በዩናይትድ ስቴትስ ብሔራዊ ደኅነት ጥቅም ስም ለግብፅ ይሰጥ የነበረው የወታደራዊ ዕርዳታ ተገትቶ የተያዘው በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል ሲሆን "ያለንን አሳሳቢ የሰብዓዊ መብቶች ጉዳይ አስመልክተን ከግብፅ ጋር መወያየቱን እንቀጥልበታለን" ሲሉ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ቃል አቀባይ አስታውቀዋል።
ይሁንና አሳስቢ ያሏቸውን የሰብዓዊ መብቶች አያያዝ አልገለጡም።
ዩናይትድ ስቴትስ ከ2017 የፋይናንስ ዓመት አንስቶ ለግብፅ በየዓመቱ $1.3 ቢሊየን ዶላርስ ትለግሳለች።
የእርዳታ ጭነት መኪናዎች
ከጁላይ 12 ጀምሮ ረድኤት ለማድረስ ወደ ትግራይ ዘልቀው ከነበሩ 445 ከባድ የጭነት ተሽከርካሪዎች ውስጥ 38ቱ ብቻ በመመለሳቸው የወደፊት የእርዳታ አቅርቦት ላይ ጉዳት እንደሚያደርስ የተባበሩት መንግሥታት የዓለም ምግብ ፕሮግራም አሳስቧል።
ይህንኑ የገለጡት የዓለም ምግብ ፕሮግራም ቃል አቀባይዋ ጄማ ስኖውደን "በአሁኑ ወቅት ሰብዓዊ እርዳታዎችን ወደ ትግራይ ለማድረስ ይህ ዋና መሰናክል ነው። በከባድ ጭነት ተሽከርካሪዎች እጥረት ሳቢያ በቂ የሆኑ ቅልፈቶችን ማሰናዳት አልቻልንም። ከትራንስፖርት ግልጋሎት ሰጪዎችና የትግራይ የአካባቢ ባለስልጣንት ጋር የጭነት መኪናዎቹ እንዲለቀቁ መሥራታችንን እንደቀጠልን ነው" ብለዋል።
ወ/ሮ ስኖውደን የጭነት መኪናዎቹ የት እንዳሉና በምን ግልጋሎት እየዋሉ እንደሆነ የማያውቁ መሆኑንንም አክለው ገልጠዋል።

